አብዛኞቻችን ልመናን የምናውቀው በአሳዛኝ ድምፀት የመላዕክትንና ቅዱሳንን ስም እየጠሩ ነው። ያው እንግዲህ ሁሉም ነገር ሲዘምን ልመናም አብሮ መዘመኑ ነው መሰለኝ አሁን አሁን የልመና ‹‹ስታይል›› እያየን ነው። በነገራችን ላይ የበለፀጉ ናቸው በሚባሉት ሀገራት ልመና በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ ታጅቦ ነው አሉ።
የሙዚቃ መሣሪያዎችን እየተጠቀሙ መለመን በእኛም ሀገር የተለመደ ነው። ለምሳሌ መገናኛ አካባቢ የሚሰሙት ባለዋሽንቶች በዕውቀቱ ሥዩም እንዳለው ለልመና ሳይሆን የባሕል ኪነት ቡድን ውድድር ነው የሚመስለው። የእነርሱ ዋሽንት ግን ለማዝናናት ሳይሆን ለማሳዘን ነው። የዋሽንት ድምፅ ልብ ውስጥ በመግባት ያሳዝናል። በጦር ሜዳ ወቅት ደግሞ ወኔን ለመሙላት ያገለግል ነበር አሉ። በነገራችን ላይ እንደ ፍቅር እስከ መቃብር ያሉ በሰው ጭንቅላት ውስጥ ‹‹ብራንድ›› የሆኑ የዋሽንት ዜማዎች ለልመና መዋላቸው በግሌ ቅር ያሰኘኛል።
አሁን አሁን እያዝናኑ መለመን በብዛት እየታየ ነው። አንዳንድ ወጣቶች ሲለምኑ፤ ልመና ይሁን ለከፋ ያምታታል። ወንዶቹ ‹‹ኧ ቆንጅት? ኧረ የሆነ ነገር ጣል አድርጊ! ኧረ ለምሳ!…›› ይላሉ። ሴቶች ‹‹ኧ ቆንጅዬው! ኧረ ውዱ! ኧረ ለምሳ ያለህን….› ይላሉ። እያዝናኑ ለመለመን ይሁን፣ ይሄኛው የተሻለ ያሳዝናል ብለው ይሁን አላውቅም።
በእርግጥ በእንዲህ አይነት መንገድ ሲለምኑ ብር ሲሰጣቸው ግን አይቼ አላውቅም። አይቼ ባለማወቄ ግን አይሰጧቸውም ብዬ አልደመድምም።
ከ8 ዓመታት በፊት ይመስለኛል ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊት ለፊት ያየሁት ልመና ነው ልመናን ከዚያ በፊት ከማውቀው አይነት የተለየ ያደረገብኝ። ከዋናው መንገድ ዳር ሆነው ሦስት ቆንጅዬ ቆንጅዬ ወጣት ሴቶች (ለዚያውም ዝንጥ ብለው የለበሱ) ወጭ ወራጁን ‹‹የእራት›› እያሉ ይለምናሉ። በመጀመሪያ እንዴት በልመና ይቀለዳል ብዬ ገረመኝ። ነገሩን ቆም ብዬ ሳስተውል ግን ሥራዬ ብለው የምራቸውን የቆሙበት ነው። ሦስቱም ሴቶች ዝንጥ ብለው የለበሱ፣ በሜካፕ የተንቆጠቆጡ ናቸው። እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎች ሰዎችም ግራ በመጋባት ሲያዩዋቸው የምርም ለልመና እንደቆሙ አረጋገጥኩ። አንዳንዱ እያሳቀ ያልፋቸዋል፤ በአዋቂነት ዕድሜ ላይ ያሉት ደግሞ ለምን እንደሆነ አላውቅም በጣም እየተበሳጩ ነው የሚያዩዋቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ለመሳደብ ሁሉ ይቃጣቸዋል። ሴቶቹ ግን በከፍተኛ ተማፅኖ ይለምናሉ፤ ትኩረት ሳይሰጥ ያለፋቸውን ደግሞ በስድብ ይወርዱበታል። ትንሽ ፈገግ ያሰኘኝ ነገር አንድ ሰው ገላመጠን ብለው አርቀው ሲሳደቡ ልመናው እያለፋቸው ነበር።
ልጆቹ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ይመስላሉ። በኋላ ነገሩን ከታዘቡ ሰዎች እንደሰማሁት ተማሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በሚያገኙት ገንዘብ መጠጥ ቤት ሊገቡበት ይችላሉ። ከቤተሰብ ለዚህ ታስቦ ስለማይሰጣቸው ልመና ይገባሉ። ልመናውን እንደ ነውር ሳይሆን እንደ መዝናኛ ጭምር ነው ያዩት።
ልክ የሆነ ልመና አለ ባይባልም፤ ዳሩ ግን የአንዳንዶች ደግሞ አናዳጅ ነው። የሰው ልጅ በተለያየ አጋጣሚ ችግር ይደርስበታል። ቤተሰብ ወይም ጓደኛ በሌለበት አጋጣሚ ችግር ቢደርስ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የተያዩ እርዳታዎች ይጠይቃል። ለምሳሌ አጉል ቦታ የስልክ ባትሪ ቢዘጋ፣ ካርድ በሌለበት ቦታ (ሞባይል ባንኪንግና ቴሌ ብር የማይጠቀም ሊሆን ይችላል) ካርድ ቢዘጋ ‹‹ተባበሩኝ›› ማለት የተለመደ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚም ልመና ነው ብሎ ማንም አይደንቀውም።
በሌላ በኩል የአካል ጉዳተኛና በዕድሜ የገፉ ሰዎች የተለያየ አይነት ርዳታ ቢጠይቁ ለማንም አይደንቅም። ሙሉ ጤነኛ ሆኖ፣ ዝንጥ ብሎ ለብሶ፣ ለዚያውም እያሾፉና እየቀለዱ መለመን ግን ምን ይሉታል?
