ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በሀገር ውስጥ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱት እና በውጭ ሀገራት ሆነው የተለያዩ የትግል አማራጮችን መርጠው ከነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ከትናንት በስቲያ ውይይት አድርገዋል፡፡
በወቅቱም በሀገሪቱ ያሉት ከ70 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራራቢ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው በአንድ ላይ በመሰባሰብ ወደ ሦስት ወይም አራት ዝቅ ቢሉ የበለጠ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማጠናከር ጠቃሚ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ህዝብንና ሀገርን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አመልክተዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ምክረ ሀሳብ እንደሚደግፉት በመግለጽ ከዚህ ቀደም ባለመሰባሰባቸው ያጡትን ዕድሎች፤ ቢሰባሰቡ ሊያገኙ ስለሚችሉት ጥቅም፤ ለመሰባሰብ ስላለው አስቻይ ሁኔታና ተግዳሮት አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰሩና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበሩ ዶክተር መረራ ጉዲና እንዳሉት፤ ፓርቲዎች በተወሰኑ አስተሳሰቦች ዙሪያ መሰባሰብ እና መጠናከር አለመቻላቸው ሀገሪቷን እና ድርጅቶቹን ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ ተጠያቂነት ያለው መንግሥት እና የፖለቲካ ሥርዓት እንዳይፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ተጠያቂነት አለመስፈኑ በሀገሪቷ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳይስፋፋ በር ከፍቷል፡፡ በጠንካራ በፓርቲዎች እጦት ምክንያት በሀገሪቱ የተፈጠረው የካድሬ አስተዳደር ለመልካም አስተዳደር ችግር እና ለዘረፋ በር ከመክፈቱም ባሻገር የአፈና ሥርዓት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
ለፓርቲዎች በተወሰኑ ርዕዮተ ዓለሞች ዙሪያ አለመሰባሰብ የገዢው ፓርቲ ስውር እጆች ትልቁ ችግር ሆኖ ቆይቷል የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ ገዥውን ፓርቲ የሚወክሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ፓርቲዎችን ለመፈረካከስ የሚዳርጋቸው ችግር እንደማይኖር እየተናገሩ መሆኑ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡
በገዢው ፓርቲ ሊቀመንበር ዘንድ ፓርቲዎች ወደ አንድ እንዲመጡ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የፖለቲካ ምህዳሩ እየተስተካከለ በመሆኑ ጉልበት፣ አቅምና ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እየነጠሩ የሚወጡበት እና የህዝብ ድጋፍ የሌላቸው ደግሞ እየተራገፉ የሚሄዱበት ሁኔታዎች እየተፈጠሩ እንደሚሄዱ አንስተዋል፡፡ ይህም ለፓርቲዎች ቁጥር መቀነስ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር መረራ ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች ቁጥራቸውን እንዲቀንሱ ህዝቡ ግፊት ማሳደር ጀምሯል፡፡ ይህ የህዝብ ግፊት ፓርቲዎች በግድም ሆነ በውዴታ ወደ አንድ እንዲመጡ ያስገድዳቸዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑ ክስተቶች በአንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ነው፡፡ ለአብነትም ኦሮሚያ አካባቢ ባደረጉዋቸው ስብሰባዎች ህዝቡ ‹‹በደማችን ባመጣነው ለውጥ መቀለድ ትታችሁ ወደ አንድ ተሰባሰቡ›› የሚል መልዕክት እያስተላለፈ ነው፡፡ ይህ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የኖሩበትን የህዝብ ድምጽ የመከፋፈል ልምዳቸውን እንዲተው ማንቂያ ደውል ነው፡፡
የአረና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የመድረክ አመራር አባል አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ዋና የሚባሉ ሦስት ወይም አራት ሀገራዊ የሆኑ ፓርቲዎች ያስፈልጓታል ባይ ናቸው፡፡ የፓርቲዎች ቁጥር መቀነስ አለበት የሚለውን ግን ፓርቲዎች ለመድረክ ፍጆታ መጠቀም የለባቸውም ይላሉ፡፡ በርካታ ፓርቲዎች መኖራቸው ለፓርቲዎችም ሆነ ለሀገሪቱ ከጉዳት ውጪ ጥቅም አያስገኝም፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲዎቹ የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ውጤቶች መሆናቸው መዘንጋት የለበትም ባይ ናቸው፡፡
ፓርቲዎቹ የሀገሪቱ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ደረጃ ውጤት ናቸው፡፡ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ፓርቲዎች ከኖሩበት አባዜ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወጥተው ሦስት ወይም አራት ፓርቲ ይሆናሉ የሚል እምነት የላቸውም፡፡ አሁን ዋናው የፖለቲካ ማጠንጠኛ የሆነው የብሔር ጉዳይ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ብሔር ተኮር ፓርቲዎች ብዙም በማይታወቁባቸው አካባቢዎች ጭምር ብሄር ተኮር ፓርቲዎች በመመስረት ላይ መሆናቸውን እንደማሳያ ያነሳሉ፡፡
እንደ አቶ ገብሩ አስራት ማብራሪያ፤ የፓርቲዎች ቁጥር እንዲቀንስ የፖለቲካ ልሂቃኑ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፡፡ ልሂቃኑ አስፍተው ባለማሰባቸው ምክንያት የፓርቲዎችን ቁጥር ለመቀነስ ሲደረግ የነበረው ጥረት ከዚህ ቀደም ተጨናግፏል፡፡ ለአብነት ያህል የራሳቸው ፓርቲ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በመሆን አንድ ሀገራዊ ድርጅት ለመመስረት ሞክሮ እውን ሊሆን አልቻለም፡፡ ይህም አሁን ለአንድነት ዝግጁ እንዳይሆኑ አድርጓል፡፡ በአጭር ጊዜም እውን ሊሆን አይችልም፡፡
የፓርቲዎች መፈረካከስ እንዲቆም የሰከነ ፖለቲካ ባህል ማዳበር እጅግ አስፈላጊ ነው የሚሉት አቶ ገብሩ፤ የተለየ ሀሳብ ያለውን ቡድን የማጥቃት እና የማግለል ልምድ መቆም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ ሁሉም የአንድ ሀገር ህዝብ እንደሆነ ማመን እና የሠ ለጠነ የፖለቲካ አግባብ መከተል እንዳለበት መገንዘብ አለበት ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያዊያን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢ.ሀ.ን) ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት እንደሚገልጹት፤ ከገዢው ፓርቲ ቀጥሎ ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎችን በመከፋፈል ለደካሞች የምስክር ወረቀት በመስጠት እና አቅም ያላቸው እንዲዳከሙ በማድረግ ይታማ ነበር፡፡ ይህ ፓርቲዎችን ለማዳከም እና ለማፈራረስ ይሰራ የነበረው ሥራ ከቀረ በፖለቲካ ውስጥ ዋናው ጉዳይ ተቀባይነት እና ችሎታ ብቻ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አንድ የፖለቲካ ስብስብ የምስክር ወረቀት ስላለው ብቻ ፖለቲከኛ ሆኖ የሚኖርበት ጊዜ እያበቃ ነው፡፡
ላለፉት 27 ዓመታት የተሰራጩት ከፋፋይ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች በመንግሥት ደረጃ እየተቀየሩ መምጣታቸውና የሚያሰባስብ፣ የሚያቀራርብ ብሎም መጥፎ አመለካከቶች እንዳይስፋፉ የሚያደርጉ ነገሮች እየታዩ መሆናቸው ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡ መልካም እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ ሆኖም አብሮ ያለመስራት ችግር በሀገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ላይ የሚታይ በመሆኑ ሰፊ ውይይት እንደሚጠይቅ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢንጅነር ይልቃል ማብራሪያ፤ ፓርቲዎች ከአሁን በኋላ እንደከዚህ ቀደሙ ተከፋፍለው መኖር እንደማይችሉ አምነው አሰላለፋቸውን መለየት አለባቸው፡፡ ካልተሰባሰቡ እድላቸው መጥፋት መሆኑን ማወቅ አለባቸው፡፡ በመሆኑም ፓርቲዎቹ ይህን አውቀው በምስክር ወረቀት እና በህጋዊነት ሽፋን መኖር የሚቻልበት ዘመን ስላበቃ ሊያስቡበት ይገባል፡፡
ካልሆነም የተለየ ስትራቴጂ ይዘው ለመውጣት ብቻ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ በሌላ ጎን ፓርቲዎቹ ቢሰባሰቡ ማህበራዊ መሰረታቸው ሰፊ ስለሚሆን መንግሥት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ጉልበት ያገኛሉ፤ የህዝብን ጥያቄዎች እና አማራጭ ሀሳቦችን ለማቅረብ እንዲሁም ህብረተሰቡን ለማነቃነቅ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2011
በመላኩ ኤሮሴ