የግድቡ ግንባታ በውጭ መገናኛ ብዙኃን እይታ
የህዳሴ ግድብ እአአ በ2020 ሀይል ማመንጨት ይጀምራል (ሮይተርስ)
የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖ ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለን ምንጭ አድርጎ ሮይተርስ እንደዘገበው እአአ በታህሳስ 2020 ግድቡ ሀይል ማመንጨት ይጀምራል። 6450 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የሃይል ማመንጫ ግድብ ባለቤት ያደርጋታል። ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት ከሆነ በሁለት ተርባይነሮች 750 ሜጋዋት ሀይል ለማመንጨት እቅድ አለ። ጨምረውም ግድቡ አጠቃላይ ግንባታው አልቆ እአአ በ2022 በሙሉ አቅሙ ሀይል ማመንጨት ይጀምራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የግድቡን የተርባይን ስራ እንዲሰራ የተሰጠው አገር በቀል ድርጅት የሆነው የብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ውል እንዲቋረጥ ካዘዙ በኋላ ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚኒስትር ደረጃ መረጃ ሲሰጥ የመጀመሪያው ነው። የብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ውል ከገባ በሰባት ዓመታት ውስጥ ምንም አይነት ተርባይን ወደ አገልግሎት አለማስገባቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የግድቡ መገንባት በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል መቃቃር መፍጠሩ የሚታወስ ሲሆን በተለይ በሀይልና በውሃ ይገባኛል ጥያቄ ሲካሰሱ እንደነበር ዘገባው ጠቁሟል። ግብፅ የግድቡ መገንባት የውሃ ተደራሽነቱን ይቀንሰዋል የሚል ፍራቻ ያላት ሲሆን ከኢትዮጵያና ከሱዳን አካባቢ አባይ ወንዝ ላይ ፕሮጀክቶች እንዲሰሩ ፍላጎት የላትም ሲል ዘግቧል። በግድቡ ዙሪያ የሶስትዮሽ ግንኙነት የተጀመረ ሲሆን በግድቡ አካባቢ የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴው ምን መምሰል እንዳለበት በየስድስት ወሩ የአገራቱ መሪዎች ውይይት ያደርጋሉ።
ግብፅ በግድቡ ምክንያት የውሃ እጥረት እንዳያጋጥማት ሰግታለች (ዘዋሽንግተን ፖስት)
ግብፅ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ የመስራት ፍላጎት እንዳላት ካሳወቀችበት ጊዜ አንስቶ ከአባይ ወንዝ የምታገኘው ውሃ ይቀንሳል የሚል ስጋት እንደፈጠረባት ዘዋሽንግተን ፖስት ያወጣው ዘገባ ያሳያል። እአአ 2011 ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስትጀምር በወቅቱ የአረብ ፀደይ በመባል የሚታወቀው የአመፅ እንቅስቃሴ በግብፅ በመቀስቀሱና የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣናቸው በመነሳታቸው ግብፅ የተፈለገውን ያክል ጫና መፍጠር አልቻለችም ነበር።
አሁን ባለው ሁኔታ ግድቡ እአአ 2022 ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን ለግድቡ አራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል። ግድቡ በአለም ሰባተኛ በአፍሪካ አንደኛ የሀይል ማመንጫ ግድብ ነው። ግድቡን መጨረስ የኢትዮጵያ መንግስት ቅድሚያ ስራው ሲሆን የአባይ ተፋሰስ አገራት ግን ውሃው ይቀንሳል የሚል ስጋት አላቸው። የታላቁ የህዳሴ ግድብ በጣም አስፈላጊና ቅድሚያ የሚሰጠው ፕሮጀክት መሆኑን የኢትዮጵያ ውሃ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል።
510 ጫማ ቁመት እና 5 ሺ 840 ጫማ ርዝመት ያለው የግድብ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ እንድትቆጣጠር ያስችላታል። በአሁን ወቅት ግብፅ ከወንዙ 80 በመቶ ተጠቃሚ ነች። በግብፅ የፖለቲካና ስትራቴጂ ጥናት ማዕከል ተንታኝ የሆኑት ሙስጠፋ ከማል እንደሚሉት ከሆነ ግብፅ ዋነኛ ስጋቷ ከወንዙ የሚመጣው ውሃ እንዳይቀንስ ነው። ሙስጠፋ እንደሚሉት ከሆነ፤ በግብፅ በኩል የሚደረገው ድርድርና የዲፕሎማሲ ስራ ምንም አይነት ለውጥ አላመጣም። በኢትዮጵያ በኩል ግድቡን በውሃ የመሙላት ስራውና ሌሎች የግንባታ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የግብፅ ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ አለም አቀፍ ስምምነት እአአ 1929 እና 1959 የተፈረመ ሲሆን፤ በስምምነቱ ግብፅ ከአባይ 55 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ክዩብ ውሃ የመጠቀም መብት እንዳላት ያሳያል። በስምምነቱ ሱዳን በሁለቱ አገራት መካከል የምትገኝ በመሆኑ 18 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ክዩብ ሜትር በዓመት የማግኘት መብት እንዳላት ተቀምጧል። ብሉናይል እና ነጭ አባይ ሱዳን ሲደርሱ የሚደባለቁ ሲሆን ናይል ወንዝ ተብለው ሜድትራንያን ባህር ይገባሉ።
