ደንዲ፡- ደንዲ ወረዳ የሚገኙ ቅርሶችን ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ ባለመንከባከቡና ለችግሮች መፍትሄ ባለመሰጠቱ ቅርሶቹ ለከባድ አደጋ እየተጋለጡ መሆኑን የወረዳው ነዋሪዎችና አባገዳዎች ገለፁ።
የሬንቦ የመኪና ኪራይና አስጎብኝ ድርጅት ሥራ አስኪያጅና የአካባቢው ተወላጅ አቶ ታፈሰ ሳህሌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አካባቢው በተፈጥሯዊ አቀማመጡ ውብና ለአ ዲስ አበባ ቅርብ ከሆኑ ከተሞች አንዱ ቢሆንም 12 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ባለመሠራቱ ለትውልድ መተላለፍ ያለባቸው ቅርሶች አደጋ አንዣቦባቸዋል።
በርካታ የቱሪስት መስህቦችን የያዘው ደንዲ ወረዳ ተመልካች በማጣቱ ታሪካዊነቱን እያጣ እንደሆነ የሚገልፁት አቶ ታፈሰ፤ በተለይ ሐይቁ የብዙ ቱሪስቶች መስህብ መሆን ቢችልም እድሉን ግን አላገኘም ብለዋል። ይህ ደግሞ መንገዱ ባለመሠራቱ፣ አመራሩም በተገቢው መንገድ ቅርሶቹ እንዲያዙ ባለመሥራቱና ሀብቱንም ባለማስተዋወቁ የመጣ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።
በቦታው ላይ ቅርስ እንዲያስጠብቁና እንዲ ያስተዋውቁ በኃላፊነት የተቀመጡ አካላት የመጀ መሪያ ተግባራቸው በአካባቢው ያለውን ቅርስ አውቆ ማሳወቅ ቢሆንም ሥራቸውን በተገቢው መንገድ አልሠሩም የሚሉት አቶ ታፈሰ፤ «እኛም ቅርስ መኖሩን አናውቀውም» በሚል አስተያየት ሊያልፉት እንደማይገባ አስረድተዋል።
የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ አራተኛ ትውልድ ልጅ የሆኑት አቶ ታደለ ደበበ በበኩላቸው፤ አካባቢው የብዙ ቅርሶች ባለቤት መሆኑን በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የጀርመን ምሁራን ባደረጉት የአርኪዎሎጂ ምርመራ ውጤት አረጋግጠዋል። በደጋ አካባቢ ከሚገኙ ቅርሶች መካከል የጥንት ሰዎች መጠቀሚያ መሣሪያ የተገኘበትም ስፍራ መሆኑንም አስረድተዋል። ነገር ግን ሀብቱ ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ ህዝቡ ባለው ሀብት እንዳይጠቀም ሆኗል። ቅርሶቹም ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጥፋት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የአካባቢው አባ ገዳዎች በበኩላቸው ‹‹እኛን አይቶ መፍትሄ የሚሰጠን አጥተናል። ለ12 ኪሎሜትር አስፋልት ብዙ ነገር እየከፈልንበት ነው። ለሀብታሙ አካባቢያችን መፍትሄ የሚሰጥ መንግሥት የለም። የአካባቢው አመራሮች ያላወቁትና ያልሠሩበት በመሆኑ አካባቢው ምድረ በዳ ሊሆን ነው በሚል ሥጋት ውስጥ ነን» ይላሉ።
እርቃኑን የቀረው የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ቤተ መንግሥት፤ ስምንት ቁጥር ቅርጽ የያዘውና በ700 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የደንዲ ሐይቅ፤ ቋፍ ላይ ያለው የማርያም ቤተክርስቲያን ጥንታዊ ስዕሎችና ሳይቋረጥ ዘመናትን ያስቆጠረው የወሊሶ የገዳ ሥርዓት መተግበሪያ ማዕከል በቦታው ድንቅዬ ቅርሶች ናቸው። ሆኖም የሚሠራለት በማጣቱ ከጥቅም ውጭ እየሆነ መምጣቱንም አንስተዋል።
«ደንዲ ሐይቅን በተፈጥሮ ሐይቅነቱ እንጂ ከበስተጎኑ የተለያዩ የታሪክና የቅርስ ቦታ መገኛ መሆኑን አናውቅም። ሌሎች ቅርሶች መኖራቸውን እኔም ከእናንተ እኩል ነው ያየሁት›› የሚሉት የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ልማት ቡድን መሪ አቶ አበራ ታደሰ፤ በስፍራው በ2010 ዓ.ም የቱሪዝም ቀን ቢከበርም ይህንን ቦታ ባለመጎብኘቱ ችግሩ እንዲገዝፍ እንዳደረገው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አሁንም አደጋ ውስጥ እንደሆነ ቢታወቅም በመንግሥት አሠራር ምክንያት በቀጣይም ቶሎ ለመድረስ እንደሚያስቸግር ገልፀዋል።
«ቅርሶቹ የሚገኙት በአደዋው አርበኛ ‘አባ መላ’ ተብለው በሚታወቁት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴና በአንጋፋውና በገጣሚ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድን የትውልድ ቦታ ቢሆንም ለታሪክነታቸው ሲባል እንኳን መጠበቅ ነበረባቸው» የሚሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባንቲ ለሚ ናቸው።
እርሳቸው እንዳነሱት፤ የችግሩ መከሰት ዋነኛ መንስኤ የአመራሩ ትኩረት ያለመስጠት ነው። ቦታውን በሚገባ አይቶ ቅርሶቹን ማሳወቅ ላይ አልተሠራም። ከራሴ ጀምሮ ከጎብኚ እኩል ማየቴ ትክክል አይደለም። በመሆኑም በቀጣይ ችግሩን ለመቀነስ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር ጊዜያዊ መፍትሄ ለማምጣት ይሠራል። ይሁንና ከፍ ያሉት የመንግሥት አካላት ግን ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው