ከተፈጥሮ ጋር ዘላቂ እርቅ የመፍጠር መነሳሳት!

ሀገርን አረንጓዴ የማልበስ ንቅናቄ /አረንጓዴ ዐሻራ/ ባለፉት ስድስት ዓመታት እጅግ ስኬታማ ከሚባሉት የለውጡ ሕዝባዊ መነሳሳቶች በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው። ንቅናቄው እንደሀገር ተራቁቶ የነበረውን የተፈጥሮ አካባቢ ዳግም ሕይወት እንዲዘራ/እንዲያገግም ከማስቻል ባለፈ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገዘፈ እውቅና ያገኘንበት ታሪካዊ የጋራ ስኬታችን ነው።

ያለፉት ሦስት እና አራት መቶ ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች የሀገሪቱ ተፈጥሯዊ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች፣ ለተለያዩ አደጋዎች ተጋልጠው የነበሩባቸው ጊዜያት ናቸው። ይህንን ተከትሎም የሀገሪቱ የደን ሀብት በብዙ የተመናመነበት፤ ከነበረበት 45 ከመቶ፤ ወደ 3 ከመቶ በታች የወረደበት፤ ከዚህም በላይ ለከፋ አደጋ ተጋላጭ በሆነ ስጋት ውስጥ ለማለፍ የተገደደበት ነበር።

ችግሩ አጠቃላይ በሆነው ሀገራዊ የአየር ንብረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ከማስከተል ባለፈ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ተጨባጭ የሆነ የተፈጥሮ አደጋዎች፤ ድርቅ እና በረሃማነትን በመፍጠር የዜጎችን ሕይወት አስቸጋሪ ያደረገበት ሁኔታ ተከስቷል። ችግሩ ከሌሎች ሀገራዊ ችግሮች ጋር ተዳምሮ ለተጨማሪ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምንጭ ሆኗል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ካለው የአየር ሙቀት መጨመር ጋር ተጣምሮ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ሀገሪቱን ለተደራረቡ ችግሮች ዳርጓታል። ስለ ችግሩ ከፍ ባለ ድምፅ ከማዜም ባለፈ ተጨባጭ ዘላቂ ስትራቴጂክ መፍትሔ ማምጣት ባለመቻሉም ችግሩ በዓመታት መካከል እየገነገነ አጠቃላይ የሕልውና ስጋት ሆኖ ተከስቷል።

ችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ካላገኘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው እና ለዓለም ስጋት ከሆነው የአየር ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ፣ የአሁኑን ብቻ ሳይሆን የመጪ ትውልዶችን በሕይወት የመኖር ዕድል አደጋ ውስጥ የሚከት፣ እንደ ሀገር ካለንበት ድህነት እና ኋላቀርነት ጋር ተዳምሮ የሕዝባችንን ነገዎች ተስፋ የሚያደበዝዝ ከሆነም ዓመታት ተቆጥረዋል።

ለችግሩ በሕዝባዊ መነሳሳት ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ በለውጡ ማግስት የተዘመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አሁን ላይ ይህንን ሀገራዊ ስጋት ወደ መልካም አጋጣሚ በመለወጥ ትውልዱን የደመቀ ታሪክ ባለቤት እንዲሆን እያስቻለው ይገኛል። የተፈጥሮ አካባቢ እንዲያገግም በማድረግ የዜጎችን/የትውልዶችን በተሻለ የተፈጥሮ አካባቢ የመኖር ተስፋን ወደሚጨብጥበት እውነታ እየለወጠው ይገኛል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እንደአንድ ሜጋ ሀገራዊ ፕሮጀክት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እየፈሰሰበት ያለ፤ መላውን ሕዝብ ያሳተፈ፤ “ዛሬ ላይ ነገን የመሥራት” ሀገራዊ መነቃቃታችን አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ለተፈጥሮ አካባቢ ከእንቅልፍ የመንቃት ያህል ተደርጎ የሚታሰብ፤ ቀጣይ ዘመናትን በተሻለ ተስፋ መጠበቅ የሚያስችል ነው።

በአረንጓዴ ዐሻራ በተደረገው ሕዝባዊ ርብርብ እንደ ሀገር 3ከመቶ ደርሶ የነበረውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን አሁን ላይ ወደ 27 ከመቶ ማድረስ የተቻለበት እውነታ ተፈጥሯል። ይህን ተከትሎም ቀደም ባሉት ወቅቶች የደረቁ ሐይቆች ማገገም ችለዋል፤ የወንዞቻችንም የፍሰት መጠን እየጨመረ ነው። ወደ በረሃማነት እየተለወጡ የነበሩ አካባቢዎችን እያገገሙ ነው።

መርሐ ግብሩ የተፈጥሮ አካባቢን እንዲያገግም በማድረግ ከተፈጥሮ ጋር እርቅ ከመፍጠር ባሻገር፤ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አጠቃላይ ከሆነው ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ከጀመርነው ሀገራዊ መነሳሳት ጋር ስትራቴጂክ ጥብቅ ትስስር ያለው ነው። አሁን ላይ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መሆን የቻለ፤ በቀጣይም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር የነበረንን የተጋላጭነት ስጋት በመቀነስ በገንዘብ የማይገመት አበርክቶ ያለው ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሚካሄዱ የችግኝ ተከላዎች ለገበያ ቀርበው ትርጉም ያለው ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን ታሳቢ አድርጎ የመተግበሩ እውነታ፤ ለዜጎች ከዚያም ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ ተጨማሪ አቅም መሆን የሚያስችል ነው። ይህም አሁን ላይ በቡና እና በአቦካዶ ላይ በተጨባጭ የሚታይ ስኬት ሆኗል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ባለቤት የሆነው ይህ ትውልድ፤ በየዓመቱ ችግኞችን በማፍላት፣ በመትከል እና በመንከባከብ እያደረገ ያለው ተሳትፎ፤ ለተፈጥሮ አካባቢ ትንሳኤ የማጎናፀፍ በታሪክ ውስጥ ድምቆ የሚታሰብ፤ ትናንቶችን በአግባቡ የመረዳት እና የመካስ፤ ነገን ብሩህ እና ባለቡዙ ተስፋ የማድረግ የትውልዶች ተልዕኮ አንድ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ይህንን ትውልድ የዚህ የገዘፈ ሀገራዊ አጀንዳ ባለቤት ከመሆን ባለፈ፤ በጭቃ እና በዝናብ ውስጥ ሆኖ የሚተከለው እያንዳንዱ ችግኝ፤ የራሱን እና የመጪ ትውልዶች ብሩህ ነገዎች የመፍጠር እና የማብዛት፤ ከዚያም በላይ ከተፈጥሮ አካባቢ ጋር ዘላቂ እርቅ የመፍጠር ሰብዓዊ ኃላፊነትን የመወጣት መነቃቃት አድርጎ ሊያስበው እና ሊረዳው፤ ለዚህ የሚሆን ወቅታዊ ዝግጁነት ሊፈጥር ይገባል

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You