ይህ ስምምነት በአባይ ላይ ለሚሰሩ ማንኛውም ፕሮጀክት የግብፅ ፈቃድ እንዲኖር ደንግጓል። እአአ 2011 ኢትዮጵያ ያለ ግብፅ ፈቃድ ግድብ በመጀመሯ የግብፅ ባለስልጣናትን አበሳጭቷል። በደቡብ ግብፅ አካባቢ የሸንኮራ አገዳ አምራች የሆኑት አህመድ ኖቢ እንደሚሉት፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በግብፅ የተነሳውን ሁከትና ብጥብጥ ተጠቅመው ግድቡን ለመስራት መነሳታቸው ግብፆችን አበሳጭቷል። ግድቡን በውሃ የመሙላት ስራው ለማከናወን የተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ግብጽን ቅሬታ ውስጥ ከቷል። ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ ለመሙላት ሰትፈጥን ለግብፅና ለሱዳን የሚያገኙት ውሃ ይቀንሳል፡:
ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት ሶስት ዓመት እንደሚፈጅ ብትወስንም ግብፅ የውሃ ሙሌቱ ስራ በረጅም ዓመት መከናወን አለበት የሚል እምነት አላት። ግብፅ የተባበሩት መንግስታ ድርጅት ዝቅተኛ የውሃ አቅርቦት ያላቸው አገራት ብሎ ካስቀመጣቸው ውስጥ ትገኛለች። ግብፅ ለህዝቦቿ በዓመት 660 ክዩቢክ ሜትር ውሃ ታቀርባለች። በዚህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የውሃ እጥረት ያለባት አገር ብሎ አስፍሯታል። በግብፅ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር የውሃ እጥረት እየጨመረ መጥቷል። ኢትዮጵያ ግድቡን ሙሉ ለሙሉ መሙላት ስትጀምር የውሃ እጥረት ችግሮች እንደከሚሰቱ በግብፅ የፖለቲካና ስትራቴጂ ጥናት ማዕከል ተንታኝ የሆኑት ሙስጠፋ ከማል ይናገራሉ። አሜሪካ ስነመሬት ጥናት ማህበረሰብ በተያዘው የፈረንጆቹ መጋቢት ወር ባወጣው ሪፖርት ግብፅ 97 በመቶ የአባይን ውሃ መጠቀም ካልቻለች የመድረቅ አደጋ ሊከሰትባት ይችላል።
ሪፖርቱ እንደሚየሳየው ከሆነ የግብፅ ህዝብ ለቀጣይ 50 ዓመታት የውሃ አቅርቦት እጥፍ እንደሚሆን ይጠብቃል። የግብፅ መንግስት እአአ 2025 በኋላ በአገሪቱ ንፁህ ውሃና ሀይል ሙሉ ለሙሉ ማቅረብ እንደሚቸገር ተናግሯል። ግብፅ በአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ያለውን የውሃ ፍሰት ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት ያደረገች መሆኑን በኔዘርላንድ አለም አቀፍ ግንኙነት ኢንስትዩትሽን ስፔሻሊስት የሆኑት ቶቢያስ ቮን ሎሶው ተቀማጭነቱን መካከለኛው ምስራቅ ላደረገ ድረገፅ በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግብፅን ጨምሮ ግድቡ እንዳይሰራ የሚደግፉ ብዙ የውጭ አገራት አሉ። ነገር ግን ታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተገነባ እንደሚገኝ ቮን ሎሶው ጠቅሰዋል። ሱዳንም ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት እንድታቆም ጫና ትፈጥር ነበር።
የኢትዮጵያ መሪዎች የግድቡ መገንባት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሀይል እንዳለው ተናግረ ዋል። ለሶስት አስርተ ዓመታት አገሪቱ የሀይል እጥረት ነበረባት። የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት፤ አገሪቱ የውሃ ፍሰቱን የመቆጣጠር ፍላጎት የላትም። ኢትዮጵያ ግድቡን ገንብታ እድገቷን የማሳደግ ፍላጎት ብቻ ነው ያላት።
ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ አገራትም ጥቅም ይሰጣል። በደቡብ ግብፅ አካባቢ የሸንኮራ አገዳ አምራች የሆኑት አህመድ ኖቢ፤ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ የመገንባት መብት አላት። ነገር ግን ለማመንጫው አነስተኛ ግድብ እንጂ ግብፅን ወደ ረሀብ የሚወስድና ረጅም ዓመት ውሃ ለመሙላት የሚፈጅ ግድብ መስራት አግባብ አለመሆኑን ይናገራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶተር አብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ በኋላ ሙስናን ለመዋጋት፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ለማስተካከልና ከጎረቤት አገራት ጋር ሰላም ለመፍጠር በገቡት ቃል መሰረት እየሰሩ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ግብፅ በመሄድ አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ውይይት አድርገዋል። በግድቡ ዙሪያ የሚነሱ አሉባልታዎች መሰረተ ቢስ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የውሃ ተጠቃሚነትን 60 በመቶ የሚቀንስ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶችን የመረቁ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በግብፅ የግብርና ምርትን ለማሳደግ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ተብሎ የተገመቱ ናቸው። በሌላ በኩልም የግብፅ የቤቶች፣ መሰረታዊ ፍላጎቶችና የከተማ ነዋሪዎች ሚኒስቴር አሜሪካ እህል አምራች ድርጅት ጋር ውል የተፈራረመ ሲሆን፤ ስምምነቱ የአነስተኛ የባህር ውሃ ማጣሪያ ማዕከል ለመገንባት ነው። ለግንባታው ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረጋል። አልሲሲ በአገሪቱ ሩዝና ሸንኮራ አገዳ የሚጠቀሙትን የውሃ መጠን እንዲቀንሱ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2011