ሀገራዊ መረጃ ለአንድ አገር ዕድገት ብዙ ጥቅም አለው። በተለይ በዕቅድ ላይ ተመስርቶ የእድገት አማራጮችን ለመተለም፤ ገበያ ለማፈላለግ፣ የተሻሉ አማራጮችን ለማየት የመረጃ ዋጋ በቀላሉ የሚተመን አይደለም። በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች መረጃዎች ይፋ ቢሆንም በመረጃዎቹ አሰባሰብ ዘዴ ልዩነት የአሃዝ ልዩነቶች ጎልተው ይታያሉ። ይህ የተጣረሰ መረጃ የመረጃውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል። በመረጃው ላይ ተመስርቶም ዕቅድ ለማዘጋጀት አዳጋች ይሆናል። ጠንካራና ደካማ ጎንን ለይቶ የተጠናከረ ቁጥጥር ለማድረግም አያስችልም።
ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በኢትዮጵያና እንደ ዓለም ባንክ ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚወጡ የአሃዝ መረጃዎች አብዛኛውን ጊዜ ልዩነት አላቸው። ልዩነቱ የሚመጣው ደግሞ በመለኪያ መንገዶቹና በመስፈርቶቹ መለያየት እንደሆነ ይነገራል። ይህም በአሃዙ እውነትነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል። ተአማኒነትንም ያሳጣል።
በኢትዮጵያ ባሉ ተቋማትም ጭምር እርስ በእርስ የሚጣረስ የአሃዝ መረጃ ይፋ ሲሆን ተመልክተናል። በተለይ የግብርና ምርትን መጠን በሚመለከት በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስና በግብርና ሚኒስቴር የሚወጡ መረጃዎች አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ ይሆናሉ።
የመረጃዎቹ ልዩነት በህብረተሰቡ ዘንድ የመስሪያ ቤቶቹን፤ እልፍ ሲልም የመንግሥትን ተኣማኒነት ከመገዳደሩ በላይ ገበያ ለማፈላለግም ሆነ ትክክለኛውን መረጃ ለማወቅ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል። ይህ ልዩነት የሚመጣውም ከናሙና አወሳሰድና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልዩነት መሆኑን ተቋማቱ ይገልጻሉ።
ችግሩን ለመፍታትም የመንግሥት ተቋማት ዋናውን የመረጃ ምንጭ የሆነውን የማዕከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ መረጃን ለመጠቀም እንደተስማሙ ታውቋል። ይህም የተጣራ፤ ተአማኒነት ያለው፤ ትክክለኛ ስምምነት የተደረሰበት መረጃ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ያስችላል። በመረጃዎቹ ላይ ተመስርቶ ምርታማነት ለማሳደግ ሆነ ገበያ ለማፈላለግና ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደሚቻል ተጨባጭ መረጃ ለማግኘት ይረዳል።
ለምሳሌ የተለያዩ አገሮች የተለያየ ችግር ያጋጥማቸዋል። በኢትዮጵያም ድርቅና ጎርፍ የተፈጥሮ አደጋዎች ሊያጋጥም ይችላል። እነዚህ አደጋዎች ቀድሞ ለመከላከል ሆነ ለመቋቋም ትክክለኛና ተአማኒ የአሃዝ መረጃ ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ በትክክለኛ መንገድና የመረጃ አሰባሰብ ስልት የተገኘ መረጃ በመጠቀም ለማቀድና የታቀደውን ለመተግበር ያስችላል።
ትክክለኛና ተአማኒ መረጃዎችን መሰብሰብ፤ የሰበሰቡትንም በአግባቡ ማሰራጨት ሲቻል የተሻሉ አቅጣጫዎችን፤ ፖሊሲዎችን፤ ዕቅዶችን በመተለም ለበለጠ ዕድገት መሥራት ይቻላል። እንዲሁም ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ለመዘርጋትም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በጥቅሉ የመረጃዎቹን ትክክለኝነት ከማረጋገጡም ባሻገር እውነት የሆኑ፤ ወይም እውነትነት ያላቸው፤ ወይም ወደ እውነት የተቃረቡ መረጃዎች ሳይንሳዊ መፍትሄዎችና ሀሳቦችን ለማፍለቅም ያግዛሉ። ስለዚህ ይህን ጥሩ ጅምር ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጋር መለኪያቸውንና መስፈርታቸውን በማጣጣም አንድ አገራዊ የሆነ የመረጃ ሥርዓት ለመፍጠር መሥራት ይገባቸዋል።
መንግሥትም የህዝቡን ጥቅም ማስከበር የሚችለው የተጣረሱ መረጃዎችን ይዞ ሳይሆን ከአንድ ቋት የሚወጡ ትክክለኛ መረጃዎችና አስረጂዎችን መሰረት በማድረግ በመሆኑ ተቋማት እንዲናበቡ፤ በተለይም ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጋር የሰመረና የተጣጣሙ እንዲሆኑ ሥርዓት መበጀት አለበት።
ሥርዓቱ ባለመኖሩ አንዳንዴም የውሸት ሪፖርትና መረጃዎች ከተቋማት ይወጣሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ መረጃዎቹን ያወጧቸው ተቋማት የያዟቸው አሀዞች ተመስርቶ ሥራ ሲሠራ ውጤቱን ያዛባዋል። በመሆኑም፤ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ መረጃ በማሰባሰብም ይሁን በመተንተን እንዲሁም አፈጻጸም በማቅረብ ረገድ በተቋማትና በማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መካከል የተናበበና የተጣጣመ የመረጃ ትስስርና ልውውጥ ሊኖር ይገባል እንላለን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2011