ፎቶ፡- በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ
አዲስ አበባ ፦ በባሕር በር ጉዳይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ከፈረንሳይ እና ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሚጨበጥ ውጤት እንደሚጠብቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመለከቱ። ፈረንሳይም ባላት አቅም ማድረግ የምትችለውን እንደምታደርግ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስታወቁ።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የኢትዮጵያ የአንድ ቀን ይፋዊ ጉብኝት አስመልክተው ትናንት መሪዎቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር በማግኘት ፍላጎቷ ዙሪያ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በዝርዝር መወያየታቸውን አስታውቀዋል።
130 ሚሊዮን ሕዝብ ይዛ፣ ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች ያለችው ኢትዮጵያ በዓለም ሕግ ፣ በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት ለምታደርገው ጥረት ስኬት እንደ ፈረንሳይ ያሉ ወዳጅ ሀገራት ጠንካራ ድጋፍ ያስፈልጋታል፤ ይህንንም የድጋፍ ጥያቄያችንን ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል በአክብሮት ተቀብለውታል ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ማክሮን ጥያቄውን ስለመቀበላቸው ከፍ ያለ ምስጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ከፈረንሳይ እና ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በባሕር በር ጉዳይ የሚጨበጥ ውጤት የሚጠብቁ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ለታላቁ ቤተመንግሥት እድሳት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መሆናቸውን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በወቅቱም ለእሳቸው ያላቸውን ከፍተኛ ፍቅር እና አክብሮት ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የምታካሂደው የኢኮኖሚ ሪፎርም እንዲሳካ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውን በመጥቀስም፤ ለፕሬዚዳንቱ ከፍያለ ምስጋና አቅርበዋል። ወደፊትም ድጋፋቸው እንዳይለያቸው ጥሪ አቅርበዋል።
“በጣም በርካታ የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግረናል። በዚህም በአፍሪካዊ እና በአውሮፓዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተደጋግፈን ለመሥራት ተግባብተናል ። ከፈረንሳይ ጋር የነበረን የመቶ ሃያ ሰባት ዓመታት ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ ለትውልድ እንዲሻገር በእኔም ሆነ በእሳቸው በኩል አበክረን እንድምንሠራ ቃል ተግባብተናል”ብለዋል። ለነበራቸው ጊዜ ፣ ድጋፍ እና ለጉብኝታቸውም በራሳቸው እና በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ትክክለኛ ነው፤ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ፈረንሳይ ባላት አቅም ማድረግ የምትችለውን እንደምታደርግ አስታውቀዋል።
ጥያቄው በንግግር እና በውይይት፤ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና ጎረቤት ሀገራትን ባከበረ፤ኢትዮጵያን እና ክልሉን በሚጠቅም መልኩ ሊከናወን እንደሚገባ ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቱርክ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ጋር የሰላም ንግግር ማድረጋቸው የሚደገፍ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ፈረንሳውያን ለባሕል እና ለቅርስ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ ያመለከቱት ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፤ በቅርቡ የእሳት አደጋ የደረሰበትን የኖተራንዳም ቤተክርስቲያናችን እንደ አዲስ ታድሶ ለሕዝብ ክፍት መደረጉን፤ በዚህም ፈረንሳውያን በጣም እንደሚኮሩ አስታውቀዋል።
“በቤተመንግሥት እድሳቱ ትላልቅ እና አዋቂ ብለን የምናስባቸው ትውልደ ፈረንሳይ እና ፈረንሳውያን አርክቴክቶች ፣ የሙዚየም እድሳት ባለሙያዎች እና የተለያዩ እውቀት ባለቤቶች ልከናል፤ የአቅማቸውን ማበርከት ችለዋል፤ በዚህም እንኮራለን፤ ሥራው ለእኛም በጣም ኩራት ነው” ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ማስፈን ይቻል ዘንድ የፕሪቶሪያ ስምምነት ትልቅ እርምጃ መሆኑን፤ፈረንሳይ የስምምነቱን ተግባራዊነት እንደምትደግፍ አስታውቀዋል። የእርሻ ሥራን ማበረታታት፣ የተጎዱ ሆስፒታሎችን መልሶ መገንባት፣ ከዛም በተጨማሪ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ የሚሆንበትን እና የሕግ የበላይነት የሚከበርበትን ሁኔታ ማየት እንፈልጋለን ፤ለዚህም እንደቀደመው የሚያስፈልገውን ድጋፍ መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
“ኢትዮጵያ ቀደምት ከሚባሉ ሀገራት አንዷናት። እዚህ በመገኘቴ በጣም ደስተኝ ነኝ ። ይቺ ሀገር በአፍሪካ ታላቅ እና ተስፋ ያላት ሀገር ነች ብዬ ልገልጽ እወዳለሁ። እዚህ ያለነው እንደ ጓደኛ እና ወዳጅ ጭምር ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በእርሶ እንደምተማመንብዎት ልገልጽልዎት እወዳለሁ፤ ፈረንሳይም በኢትዮጵያ ትተማመናለች” ብለዋል።
እኛን የሚያገናኘን የወጣቶቻችን የወደፊት ትክክለኛ እጣ ፈንታ ነው። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኃላፊነታቸውን መወጣት በመቻላቸው ላመሰግን እወዳለሁ። ለወደፊት ቀጣናው ሰላማዊ እና የበለጸገ እንዲሆን ኢትዮጵያ የሚኖራት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ከጉብኝታቸው በኋላ በኤክስ ገጻቸው በአማርኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ለሰው ልጅ መገኛነት የመጀመሪያ አሻራ ያላት ሀገር ናት። በኢትዮ-ፈረንሳይ መካከል ያለው ግንኙነት በታሪክ ሂደትና በትላልቅ የጋራ ፕሮጀክቶች ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።
እ.ኤ.አ በ2019 መሠረታዊ የሆኑ የባህልና የቅርስ ጥበቃን ከሳይንሳዊ ፕሮግራም ጋራ አያይዘን ለመሥራት ወስነን ተነስተናል፤ በላሊበላም የሠራነው በዓለም ላይ ልዩ የሆነ የቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክት በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ አመልክተዋል።
በአንድ ወቅትም የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳት ፕሮጀክትንም ሠርተን ዛሬ የሚያኮራ እውነታ ሆኖ እየታየ ነው። ወደፊትም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዘመንን ለመደገፍ እና በትግራይ የሰላምና የመረጋጋት መሠረት የሆነውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ትብብር እናደርጋለን ብለዋል።
በመልዕክታቸው የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የወደፊቷ የኢትዮጵያ ተስፋ የብልፅግናና የሰላም እንደሚሆን ፈረንሳይ እምነቷ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው በማህበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በብሔራዊ ቤተመንግሥት በነበረን የሁለትዮሽ ውይይት ሰፋ ያለ መጠነ ርዕይ ባላቸው የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል።
ክቡር ፕሬዚዳንት እና የፈረንሳይ መንግሥት በብሔራዊ ቤተመንግሥት በመካሄድ ላይ ባለው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት ሥራዎች ላይ ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋናዬን አቅርቤያለሁ።
በውይይታችን በተለያዩ ዘርፎች የሚኖሩ ትብብሮችን የፈተሽን ሲሆን የፈረንሳይን ኢንቨስትመንት መጨመርን አስመልክቶ ብሎም በትምህርት እና ባሕል ዘርፎች ያለንን ግንኙነት በማጠናከር ጉዳዮች ላይ ተነጋግረናል። ታሪካዊ ትስስራችንን ይበልጥ የመገንባት አስፈላጊነትንም በውይይታችን አፅንኦት ሰጥቼ አንስቻለሁ ብለዋል ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በበኩሉ የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት አስመልክቶ በማህበራዊ ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልእክት፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የመጡትን የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ተቀብለዋል። ፕሬዚዳንቱ በ2011 ዓመተ ምህረት በነበራቸው ጉብኝት ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የእድሳት ሥራ ድጋፍ እንደሚሰጡ አሳውቀው ነበር።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ በታደሰው ብሔራዊ ቤተመንግሥት ክቡር ፕሬዚዳንቱን የተቀበሉ ሲሆን፤ ቤተመንግሥቱንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በሁለትዮሽ ውይይታቸው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፈረንሳይ ለብዙ ዘመናት ተዘንግቶ ለቆየው የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት ላደረገችው የእድሳት ድጋፍ አመስግነዋል።
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል በበኩላቸው፤ አስደማሚውን የቤተ መንግሥት እድሳት አድንቀው፤ በዓድዋ መታሰቢያ ግንባታ እንደታየው የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባሕል ለማክበር የተደረገውን ጥረት ክብር ሰጥተዋል።
መሪዎቹ ሰፊ መጠነ ርዕይ ባላቸው የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ በኢንቨስትመንት፣ ባሕል እና ትምህርት ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በተመለከተም ረጅም ዘመን ለቆየው መሻት ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት ሁለቱ ወገኖች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የነበራቸውን ውሎ የጋራ ፍላጎታቸውን የትብብር ቁልፍ ጉዳዮች በተመለከተ የጋራ መግለጫ በመስጠት አጠናቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ትግል መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኞች መታሰቢያ ሀውልት ስር የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።የዓድዋ ድል መታሰቢያንም ጎብኝተዋል።አዲስ አበባ ባሳየችው ፈጣን ለውጥ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም