ለመጪው የገና በዓል በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፡- መጪውን የገና በዓል አስመልክቶ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የቁጥጥር ግብረ ኃይሉ ርምጃ የሚወስድ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለጸ፡፡ ለመጪው የገና በዓል በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የግብይትና የገበያ ልማት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍሰሀ ጥበቡ፤ በበዓል ወቅት የሚፈጠረውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታት በምክትል ከንቲባ የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡ ግብረ ኃይሉ በቂ የሆነ ምርትን ለተጠቃሚው ከማቅረብ ባሻገር ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴንም የሚቆጣጠር ነው፡፡
መጪውን የገና በዓል አስመልክቶ በቂ ምርት በመኖሩ በምርቶች ላይ የሚደረጉ ያልተገቡ የዋጋ ጭማሪዎች አይኖሩም ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በቂ የእህል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት አለ፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ካሉ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ መጪው የገና በዓልን አስመልክቶ የሰብል ምርት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ለግብይት ሥርዓት ምቹ የሆኑ አማራጭ የግብይት ስፍራዎች እየተዘጋጁ ነው፡፡ ማህበረሰቡ የሚፈልጋቸውን የሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችና የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶችን በባዛር ፣ በቅዳሜና እሁድ ገበያ እንዲሁም በመደበኛ የግብይት ቦታዎች ላይ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
በከተማዋ በ11 ክፍለ ከተሞች ላይ በባዛር ገበያ፣ በገበያ ማዕከላት እና በግብርና የገበያ ማዕከላት ላይ በቂ የምርት አቅርቦት ለማድረስ ታቅዷል የሚሉት ኃላፊው፤ በምርቶች ላይ ያለውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት በየአካባቢው የተቋቋመው የእሁድ ገበያ የገና በዓል ከመድረሱ አስቀድሞ እስከ በዓሉ እለት በየቀኑ አገልግሎት እንደሚሰጡም ተገልጿል፡፡
እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ፤ የቁም እንስሳት አቅርቦት ላይ በቂ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፤ የቁም እንስሳት ግብይት በሚደረግባቸው ማዕከላት በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ሥራዎች ድርጅት ማዕከል የሆኑ ቦታዎች ፣ በመደበኛነት አገልግሎት በሚሰጡ የግብይት ስፍራዎች ፣ የኅብረት ሥራ ማህበራት ፣ የገበያ ማዕከላት እንዲሁም የከተማ ግብርና ቦታዎች የሚያከናውኑት ሽያጮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡
ግብረ ኃይሉ በበዓል ወቅት የሚኖረውን ከፍተኛ የግብይት ፍላጎት አስመልክቶ በገበያው ላይ ባልተገባ ሁኔታ የማህበረሰቡን ጤና የሚጎዱ ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸው ምርቶች ፣ የመጠመቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ይቆጣጠራል ሲሉ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በዚህ ተግባር ላይ ሲሰማሩ የተገኙ ነጋዴዎችም ሕጉን ተከትሎ አፋጣኝ ርምጃ ይወስዳልም ብለዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ የተውጣጣው ከአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ፣ የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ንግድ ሥራዎች ድርጅት፤ ከከተማ ግብርና እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያካተተ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ ሦስት ዘርፎች ያሉት መሆኑን የሚናገሩት የቢሮው ኃላፊ፤ የአቅርቦት ዘርፍ፣ የሕገ-ወጥነትና የኢንስፔክሽን፣ ድጋፍና ክትትል የተባሉ ዘርፎችን የያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ግብይት በሚያደርግበት ወቅት የሚመለከታቸውን ሕገ-ወጥ ተግባራት ቢሮው ባዘጋጀው ነጻ የጥቆማ የስልክ መስመር 8588 ላይ እና በየገበያ ማዕከላት በየወረዳው ጥቆማ ማድረግ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም