በጀርመን ከደረሰው ጥቃት ጀርባ

በጀርመን ማግደቡርግ ከተማ ሕዝብ በተሰበሰበት የገና ገበያ ላይ በተፈጸመ የመኪና ጥቃት የ9 ዓመት ሕጻንን ጨምሮ አምስት ሰዎች ሲገደሉ ከ200 በላይ ሰዎች ቆስለዋል። አንድ ግለሰብ መኪናውን ሕዝብ በተሰበሰበበት ገበያ ላይ እንደነዳ እና በቁጥጥር ሥር እንደዋለ የጀርመን ፖሊስ አስታውቋል። ግለሰቡ ጥቃቱን ብቻውን ነው የፈጸመው ተብሏል።

የመጀመሪያው ድንገተኛ ጥሪ ሲደረግ ግለሰቡ መኪናውን የገና በዓል ገበያተኞች ላይ መንዳቱ ተገልጿል። ድንገተኛ አደጋ ነው ተብሎ የታሰበ ቢሆንም ጥቃት መሆኑ ኋላ ላይ ታውቋል። የእግረኞች መንገድ ላይ ነድቶ ሰዎቹን እንደገደላቸው ተገልጿል። መንገዱ ለአደጋ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ግለሰቡ መኪናውን በፍጥነት እየነዳ ገበያውን ደረማምሶ ሕዝብ ወደ ተሰበሰበበት ሥፍራ ሲያቀና ቪዲዮው በማኅበራዊ ሚዲያ ወጥቷል።

የዓይን እማኞች ከእግረኛ መንገድ ሮጠው በማምለጥ ራሳቸውን እንዳዳኑ ተናግረዋል። ግለሰቡ ወደ እግረኛ መንገዱ በገባበት መንገድ መልሶ መውጣቱን ፖሊስ አክሏል። ግለሰቡ ጥቁር ቢኤምደብሊው አጠገብ በቁጥጥር ሥር ሲውል ታይቷል። አጠቃላይ ክስተቱ 3 ደቂቃ የወሰደ እንደሆነ ተገልጿል።

በመኪና ጥቃቱ የ9 ዓመት ሕጻንን ጨምሮ አምስት ሰዎች ሲገደሉ ከ200 በላይ ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ቢያንስ 41 የሚሆኑት አስጊ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። የሞቱት ሰዎች ማንነት ገና ይፋ አልሆነም። ጥቃቱን የፈጸመው የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት ያለው የ50 ዓመት የሥነ ልቦና ባለሙያ ታሌብ አል-አብዱልሞህሰን መሆኑ ተገልጿል። የሚኖረው ጥቃቱ ከደረሰበት ከተማ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው በርግበርግ መሆኑ ታውቋል።

ግለሰቡ በግድያና የግድያ ሙከራ እንደሚከሰስ በዐቃቤ ሕግ ተገልጿል። ተጠርጣሪው ጥቃቱን ለምን እንደፈጸመ ግልጽ አይደለም። በ2006 ወደ ጀርመን እንደሄደና በ2016 ጥገኝነት እንዳገኘ ተገልጿል። የጀርመን የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ናንሲ ፌሰር ተጠርጣሪው “ሙስሊም ጠል እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል” ብለዋል።

ተጠርጣሪው በማኅበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች ድረ ገጾች ላይ እስልምናን እንደሚነቅፍ የሚጠቁሙ ጽሑፎች የተገኙ ሲሆን፤ የጀርመን መሪዎች አውሮፓን ሙስሊም ለማድረግ እየተመሳጠሩ ነው የሚል የሴራ ትንታኔም ያራምዳል። ከአንድ ዓመት በፊት ስለ ግለሰቡ ለፖሊስ ጥቆማ ቢሰጥም አስጊ መሆኑን የሚጠቁም ነገር አለማግኘታቸውን አመራሮች ተናግረዋል።

የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሹልዝ “ከማግደቡርግ የሰማነው ዜና ከፍተኛ ፍርሃት ፈጥሯል” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል። የማግደቡርግ ከተማ ካውንስለር ኖኒ ክሩግ፣ የገና ገበያው ዝግ እንደሚሆን ተናግረዋል። የገበያ አካባቢው መዘጋቱን አስታውቆ በጥቃቱ የደረሰውን ሐዘን ለመግለጽ ጥቁር ስክሪን ታይቷል። የሳዑዲ መንግሥት ለጀርመን ሕዝብ ሃዘኑን ገልጿል።

“የጀርመን ሕዝብ ከጎናችሁ ነን። በጥቃቱ ከሞቱና ከተጎዱ ቤተሰቦች ጎንም እንቆማለን። እንዲህ ያለ ጥቃትን እናወግዛለን” ብሏል የሳዑዲ መንግሥት። የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር “በጥቃቱ አዝነናል። ለሞቱት፣ ለቆሰሉትና ጥቃቱ ጠባሳ ለጣለባቸው ሃዘናችንን እንገልጻለን” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You