ደስታን የፈጠረ ትምህርት ቤት

የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የትምህርት ቤቶች ውስጣዊ አደረጃጀት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል። የተማሪዎችን ባሕርይ እና የመማር ማስተማር ሁኔታን በማሻሻል በኩል የማይተካ ሚና አላቸው። ተማሪዎችን በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከት ብቁ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ከዚህም አንጻር እንደ ሀገር በተለያየ መልኩ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ይገኛሉ። በገላን ጉራ መንደር ውስጥ ለልማት ተነሺዎች ተብሎ የተገነባው የገላን ጉራ ትምህርት ቤት ደግሞ ለዚህ እንደ ጥሩ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ትምህርት ቤቱ ከካዛንችስ፣ ከፒያሳ፤ ከመገናኛ ከሽሮሜዳ አካባቢ የመጡ ተማሪዎች የሚማሩበት ሲሆን፤ ለአካባቢው ነዋሪዎችም መልካም የመቀራረቢያ አጋጣሚን የፈጠረ ነው።

ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ጀምሮ መሟላት ያለባቸውን ሁሉ በማሟላትም የተሠራም ነው። ለአብነት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱን ብናነሳ ሕጻናቱ የሚተኙበት፤ የሚመገቡበትና የሚማሩበት እንዲሁም የሚፀዳዱበት ደረጃውን የጠበቁ ክፍሎች ተገንብተዋል። መፀዳጃ ክፍሎቹም በፆታቸው እንዲመች ተደርጎ የተገነቡ ናቸው። ከዚያም ባሻገር ሕጻናቱ ወጣ ሲሉ የሚዝናኑባቸው ቦታዎች ተመቻችተውላቸዋል።

ወደ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ስንገባም ይህንኑ ሁኔታ እንመለከታለን። ትምህርት ቤቱ ከአዲስነቱ የተነሳ ነገሮች ያልተስተካከሉለት ቢመስሉም አብዛኛው ሥራው የሚስብና ከትምህርት ቤቱ ውጡ የማያሰኝ ነው። እንደ ሀገር በትምህርት ቤት ውስጥ የተማሪዎች መማርና የመማር ውጤቶች በጎ ተፅዕኖ የሚያሳድሩት የትምህርት ቤት ዓበይት ርዕሰ ጉዳዮችንም አሟልቶ የተገኘ ነው። እነዚህም መማርና ማስተማር፤ የትምህርት ቤት አመራር፤ ምቹ የኅብረተሰብ ተሳትፎና የትምህርት ሁኔታና አካባቢ የሚሉት ሲሆኑ፤ ትምህርት ቤቱ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አሟልቶ አግኝተነዋል።

ግቢው በአረንጓዴ ችግኞች ያማረ ባይሆንም አቧራ እንዳያስቸግር በማሰብ በአርቴፊሻል ሣሮች ተውቧል። ተማሪዎች ዘና ብለው እንዲማሩም ልዩ ልዩ የመዝናኛ ቦታዎች ተገንብተዋል። አንዱ ሰፊው ስታዲየም ነው። ሌላው በትንሽ ስፍራ ላይ ያለችው የኳስ ሜዳና የቅርጫት ኳስ መጫዎቻ ሜዳው ነው። ይህ ደግሞ ተማሪዎች በዙሪያው ተቀምጠው እንዲያጠኑ፤ አለያም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ፤ ካሻቸው ደግሞ በቡድን ሆነው እንዲመካከሩ ዕድል ይሰጣቸዋል። ክፍላቸውም ያማረ በመሆኑ በዚያ የፈለጋቸውን እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው ነው። ለዚህም ምስክርነታቸውን የሚሰጡን አሉ።

አንዱ ተማሪ ኢምራን መሐመድ ነው። ስለ ትምህርት ቤቱ ሲናገር፤ ይህ ልዩ ምድር ለእኛ ገጸ በረከት ነው። ከዚህ በፊት በነበርንባቸው ትምህርት ቤቶች ያላየነውን ነው የሰጠን። የትምህርት ቤቱ ፅዳትና አሠራርም ለእኛ ከነበርንበት ስፍራ በእጅጉ የተሻለ ነው። በተለይም የትምህርት ክፍሎቹና የስፖርት ሜዳው ወይም ስታዲየሙ እጅጉን ደስታን የፈጠረልን ነው። ምክንያቱም ትምህርት ቤት መማሪያ ብቻ ሳይሆን ማጥኛም፤ መዝናኛም፤ ራስንም ማዳመጫ ነው። እናም ገላን ጉራ ትምህርት ቤት ይህንን ሰጥቶናል።

ተማሪ ኢምራን አሁን ያለበት ትምህርት ቤት በእጅጉ ተመችቶታል። ትምህርት ቤቱ መኖሪያ ቤቱ እስኪመስለው ጭምር እየቆየበት ነው፤ ያጠናበታልም። በተለይም ከስታዲየሙ ግንባታ ጋር ተያይዞ ብዙ ደስ የሚሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ዘና ከማለት አልፎም ከጓደኞቹ ጋር ንጹሕ አየር እየሳቡ በቡድን የሚያጠኑበትን ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በዚህም ትምህርት ቤቱን የሚስብና አትራቁ የሚያሰኝ ሆኖ አግኝተነዋል ይላል።

ተማሪ ኢምራን የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ ከካዛንችስ ምሥራቅ ጎሕ ትምህርት ቤት ከመጡት ተማሪዎች መካከል ነው። ነባር ትምህርት ቤቱ አሁን ከአለበት ጋር ሲያነጻጽረው በብዙ መልኩ የተለየ እንደሆነ ይናገራል። የቀድሞ ትምህርት ቤቱ የመዝናኛ ቦታውና ስፋቱ ምንም ዘና የሚያደርግ አይደለም። ስታዲየም ይቅርና ጥሩ የመጫወቻ ሜዳ እንኳን የለውም። ስፖርት ሲሠሩም ሁልጊዜ ልብሳቸው፤ ሰውነታቸው በአቧራ ይሸፈናል። አሁን ግን ይህ አያጋጥማቸውም። ስታዲየሙ በአርቴፊሻል ሳር የተሸፈነ በመሆኑ ምንም አይነት አቧራ አያገኛቸውም። ጎን ለጎን የቅርጫት ኳስ መጫወቻ የተመቻቸላቸው በመሆኑ ተማሪው በፈለገው ዘርፍ ዘና እያለ ትምህርቱን ይከታተላል።

ተማሪ ኢምራን በምሥራቅ ጎሕ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብዙ ነገር ይጎል ነበር። ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያቆየው የመምህራን የማስተማርና እነርሱን የመደገፍ ሁኔታ ብቻ ነው። አሁን ግን ብዙ ነገሮች እርሱን ማርከውታል። አንዱ የትምህርት ቤቱ ምቹነት ሲሆን፤ ሌላው መምህራን በትምህርታቸው ወደ ኋላ እንዳይቀሩ የሚያደርጉት ጥረት ነው። ይሁን እንጂ በአፋጣኝ እንዲሟሉላቸው የሚፈልጋቸው ነገሮች እንዳሉ ሳይጠቁም አላለፈም። እነዚህም ትምህርት ቤቱ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች ናቸው። ቤተ መጽሐፍቱ በሚገባ አልተደራጀም፤ ቤተ ሙከራም የለም። እናም በተለያየ መንገድ መምህራን እያገዙን ቢሆንም ትምህርት ቤቱ በአፋጣኝ መፍትሔ የሚሰጥበትን መንገድ ቢያመቻች ሲል አስተያየቱን ለግሷል።

ተማሪ ሀያት ዋሲሁን ሌላኛዋ ምስክርነቷን የሰጠችን ነች። እንደ ኢማን ሁሉ በትምህርት ቤቱ ምቹነት መደሰቷን ትገልጻለች። ይህ ትምህርት ቤት በተለይም ለሴቶች ጥሩ ዕድልን ይዞ የመጣ እንደሆነ ታስረዳለች። ምክንያቱም ከቤታቸው ርቀው እንዳይሄዱ ያግዛቸዋል። በትምህርት ቤቱ ውስጥ እያጠኑና የቤት ሥራዎችን እየሠሩ ቢቆዩም ለቤታቸው በቅርብ ርቀት ላይ የተሠራ በመሆኑ የሚያስጨንቃቸው ነገር የለም። እስካሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር በአሁኑ በእጅጉ መደሰቷን ትናገራለች።

ቀደም ሲል በምትማርበት ትምህርት ቤት መምህሮቿ የተሻሉ እንደሆኑ አንስታ፤ ለማጥናት ያለው ምቹነት ግን እምብዛም እንደሆነ ትጠቅሳለች። ይህ ትምህርት ቤት ግን ፀጥታና ምቹነት የተሻለ ተማሪ እንድትሆን እንደሚያግዛትም ታምናለች። ለዚህም መምህሮቻቸው እያገዟቸው እንደሚገኙም ታስረዳለች። የእነርሱን ልዩ ድጋፍም ሳታደንቅ አላለፈችም። ትምህርት ሲጀምሩ ጀምሮ አቅማቸውን እየለዩ ለእነርሱ የሚመጥን ትምህርት እየሰጧቸው እንደሆነም ታነሳለች። በአቅራቢያቸው ካሉ ትምህርት ቤቶች ጋር ጭምር በመነጋገር የተለያዩ መጽሐፍትን የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዳመቻቹላቸው ጠቅሳ ለዚህም ምስጋና አቅርባለች።

ሀያት እንደ ኢማን ሁሉ ቢሟሉልን የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን የምትላቸው መሠረተ ልማቶችና ግብዓቶች አሉ። አንዱ የአይሲቲ ክፍል ነው። ሌላው ደግሞ ቤተ መጽሐፍት ሲሆን፤ በመምህሮቻችን በቅርቡ ይህ ነገር እንደሚሟላልን ተነግሮናል። ነገር ግን ውጤቱ ቶሎ መታየት አለበትና ሁሉም ተረባርቦ ለመፍትሔው መሥራት ይገባልም ስትል ሀሳቧን ገልጻለች።

አቶ አስቻለው ኃይሉ የገላን ጉራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው። ከደራርቱ ቱሉ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት ቤቱን ለመምራት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት ተዛውረው መምጣታቸውን ይናገራሉ። አሁን ትምህርት ቤቱን የመምራት ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ያስባሉ። ከዚህ አንጻርም ትምህርቱን ሲያስጀምሩ በተለየ ወኔ እንደሆነ ያነሳሉ።

የተረከቡት ትምህርት ቤት ብዙዎች የተደመሙበት ነው። ለዘጠና ቀን ታቅዶ በስልሳ ቀን የተጠናቀቀ እንደሆነም አውቀዋል። እናም ይህንን እውነት በተማሪዎችም ውጤት መድገም ይፈልጋሉ። በመሆኑም በመንግሥት በጀት ብቻ ይህንን ማድረግ አይችሉምና የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። አንዱ ተማሪዎች ማንበቢያ ክፍል ብቻ ሳይሆን የሚያነቡት መጽሐፍም ያስፈልጋቸዋል በማለት ‹‹ሁለት ያለው አንድ ይስጥ›› የሚል እንቅስቃሴ ጀምረው መጽሐፍትን እየሰበሰቡ ናቸው። በተገኙት መጽሐፍትም ቤተ መጽሐፍቱ አገልግሎት እንዲሰጥ ሥራ ጀምረዋል። ሌላው ‹‹ሁለት ያለው አንድ ይስጥ›› እንቅስቃሴያቸውን በኮምፒውተሮች ዙሪያም አድርገዋል። በዚህም ወደ አስር ኮምፒውተሮችን አግኝተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

‹‹ተማሪዎች ብቻቸውን የሚንቀሳቀሱ አይደሉም። በሁሉም ዘርፍ ውድድር ይጠብቃቸዋል። ያለው ችግር ከሌሎቹ ጋር እንዳይወዳደሩ ሊያደርጋቸው አይገባም›› የሚሉት ርዕሰ መምህሩ፤ ሁሉም ጋር ተወዳድረው አሸናፊ፤ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ እንዲሆኑ ለማስቻል ልዩ ልዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነም ያነሳሉ። በአብነት የሚጠቅሱትም በትምህርታቸው ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ቅዳሜና እሁድ ሳይባል አስጠኚ መምህራንን በመመልመል በልዩ ትኩረት እንዲማሩ ማስቻሉን ነው። በተመሳሳይ በአካባቢያቸው ያሉትን ፀጋዎች በመጠቀም የተማሪዎችን ውጤታማነት ማሻሻል ነው። ለምሳሌ ዩኒቨርሲቲ ጭምር በአካባቢው ላይ ስላለ የተደራጁ ቤተ መጽሐፍትንና ቤተ ሙከራዎችን እንዲጠቀሙ ለማስቻል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የግቢ ማማር የመጨረሻ ግብ እንዳልሆነ የሚጠቁሙት አቶ አስቻለው፤ ከግቢ ውበት ባሻገር ተማሪዎች ላይ መሠራት ያለበት መሠረታዊ ነገር አለ። ይህም የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻልና ውጤታማ ተማሪ መፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ በሥነምግባር የታነጸ ዜጋ ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ትምህርት ቤቱ ምቹነት አለው። አዲስ መምህር፤ ርዕሰ መምህርና አዲስ ተማሪን ይዞ የተነሳ ነው። በመሆኑም ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ ከእውቀት ባሻገር የሚታዩ መሆን መቻል አለባቸው። በትምህርት ቤቱ መልካም ባሕልን የሚያጎለብቱ፤ ሕግን የሚያከብሩ፤ ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑና አዲስ መሰባሰብ የተቃኙ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም አዲስ ባሕልን፤ ልምድንና እውቀትን አስተባብሮ የሚይዝበት ሊሆን ይገባል። እናም ይህንን መሠረት ለመጣል ሁሉም እየተጋ ይገኛልም ብለውናል።

የገላን ጉራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት እርካታን የሚሰጥ መሆን አለበት። ተግባሩ ደግሞ ከተማሪዎች ይነሳል። ከዚያ ወላጆች ጋር ይደርሳል የሚሉት ርዕሰ መምህሩ፤ አሁን በአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ 157 የሚደርስ ተማሪ እንዳለ ይናገራሉ። ገና በመምጣት ላይ ያሉ ተማሪዎች በመኖራቸውም ቁጥራቸው ከዚህም እንደሚልቅ ያስረዳሉ።

ይህ ትምህርት ቤት ለልማት ተነሺዎች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ማኅበረሰብም የተበረከተ ልዩ ስጦታ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አስቻለው፤ ትምህርት ቤቱ በቅርብ ርቀት ላይ ለሚገኙ ተማሪዎችና ወላጆች እፎይታን የፈጠረ እንደሆነ ያስረዳሉ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአካባቢው ላይ በስፋት ቢኖርም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግን እንደ ልብ አይገኝም። በዚህም ተማሪዎች ርቀው እንዲሄዱ ይገደዳሉ። ቤተሰብም ልጆቹ በሠላም ለመግባቱ ይጨነቃሉ። አሁን ግን ይህ ሁኔታ መፍትሔ በማግኘቱ ብዙዎች ደስተኞች ስለመሆናቸውም ይናገራሉ።

መምህር ኃይሌ ተዝገራ ከአቃቂ ቃሊቲ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡና አሁን በገላን ጉራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሒሳብ መምህር በመሆን የሚያገለግሉ ናቸው። ተማሪዎቻችን የእኛ ኃላፊነት ናቸውና የትምህርት ቤቱ መሠረተ ልማትና ግብዓት እስኪሟላ ድረስ እነርሱን ለመደገፍ የማናደርገው ነገር አይኖርም ይላሉ። አሁን ላይ አማራጭ የሚሏቸውን ተግባራት እያከናወኑ እንደሆነም ይገልጻሉ። አንዱ ከዚህ ቀደም ያስተምሩባቸው የነበሩ ሞዴሎችን ይዘው በመምጣት ትምህርቱን በሚገባቸው መልኩ መስጠት እንደሆነም ይናገራሉ።

ተማሪዎቹ አዲስ ከመሆናቸው የተነሳም አቅማቸውን የመለየት ሥራ ሁሉም መምህር በየትምህርት አይነቱ እያከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት መምህሩ፤ አንዳንድ የትምህርት አይነቶች የግድ ቤተ ሙከራ የሚፈልጉ በመሆናቸው የሚደርሱበት ምዕራፍ ላይ ቆም ብለው በቻሉት ልክ በታብሌት እንዲሁም በሞባይላቸው የተግባር ትምህርቱን እንዲሠሩ እየተደረገ እንደሆነ ያነሳሉ። አክለውም ጊዜው የቴክኖሎጂ በመሆኑ አብዛኛውን ትምህርት ተማሪዎች ጭነው እንዲመጡ በማድረግ የመማር ማስተማር ሥርዓቱን ለማሳለጥ እየተሞከረም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ከቂሊንጦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጋር በመወያየት ተማሪዎቻቸው በቁጥራቸው ብዙ ስላልሆኑ ቤተ መጽሐፍትና ቤተ ሙከራዎችን እንዲጠቀሙ መደላደልን መፍጠራቸውንም ያስረዳሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለም የግብዓትና ልማቱ ጉዳይ በአጭር ጊዜ እንደሚፈታ ያምናሉ። ለዚህም ሁሉም የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ርብርብ እያደረገ እንደሆነም ይጠቅሳሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You