ከኦሮሞ የባሕል አልባሳት መዘመን ጀርባ ያለችው ዲዛይነር

በዓልን ከዶሮና ጠላ፣ ከቄጤማው ጉዝጓዝና ከምግብ መጠጡ እኩል በዓል የሚያስመስሉት የባሕል አልባሳቶች ናቸው። በበዓላት ወቅት በገጠርም ይሁን በከተማ በባሕል አልባሳት አጊጦና ተውቦ መታየት የተለመደ የሆነውም ለዚህ ነው።

ከበዓላት ወቅት ውጪ የባሕል አልባሳት በብዙዎች ዘንድ ሲዘወተር አይታይም። የባሕል አልባሳት ከበዓል ወቅት ውጪ የባሕል ዘፈን ክሊፖች፣ የሃይማኖት ቦታዎችና የሠርግ ዝግጅቶች ላይ ብቻ የተገደቡ ናቸው ማለት ይቻላል።

የኦሮሞ የባሕል አልባሳት ደግሞ በተለይ በኢሬቻ በዓል ላይ በስፋት ይታያሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በኦሮሞ የባሕል አልባሳት ከኢሬቻ በዓል ውጪ እየተዘወተሩ ማየት እየተለመደ መጥቷል። ለዚህም አልባሳቱ አይነግቡ ሆነው በሚያማምር ዲዛይን መሠራት መጀመራቸው አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳት መዘመንና ማማር ዲዛይነሮች ትልቅ አብዮት መፍጠራቸውን ብዙዎች ይስማማሉ። ይህን አብዮት ከፊት ከሚመሩት መካከል የሎቲ ዲዛይን ባለቤት የሆነችው ዲዛይነር መርሲሞይ ኩምሳ (ሜርሲ) አንዷ ነች።

ሜርሲ ትውልዷ አዲስ አበባ ነው። ቤተሰቦቿ ስለ ባሕል እንድታውቅ አድርገው አሳድገዋታል። የኦሮሞ የባሕል አልባሳትን እየለበሰችም አድጋለች። ከበዓላት ባሻገር በትምህርት ቤት ቆይታዋ የብሔር ብሔረሰቦች ቀንና መሰል አከባበሮች ላይ በነዚህ የባሕል አልባሳት አጊጣለች። ይህም በዓይነት የተለያየ የሆነውን የኦሮሞ የባሕል አልባሳትን አንዱን ከአንዱ እንድትለይ አድርጓታል።

ሜርሲ በኢሬቻ በዓል ላይ ስትታደም በርካቶች በተለያዩ የኦሮሞ የባሕል አልባሳት ተውበው አይታ ተገርማለች። ይህም ለራሷም ይሁን ለሌሎች የኦሮሞን የባሕል አልባሳት ይበልጥ አሳምራና ለመሥራት እንድታስብ አድርጓታል። ያምራሉ ብላ ከምታስባቸው ዲዛይኖች ውስጥ እንከኖችን ነቅሳ በማውጣት እንዲህ ቢሆን የተሻለ ነው እያለችም ታስብ ነበር። ሜርሲ ስድስት እህትና አንድ ወንድም አላት። ከፍ እያሉ ሲመጡ ከእህቶቿ ጋር የተሻለ የኦሮሞ የባሕል ልብስ መፈለግ ጀመሩ። ያኔ ታዲያ ገበያ ላይ ያሉት የልባቸውን መሻት አልሞላ ቢሏቸው ከኢንተርኔት ላይ የተሻሉ ዲዛይኖች በመምረጥ እንደሚፈልጉት የባሕል ልብስ ማሠራት ጀመሩ።

በተለይም ዲዛይን ጎበዝ ናት የምትላት ታናሽ እህቷን ንድፎችን በመያዝ ዲዛይነሮችና ልብስ ሰፊዎች ጋር እያሠሩ የልባቸውን መሻት ይለብሱ እንደነበር ታስታውሳለች።

የኦሮሞ የባሕል አልባሳት አልተሠራባቸውም ብላ ማሰብ የጀመረችው ዲዛይነር ሜርሲ፣ አልባሳቱ ይጎድላቸዋል ብላ የምታስባቸውን ክፍተቶች ለማስተካከል ከሰው ከመጠበቅ የራሷን አሻራ ለማሳረፍ ቆርጣ እንድትነሳ አድርጓታል። ካላት ፍላጎት በተጨማሪ በእውቀት ብትደግፈው የተሻለ እንደሚሆን ስላመነችም የዲዛይን ትምህርት ቤት ገብታ ትምህርት ቀሰመች። ከዚያም ለተወሰነ ጊዜ በቤት ውስጥ ትዕዛዞችን እየተቀበለች መሥራት ጀመረች። በሂደትም “ሎቲ ፋሽን” ስትል የሰየመችውን የባሕል አልባሳት ቤት ከፍታ መንቀሳቀስ ጀመረች። በዚህም የባሕል አልባሳቱ ሳቢ እንዲሆኑ የበኩሏን እያበረከተች ትገኛለች።

ሜርሲ በተለይም የባሕል አልባሳቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ከመለበስ በተጨማሪ በአዘቦት ቀን እንዲለበሱ ትኩረት አድርጋ እየሠራች የምትገኘው ሜርሲ፣ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ የባሕል አልባሳት በኢሬቻ በዓል ላይ ብቻ ከመለበስ መሻገራቸውን ትናገራለች። እንደ እሷ ገለፃ፣ ሰዎች ሠርግ፣ ልደት፣ ክርስትና እና የተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በዘመናዊ መልኩ በተሠሩት የባሕል አልባሳት ሲያጌጡ መመልከት የተለመደ ሆኗል። አሁን ደግሞ ከዝግጅቶችም አልፎ በአዘቦት መለበስ ጀምረዋል።

ዲዛይነሯ ሥራዎቿን በማኅበራዊ ድረ-ገጽ በተለይም በፌስቡክና ቲክቶክ ታስተዋውቃለች። ታዋቂ የኦሮሞ ሞዴሎችም ሥራዎቿን በማኅበራዊ ሚዲያዎቻቸው ያስተዋውቁላት። ሥራዎቿ በተለይም በኢሬቻ በዓልና በሠርግ ወቅት ፈላጊያቸው ብዙ መሆኑን የምትናገረው ሜርሲ፣ ያም ሆኖ በአዘቦትም በዘመናዊ መልኩ የሚሠሩ የባሕል አልባሳት ተፈላጊነታቸው ጨምሯል ትላለች። በተለያየ ጊዜ ለሠርግና የተለያየ ዝግጅቶች ሲኖሩ ሰዎች የባሕል ልብስ ለብሰው መሄድ ፍላጎታቸው ጨምሯል።

በቤቷ የተወሰኑ የተዘጋጁ በዘመናዊ መልኩ የተሠሩ የባሕል አልባሳት አሉ፤ ሰው አይቶ ከወደዳቸውና ልኩ ከሆነ እነሱን ይዞ መሄድ ይችላል። ከዚያ ውጭ ግን ከዚህ ቀደም ከሠራቻቸው የሷ ፈጠራ ከሆኑ አልባሳት መካከል መርጦ ወይ በንግግር አዲስ ዲዛይን ተሠርቶለት በልኩ የማሠራት አማራጭ አለው። ከዛ ውጪም ይሄኛው ልብስ እንዲሠራልኝ እፈልጋለሁ ለሚል ደንበኛውም የፈለገው ልብስ በልኩ ታዘጋጃለች።

የባሕል አልባሳቱን ፈላጊ እየጨመረ የግብዓቶች ዋጋም እየጨመረ መምጣቱን የምትናገረው ዲዛይነሯ፤ ያም ቢሆን የአልባሳቱ ፍላጎት ከፍተኛ ነው ትላለች። ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ውስጥ በቁጥር የነበሩት የኦሮሞ የባሕል ልብስ መሸጫዎች አሁን መበርከታቸውንም ትናገራለች።

ሜርሲ ሀገር ውስጥ ከምትሸጠው በላይ አብዛኛው አልባሳቶቿ ወደውጭ ሀገር የሚላኩ መሆኑን ትናገራለች። በውጪ ያለው የኦሮሞ ማኅበረሰብ ለስብሰባ፣ ለልደት፣ ለሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች በጋራ አንድ አይነት በማዘዝና ተመሳሳይ በመልበስ ዲዛይኗን እንደሚጠቀሙም ትናገራች። ይህም የኦሮሞ ባሕል አልባሳትን የተሻለ ለማዘመን ያላትን ፍላጎት አሳድጎታል። ለአለባበስ ምቹና ማራኪ ሆነው በተለያዩ ቦታዎች ሲለበሱ ማየትም ትፈልጋለች። የባሕል አልባሳቱ ከኢሬቻ በዓልና ከተወሰኑ ፕሮግራሞች ውጪ እንዲለበሱ ለማድረግም ጥረቷን ቀጥላለች። ከኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ባሻገር ሌሎችም ምርቶቿን እንዲጠቀሙም ትሻለች።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You