እነዚህ ከዓመታት በፊት የምታዘባቸው የልመና አይነቶች ነበሩ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሰብዓዊነትን የሚፈታተን የማዘናጋት ልመና ተጀምሯል። ይሄ ልማድ እየዳበረ ከሄደ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትንና ሰብዓዊነትን የሚፈታተንና የሚሸረሽር ይሆናል። ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
በመጀመሪያ የሆነ ትብብር የሚፈልጉ መስለው ያናግሩሃል። የቦታ ስም፣ የተቋም ስም ወይም የታክሲ መያዣ የሚጠይቁኝ፣ ወይም ሌላ የመረጃ ትብብር የሚጠይቁኝ መስሎህ ‹‹አቤት!›› ብለህ ጠጋ ትላለህ፤ ወይም ቆም ስትል እነርሱ ጠጋ ይሉሃል። ይህኔ ለይስሙላ ትንሽ መረጃ የሚመስል ነገር (ቦታ ሊሆን ይችላል) ከጠየቁህ በኋላ ወደ ዋናው ጉዳያቸው ይገባሉ። ዋናው ጉዳያቸው ‹‹እንዲህ ሆኜ፣ እንዲህ ሆኜ…›› በሚል ገንዘብ መጠየቅ ነው። በቀጥታ ገንዘብ ቢጠይቁ የተለመደ የልመና አይነት ስለሆነ እና በጣም ስለተደጋገመ ማንም አይሰጠንም ብለው በማሰብ ነው። እንዲህ በማዘናጋት ሲሆን ግን የተጠየቀው ሰው በይሉኝታ ሊሰጠን ይችላል ብለው በማመን ነው። አስቁሞ መረጃ ሲጠይቁ ከቆዩ በኋላ መጠየቅ ይሉኝታ የሚያስይዝ ስለሚመስላቸው ነው። ወይም የምርም ተቸግሮ ነው የሚል ስሜት ይፈጥራል በሚል ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን ይሄኛው ዘዴ ራሱ የተበላበት ሆኗል። ምናልባት መጀመሪያ አካባቢ የጀመሩት ሰዎች ተጠቅመውበት ሊሆን ይችላል። እየቆየ ሲሄድ ግን በብዙዎች ዘንድ ይለመድና የማያዋጣ ዘዴ ይሆናል።
የዚህ አይነት ልመና ትልቁ ችግሩ የመተባበር ባሕላችንን የሚሸረሽር መሆኑ ነው። መተማመን እንዳይኖር የሚያደርግ መሆኑ ነው። የምርም መረጃ አስፈልጓቸው የሚጠይቁ ሰዎችን የሚተባበራቸው እንዳያገኙ ማድረግ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ አስቡት! ማንኛውም ሰው አዲስ አበባን ከጫፍ እስከ ጫፍ ሊያውቅ አይችልም። ቢያንስ ለተወሰኑ አካባቢዎች እንግዳ መሆኑ አይቀርም፤ ምክንያቱም የከተማ ባሕሪ ነውና የሚቀያየሩ ነገሮች፣ የሚፈርሱና የሚታደሱ ነገሮች ይኖራሉ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ቀደም ሲል የሚያውቃቸው ምልክቶች ይጠፋሉ ወይም ይቀየራሉ፤ ስለዚህ ማንም ሰው ቢሆን ለመጠየቅ ይገደዳል። የንግድ ተቋማትም ሆኑ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለያየ ምክንያት አድራሻ ሊቀይሩ ይችላሉ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ማንም ሰው መረጃ ለመጠየቅ ይገደዳል ማለት ነው፡፡
እንዲህ አይነት የሚያዘናጉ የልመና አይነቶች ግን ሰዎች እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩ የሚያደርጉ ናቸው። ‹‹ወንድሜ! እህቴ! ጋሼ!…›› እያሉ የሚጠሩ ሰዎችን ባላዬ ባልሰማ የሚያልፋቸው ይበዛል ማለት ነው፤ ምክንያቱም በተደጋጋሚ እንደዚያ እያሉ ጠርተውት ልመና ያጋጠመው ሰው ሊሰለችና መተባበሩንም ሊተወው ይችላል። መንገደኛ ባናገረው ቁጥር ‹‹ያው ለልመና ነው!›› የሚል ስሜት ይፈጠርበታል።
እንግዲህ ለጊዜው መፍትሔ ሊሆን የሚችለው በእንዲህ አይነት ምክንያት ከሰብዓዊነታችን አለመራቅ ነው። አጭበርባሪዎች ቢያሰለቹንም መታገስና የተቸገረውንና ያልተቸገረውን ለመለየት መሞከር ነው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም