ዶናልድ ትራምፕ የአውሮፓ ሀገራት የአሜሪካን ነዳጅ እንዲገዙ አሳሰቡ

ዶናልድ ትራምፕ የአውሮፓ ሀገራት የአሜሪካን ነዳጅ እንዲገዙ አሳሰቡ፡፡ በመጪው ጥር ወር 2017 ዓ.ም በይፋ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት የሚገቡት ዶናልድ ትራምፕ ከወዲሁ የአሜሪካ ትቅደም ፖሊሲያቸውን ተግብረዋል፡፡ ቻይናን ጨምሮ ሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ ግብር እንደሚጨምሩ የተናገሩት ትራምፕ፤አሁን ደግሞ የአውሮፓ ኅብረትን አሳስበዋል፡፡

ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሉት “የአውሮፓ ኅብረት የአሜሪካንን ነዳጅ በገፍ እንዲገዙ ነግሬያቸዋለሁ፤ ይህ ካልሆነ ግን ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶቻቸው ላይ የታሪፍ ጭማሪ ይጠብቃቸዋል” ብለዋል፡፡

የአውሮፓ ሀገራት ዋነኛ የነዳጅ አቅራቢ የነበረችው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት መግባቷን ተከትሎ የገበያ ድርሻዋ ቀንሷል፡፡ ከሩሲያ ጥገኝነት መላቀቅ አለብኝ ያለው የአውሮፓ ኅብረት ላለፉት ሶስት ዓመታት ከአሜሪካ እና ኖርዌይ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ሲገዛ ቆይቷል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በተደረገ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድል የቀናቸው ዶናልድ ትራምፕ፤ የአውሮፓ ሀገራት ተጨማሪ ነዳጅ ከአሜሪካ እንዲገዙ ጫና ማድረግ ጀምረዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ የዶናልድ ትራምፕን አስተያየት እንዳየው ገልጾ፤ በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ከአሜሪካ ጋር ጥሩ የንግድ ግንኙነት እንዳለው አሳውቋል፡፡

ተመራጭ ፕሬዚዳንቱ ካናዳ ወደ አሜሪካ በምትልካቸው ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጭማሪ አደርጋለሁ ካሉ በኋላ በሀገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት የተከሰተ ሲሆን፤ ኦታዋ የተባለችውን ካላደረገች የአሜሪካ 51ኛዋ ግዛት ሆና ትቀላቀለን ብለዋል፡፡

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You