የሀገር በቀል ኢኮኖሚው ማሻሻያ ምሰሶ ናቸው ተብለው ከተለዩት አንዱ ቱሪዝም ነው። የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስፋት፣ ቅርሶችን የመጠገንና የማደስ ፣ ከተሞችን የማዘመን፣ ታሪካዊ ቦታዎችን እና ታሪክ ገላጭ ቁሳቁስን ለቱሪስቶች ክፍት በማድረግ ወረትን ወደ ሀብት የመቀየር ሥራ እየተሠራ ነው።
ታላቁ ቤተ-መንግሥት፣ የጂማ አባጅፋር ቤተ-መንግሥት ታድሰውና ተውበው ለጎብኚዎች ክፍት መደረጋቸው የሚታወስ ነው። ከሰሞኑም የኢዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት ሙዚየም ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት ሊደረግ መሆኑ እየተነገረ ነው። የጎንደር የፋሲል ግንብ፣ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዕድሳት እየተካሄደ ሲሆን፤ የአክሱም ሐውልትና ሌሎችም እድሳት ሊደረግላቸው እንደሆነ ታውቋል። የቱሪስት ጸጋን ወደ ሀብት ለመቀየር እየተደረገ ያለውን ንቅናቄ የዘርፉ ሙያተኞች እንዴት ይገልጹታል?
በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የቅርስ ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ይልማ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ ማንኛውም ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገቱን የሚያስቀጥለው ባለው ሀብት ላይ ተመስርቶ ነው፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቅርስ ሀብት ያላት ሀገር ነች፤ ይህን ከፍተኛ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ቢቻል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይቻላል።
ለዘመናት ጥቅም መስጠት ሲገባቸው ከጎብኚዎች እይታ ተሰውረው የቆዩ ቅርሶች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አሉ። ቱሪዝም በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና እንዲወጣ ሲታሰብ እነዚህን ሀብቶች ጥቅም ላይ ማዋል የግድ ይላል። ከቅርሶቹ ሀገር ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ መደረጉም ተገቢነት ያለው ነው። ቅርሶች ባህላዊ፣ ኪነ-ጥበባዊ፣ ታሪካዊና ትምህርታዊ ፋይዳቸውም ከፍተኛ ነው ይላሉ።
ቅርሶችን አሰባስቦ የሚይዝ ሙዚየም ተገነባ ማለት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ደህንነታቸው ተጠበቀ ማለት ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ የመተላለፍ ዋስትናም ያገኛሉ። በተለያዩ ቤተ መንግሥቶች የሚገኙ ቅርሶችን ለጎብኚዎች ክፍት ማድረጉ የውጭ ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር የሚያደርግ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅርሳ ቅርስና ቤተመጻሕፍት ወመዘክር ቱሪዝም መምሪያ ዋና ኃላፊ መላከ ሰላም ቀሲስ ዳዊት ያሬድ በበኩላቸው፤ ቅርሶች ትናንት የነበሩ ትውልዶች ምን ነበሩ? የሀገሪቱና የሕዝቦቿ የእድገትና የስልጣኔ ደረጃ ምን ላይ ደርሶ ነበር? ታሪኳ ምንድን ነው? የሚለውን ቁልጭ አድርገው የሚያስረዱ ናቸው ይላሉ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንደ ሀገር በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችን በባለቤትነት ታስተዳድራለች። ይሁንና የምታስተዳድራቸው ቅርሶች ከአንድ ተቋም አልፈው ፣ የሀገር ፣ ከሀገርም አልፈው የዓለም ሀብት ናቸው። ቅርሶች የእገሌ ወይም የእገሌ የሚባሉ አይደሉም፤ የሚወክሉት ፣የሚገልጡትና የሚያሳዩት ሀገርን እና ሕዝብን ነው፤ ቅርሶችን የማሰባሰብና የማደስ ሥራ ከሚሠራ ጋር ሁሉ በገንዘብ፣ በሙያ ፣ በሃሳብና በጉልበትም ጭምር መተባበር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ አድርጎ እየሠራ ከመሆኑ አንጻር ቅርሶችን በማደስ እና በመንከባከብ ገቢን ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት የሚደገፍ ነው ይላሉ።
ቅርሶች የሀገር ውስጥንም ይሁን የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን በመሳብ በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ለምሳሌ እዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት ከአሁን ቀደም ለቱሪስት ክፍት ባለመደረጉ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲሰጥ አልነበረም። አሁን ለቱሪዝም ዘርፉ ከተሰጠው ትኩረት አንጻር በውስጡ ያለውን ሀብት በአንድ አሰባስቦ ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ መዘጋጀቱ የገቢ አቅም ከመፍጠርም በላይ በቅርሶች ጥገና ፣ በሙዚየም ማደራጀት እና በአስጎብኚዎች ዘርፍ ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል የሚፈጥር ነው የሚሉት ደግሞ አቶ ሀብታሙ አብርሃ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃና ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።
የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተጠቃሚ የሚያደርገው የተወሰኑ አካላትን ብቻ ሳይሆን ከትልልቅ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች ድረስ ያሉትን በሙሉ ነው፤ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት እንደሀገር ኢኮኖሚውን ያነቃቃል። አንድ ቅርስ በዓለም ቅርስነት የሚመዘገበው ለዕይታ ሲቀርብ ነው። በዘርፉ ስምና ዝናን ካተረፉ ሀገራት ጋር በመተባበር ቅርሶችን በማደስና በመጠበቅ በዓለም ዘንድ ጎልተው እንዲታዩ ማድረግ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ያመለክታሉ።
ከዚህ አንጻር ፈረንሳይ ከፋይናንስና ከሙያዊ ድጋፍ፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግርና ከልምድ ልውውጥ አንጻር ለኢትዮጵያ በቅርሶች ዕድሳት እያደረገች ያለው ድጋፍና አስተዋጽኦ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው ይላሉ ዶ/ር ዮናስ።
አቶ ሀብታሙ ይህንኑ ሃሳብ ሲያጠናክሩ፤ ቅርሶች የአንድ ሀገር ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ሀብት ናቸው፤ ለአንድ ሀገር ሕዝብና መንግሥት የሚተው ጉዳይ ስላልሆነም ነው ዩኔስኮ እውቅና እየሰጠ ጥበቃ የሚያደርግላቸው ይላሉ፤
የፈረንሳይ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቅርሶችን በማደስ እና በመንከባከብ ተባባሪ መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሠሩት የዲፕሎማሲ ውጤት እንደሆነ ቢታወቅም፤ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ብቻዋን ማከናወን የማትችለውን የጥገና ሥራ የፈረንሳይ መንግሥት ማገዝ የቻለው፤ ቅርሶች ዓለም አቀፍ ሀብት በመሆናቸውም ጭምር እንደሆነ ያስረዳሉ። እገዛው ከፋይናንስ አቅም ጋር ብቻ ሳይሆን ከሙያ አንጻርም በመሆኑ ቅርሶችን በጥንቃቄ ለማደስ ትልቅ እድል እንደሆነ ያብራራሉ።
አሠራርን የሚያቀሉ ቴክኖሎጂዎች ባሉበት በዚህ ዘመን ያልተሠሩ ሥራዎች በጥንቱ ዘመን ተሠርተዋል የሚሉት መላከ ሰላም ቀሲስ ዳዊት በበኩላቸው፤ በላሊበላ ፍልፍል አቢያተ ክርስቲያናት ከአንድ ወጥ ድንጋይ ሥነ- ሕንፃና ሥነ-ውበት ተጣምረው የታዩበት፤ ዛሬም ድረስ የሚያስደምም ድንቅ ሥራ እንደተሠራ ያስረዳሉ።
ይህ ደግሞ አባቶቻችን ከብዙ ዓመት በፊት ዛሬን አሻግረው የተመለከቱ መሆኑን የሚያሳይ ነው ይላሉ።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፈረንሳይ መንግሥትን በማነጋገር ቅርሶች እንዲታደሱ የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀው፤ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጥገና እንዲደረግ ማድረጋቸውም ተገቢነት ያለው ስለመሆኑ ያስረዳሉ።
አቶ ሀብታሙ፤ ቅርሶች ያለፈውን የአሁኑንና የመጪውን ትውልድ ማስተሳሰር የሚችል ጥልቅ እና እምቅ የሆነ ጥበባዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው ይላሉ። እንደ ላልይበላ ያለውን ድንቅ የእደጥበብ ውጤት ሀገሬው ብቻ ሳይሆን ዓለምም በስስት የሚመለከተው ነው። ቅርሶችን መጠበቅ በአግባቡ ማደራጀትና ለቱሪስቶች ክፍት ማድረጉ ኢኮኖሚያዊ ትርፍን የሚያስገኝ ከመሆኑም ባሻገር የአንድን ሀገር የስልጣኔ ደረጃ፣ የአኗኗር ባህል እና ታሪክ የሚያስረዳም እንደሆነ አብራርተዋል።
በኢዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት የሚገኙ ቅርሶች ታድሰውና ለጎብኚዎች በሚስቡ መልኩ ክፍት የሚደረጉ መሆኑንም የሀገሪቱን ታሪክ ለመረዳት የሚያስችል እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያለው እንደሆነ ይገልጻሉ።
ሁሉም ሰራሽ ቅርሶች ታሪካዊ ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ አድሶና ተንከባክቦ ወደ ሀብት ለመቀየር የሚደረገው ጥረት ነገ ኢኮኖሚያዊ ፍሬውን እንድናጣጥም ያደርገናል ነው ያሉት ምሁራኑ።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም