
አዲስ አበባ፦ በሞጆ ከተማ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንደተሰጠ ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
የሞጆ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ እሸቱ ሹሚ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በሞጆ ከተማ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በንግድና አገልግሎት እንዲሁም በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሠማራት ፍላጎት ላላቸው 60 አዳዲስ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል። ከእነዚህም ውስጥ 30 ለሚሆኑት ባለሀብቶች የመሥሪያ ቦታ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
ፈቃድ የተሰጣቸው ኢንቨስትመንቶች ወደ ሥራ ሲገቡ አንድ ሺህ 140 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተናግረው፤ ይህም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
በባለፈው በጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶችም ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አመልክተው፤ በአጠቃላይ በሞጆ ከተማ 29 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 297 ባለሀብቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ለ29 ሺህ 605 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ የገለጹት አቶ እሸቱ፤ በቀጣይም በርካታ ባለሀብቶችን ወደ ከተማዋ ለመሳብ የንግድ ቀጣናንና የኢንዱስትሪ አካባቢን የማስፋት እንዲሁም መልሶ ልማት የሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች የመለየት ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
በቆዳ ፋብሪካ፣ በሥጋና ቄራዎች፣ በኮንስትራክሽን እና በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሠማራት ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮችና ባለሀብቶች ሞጆ ከተማ ምቹ መሆኗን ጠቁመው፤ ከተማ አስተዳደሩ የከተማውን የወደፊት እድገት ታሳቢ ያደረገ የከተማ ፕላን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ይህም የከተማውን ደረቅ ወደብ እና የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን መሠረት ባደረገ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ እሽቱ፤ ይህም የከተማዋን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መሠረት ያደረገ ኢንቨስትመንት እንዲበራከት የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
የሞጆ ከተማን የኢንዱስትሪና የሎጀስቲክስ ከተማ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረው፤ ከተማው ያለውን እምቅ አቅም በሚዲያና በሌሎች አማራጮች የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም