“አትግደል” የሚለው በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ያለው መንፈሳዊ ሕግ በጦርነት ሕግ እና በተለዩ-ጉዳዮች የወንጀል ቅጣት እንዲሆን ተፈቅዶ ካልሆነ በስተቀር በምድር ሕግጋትም የፀና ሕግ ነው። ሰው መግደል በየትኛውም ዘመናዊ የሕግ ሥርዓት ከፍተኛ ቅጣት የሚያስቀጣ በሰው የሕይወት መብት ላይ የሚፈፀም ደረቅ ወንጀል ነው።
የሕይወት መብት የመጀመሪያ ትውልድ ከሆኑት ሰብዓዊ መብቶች ውስጥ ቀድሞ የሚጠቀስ እጅግ መሠረታዊ መብት ነው። የሌሎች መብቶች ሁሉ ማደሪያውም ይኸው መብት ነው ለማለት ይቻላል። ለዚህም ይመስላል የ1960 የፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀፅ 1 ስር “ሰው ከተወለደበት ቀን አንስቶ እስከ ሞተበት ቀን ድረስ የሕግ መብት አለው” በማለት የሚጀምረው።
የሕይወት መብት ሰብዓዊ ብቻ ሳይሆን ሕገ-መንግሥታዊ መብትም ነው። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 15 ስር “ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው። ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም” በማለት የሕይወት መብትን ደንግጎ ይገኛል።
የሕይወት መብትን አስመልክቶ ሀገራት የሞት ቅጣትን በሕጋቸው ውስጥ ማስቀመጣቸው ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት በሕይወት የመኖር መብት ከሚገደቡት መብቶች ውስጥ ሊመደብ ይገባል ወይስ አይገባም? በሕይወት የመኖር መብት ከሌሎች በተለይም ከ4ኛ ትውልድ ሰብዓዊ መብቶች ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት ይታያል የሚሉ እና ሌሎች ጉዳዮች በሕግ ጁሪስፕሩደንስ (በሕግ ሳይንስ) ውስጥ አሁንም የመወያያ አጀንዳዎች ናቸው። የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ ግን በሰው ሕይወት ላይ የሚፈፀም ወንጀል በ1996 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንፃር እንዴት ይታያል የሚል ነው።
ነፍሰ ገዳይነት ምንድነው?
የ1996 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ የሚሰርቅ ሰው ሌባ ነው፤ ውንብድና የሚፈፅም ሰው ወንበዴ ነው፤ የአታላይነት ወንጀል የሚፈፅም ሰው አታላይ ነው…ወዘተ በማለት ስያሜ አይሰጥም። ነገር ግን በአንድ ጉዳይ ላይ ወንጀሉን ለሚፈፅመው ሰው ስያሜ ሲሰጥ እንመለከታለን። የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 538 (1)፡- “ማንም ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት በማናቸውም አይነት መሣሪያ ወይም ዘዴ ሌላውን ሰው የገደለ እንደሆነ ነፍሰ-ገዳይ ነው” በማለት በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ድርጊቱን ለሚፈፅሙ ሰዎች ስያሜ ሰጥቷል። ታዲያ የዚህ ምክንያቱ ምንድነው ያልን እንደሆነ አንድም በሀገራችን “ነፍሰ-ገዳይነት” የሚለው ስያሜ አሉታዊ ኃይል እንዲኖረው አድርጎ በመጠቀም ረገድ ያለውን ባሕል ለማበረታታት በሌላ በኩል ደግሞ ለሰው ልጅ ሕይወት ከፍ ያለ ዋጋ ሰጥቶ ማለፉን የሚያረጋግጥ ይመስላል።
በሀገራችን የወንጀል ሕግ የሰው ግድያ ወንጀል በአራት ተከፍሎ የተቀመጠ ሲሆን እነዚህም ከባድ የሰው ግድያ፣ ተራ የሆነ የሰው ግድያ፣ ቀላል የሆነ የሰው ግድያ እና በቸልተኝነት ሰውን መግደል ናቸው። ከእነዚህ ከአራቱ ወንጀሎች በአንዱ የተሳተፈ እና ሰውን የገደለ ሰው ከፍርድ ቤት ቅጣት በተጨማሪ ይህንን ነፍሰ-ገዳይነት የሚለውን ስያሜ የመሸከም ኃላፊነት አለበት። ሌላው ቀርቶ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ሰው መግደልም ነፍሰ ገዳይ የሚያስብል ነው፡፡
ከባድ የሰው ግድያ በሕጉ አንቀፅ 539 የተቀመጠ ሲሆን ግድያን ከባድ ግድያ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን በዋናነት ግን መመዘኛው ወንጀሉን ለመፈፀም ከነበረ የሀሳብ መጠን እና ወንጀል ለመፈፀም ካለ ከፍተኛ ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው። ወንጀሉን ለመፈጸም አጥብቆ መፈለግ፣ ቀድሞ ማሰብ ወይም አፈፃፀሙን ጨካኝ ማድረግ በዋናነት ግድያን ከባድ ግድያ ያደርገዋል።
ይህንን ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦች ወንጀል ለመፈፀም ከፍ ያለ ፍላጎት አላቸውና ከወንጀል ፍትሕ አንፃር የአደገኛ ሀሳብ ባለቤቶች ናቸው። በመሆኑም ሕጉ በዛው መጠን ወንጀሉን የፈፀመውን ግለሰብም ይሁን ሌሎችን ለማስተማር የሚችል፤ ወንጀል የመሥራት ሀሳብን ሊቀጣ የሚችል ከባድ ቅጣት ይጥልበታል።
ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል በእድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ወይም በሞት ያስቀጣል። የጥንታዊ የሀሙራቢ ሕግ ብልጭታን በከፊል በዚህ ጉዳይ ልንመለከተው እንችላለን። ዓይን ላጠፋ ዓይን እንደሚባለው የሰው ሕይወትን በከባድ ግድያ ላጠፋ ሰው ሁኔታዎች ተሟልተው በተገኙ ጊዜ የእሱ ሕይወትም እንዲጠፋ ፍርድ ሊሰጥበት ይችላል።
ተራ የሰው ግድያ የሚባለው በሕጉ አንቀፅ 540 ስር የተመለከተ ሲሆን በድንገተኛ ፀቦች ወይም ግጭቶች መካከል የሚፈፀሙ ከባድም ቀላልም ያልሆነ የሰው ግድያ ወንጀሎች የሚታዩበት ድንጋጌ ነው። ይህ ወንጀል በአብዛኛው ጊዜ የሚፈፀመው በማይተዋወቁ ሰዎች፤ ቀድሞ ፀብ በሌላቸው ሰዎች መካከል በተለያዩ አጋጣሚዎች ነው።
ዓቃቤ ሕግ በነበርኩበት ጊዜ ከማስታውሳቸው በዚህ አንቀፅ ስር ከተዳኙ ጉዳዮች መካከል አንዱ መጠጥ ቤት ውስጥ ገዳይ ሟችን “ከእኔ ጋር ቀድማ ከደነሰች ሴት ጋር ለምን አብረህ ደነስክ፣ ንቀኸኝ ነው” በሚል ፀብ የተነሳ ሟችን ጠርሙስ ሰብሮ በተለያዩ ቦታዎች ሟችን በመውጋት ሕይወቱ እንዲያልፍ ያደረገበት መዝገብ የማረሳው ነው። በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ በቆየሁበት ጊዜ የተመለከትኩት በዚህ የግድያ ወንጀል የሚሳተፉ ሰዎች አብዛኞቹ ከወንጀሉ ድርጊት በኋላ ወዲያውኑ በከፍተኛ ፀፀት ስር የሚወድቁ ናቸው።
ከባድ የግድያ ወንጀል የሚፈፅሙ ሰዎች የቀደመ ዝግጅት የሚያደርጉ፤ አስበው እቅድ የሚይዙ ውጤቱንም ከሞላ ጎደል የሚቀበሉ የወንጀል ሀሳብ የሚያመዝንባቸው ሰዎች ናቸው። ቀጥለን እንደምናየው በቀላል ግድያ ወንጀል የሚሳተፉ ሰዎች ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ገፊ ምክንያቶች አሏቸው። በተራ የሰው ግድያ ወንጀል የሚገቡ እና ይህንን ወንጀል የሚፈፅሙ ሰዎች ግን በቅፅበት እልህ፣ ትዕግስት ማጣት፣ አልደፈርም ባይነት….ወዘተ በመሳሰሉ የስሜት ሚዛን መጓደል ወንጀሉን የሚፈፅሙ በመሆኑ ወዲያውኑ በከፍተኛ ፀፀት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡
በዚህ ወንጀል ውስጥ ከመውደቅ የሚጠቅመን ትልቅ ባሕሪ ትዕግስት ነው። ጊዜያዊ ግጭት ከታገስነው እና ከተውነው ወይም በሠላም ከፈታነው ወዲያውኑ የሚያልፍ ሲሆን ለምን ተነካሁ በማለት ከገባንበት ደግሞ ራስንም ሌላን ሰውም የሚጎዳ ውጤት ይዞ የሚመጣ ይሆናል። በተለይም በምሽት መዝናኛ ቤቶች አካባቢ በፍፁም ፀብ ውስጥ እንዳይገቡ ፀሐፊው ይመክራል። በወንጀል ሕጋችን መሠረት ይህንን ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች እንደ ሁኔታው እና እንደ አፈፃፀሙ ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት ይቀጣሉ፡፡
ሦስተኛው የግድያ ዓይነት ቀላል የሆነ የሰው ግድያ ሲሆን በሕጉ አንቀፅ 541 ስር የሚዳኝ ነው። በዚህ ስር የሚወድቁ ግድያዎች መነሻቸው አስገዳጅ የሆኑ ምክንያቶች ወይም ድርጊቱን የሚፈፅመውን ሰው ሞሯል የሚፈትኑ ፅኑ ምክንያቶች ናቸው። ለምሳሌ ራስን ለመከላከል ወደ ፀብ የገባ ሰው የወሰደው እርምጃ ራስን ለመከላከል ከሚያስፈልገው የምጣኔ ምዘና በላይ ሆኖ ሰው ከሞተበት በዚህ ድንጋጌ ስር ይቀጣል።
ሊደበድብህ ዱላ ይዞ የመጣን ሰው የሰዎችን እርዳታ ወይም የሕግ ድጋፍ ልታገኝ በማትችልበት ሁኔታ እና ልትሸሽ በማትችልበት ሁኔታ አግኝቶህ ራስህን ለማዳን በዱላ ብትደበድበው ወይም ብትመክተው ራስን የመከላከል ድርጊት ስለሚሆን ምንም አማራጭ አጥተህ የፈጸምከው መሆኑ በፍርድ-ቤት ከተረጋገጠ ከወንጀል ቅጣት አያስጥልም። ነገር ግን ይህንን ዱላ ይዞ የመጣን ሰው መሣሪያ ተኩሰህ ብትገድለው ከተፈቀደልህ የመከላከል መጠን አልፈኃልና በቀላል የሆነ የሰው ግድያ ወንጀል ያስከስስሃል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በዚህ ድንጋጌ ስር ይታያሉ፡፡
ሌላው የዚህ ግድያ ዓይነት የሚሸፍናቸው ጉዳዮች ከሰው ልጅ ሚዛናዊ የሞራል ሁኔታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው። ለምሳሌ አንድ ባለትዳር የሆነ ሰው የሕግ ሚስቱ ከሌላ ወንድ ጋር “ተኝታ” ቢያገኛት እና የግድያ ወንጀል በአንዳቸው ላይ ቢፈፅም ከፍ ያለ ደም የሚያፈላ ምክንያት በመሆኑ የግድያው ዓይነት በዚህ ድንጋጌ ስር የሚታይ ይሆናል። ቀላል የሰው ግድያ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡
የመጨረሻው በቸልተኝነት ሰው መግደል ሲሆን ይህም በዋናነት ከጥንቃቄ ጋር የተያያዙ ችግሮችን የሚቀጣ ሕግ ነው። በተለይም የሌላ ሰውን ሕይወት፣ ጤንነት ወይም ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ወይም ሌላ ግዴታ ያለባቸው እንደ ሕክምና ባለሙያዎች ወይም አሽከርካሪዎች ከጥንቃቄ ጉድለት በሰው ሕይወት ላይ ወንጀል በፈጸሙ ጊዜ እንደ ነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ድረስ ሊቀጡ ይችላል።
ይህም ሁኔታ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 543 ስር ባሉት ንዑስ ድንጋጌዎች የሚታይ ነው። በቸልተኝነት ሰው መግደል ታዲያ ሁልጊዜ ባለሙያዎችን ብቻ የሚመለከት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በተለይም በገጠሩ አካባቢ ልጁን ለመቅጣት ሲል ያልተገባ ወይም ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሞ ልጁን የሚገድል ወላጅ ያጋጥማል። እነዚህ እና መሰል ጉዳዮችም በቸልተኛነት ሰው መግደል የሚያስቀጡ ናቸው።
በአጠቃላይ የወንጀል ሕጉ በእነዚህ አራት የግድያ ዓይነቶች በሰው ሕይወት ላይ ወንጀል የሚፈፅሙ ሰዎችን ይቀጣል። በሕጉም ነፍሰ-ገዳይ ተብለው ይታወቃሉ። ከዚህ የሕጉ ስያሜ እና ቅጣት መገንዘብ የሚገባን መሠረታዊ ጉዳይ ሁልጊዜም ቢሆን ከግድያ ወንጀል ፈፅሞ መራቅ እንደሚገባን እና በየትኛውም ሁኔታ ይህንን ወንጀል ከመፈፀም መቆጠብ እንደሚገባን ነው። የራሳችንን ሕይወት በምንወደው ልክ ለሌሎች ሰዎች ሕይወትም ተገቢውን ዋጋ መስጠት ሰብዓዊነት እና ዘመናዊነት መሆኑን ተገንዝቦ፤ ፈታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙ ጊዜያት እንኳን ሌሎች አማራጮችን ተጠቅሞ በማሳለፍ ይህንን ወንጀል መፀየፍ ይገባል።
ክብር ለሰው ልጅ ሕይወት !
አመሰግናለሁ፡፡
ይግረማቸው ከፈለኝ ወግደረስ (LLB, LLM)
ጠበቃ፣ የሕግ አማካሪ እና በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አሠልጣኝ
0910037554/yigremachewk@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም