
አዲስ አበባ፡- አፍሪካ በሥራ ፈጠራ ዘርፍ ያላትን አቅም ወደ ተግባር በመለወጥ አካታች ኢኮኖሚን መገንባት እንደሚገባት ተጠቆመ፡፡ ከግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የሰነበተው 20ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ጉባኤ ትናንት ተጠናቋል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት፤ አፍሪካውያን ትብብርና ፈጠራ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን የማሳካት ኃይል እንዳላቸው ተገንዝበው፤ እነዚህን አቅሞች ወደ ተግባር መለወጥ ይገባቸዋል፡፡ ሥራ ፈጠራን ለችግሮች የማይበገሩ ማኅበረሰቦችን ከመገንባት እና የአካባቢ ደህንነትን ከመጠበቅ ጋር በማስተሳሰር መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሥራ ፈጠራና ከተማ ልማት ዘርፎች ያላትን አቅም በተግባር ለመተርጎም ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ሥራ ፈጠራን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ያስተሳሰሩ በርካታ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንና ይህም የተሸረሸሩና የተራቆቱ መሬቶችን ምህዳር ለመመለስ እገዛ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡
እንደእሳቸው ገለጻ፤ እንደ አዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ያሉ የከተማ ልማት ፕሮጀክቶች የተቀናጁ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች አካባቢያዊና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ የልማት ውጤቶችን ማስገኘት እንደሚችሉ አሳይተዋል፡፡ የከተማዋ ልማት ለበጎ የከተማ አመራርና አስተዳደር ሥርዓት እንዲሁም በሥራ ፈጠራ ላይ ለተመሠረተ ዘላቂ ልማት ምሳሌ መሆን የሚችል ተግባር ነው፡፡
20ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ጉባኤ በርካታ የልምድ ልውውጦች የተደረጉበት የትብብር፣ የፈጠራና የጋራ ርዕይ መድረክ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ በጉባኤው በሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ የኢንቨስትመንት አቅምን ለመጠቀም እንዲሁም ሥራ ፈጠራን፣ ማኅበራዊ ዋስትናንና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን የመቋቋም ብቃትን ከመሠረተ ልማት ጋር ማስተሳሰር የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ምክክር ተደርጎባቸዋል፡፡
ለአፍሪካ፣ በተለይም ለአህጉሪቱ ወጣቶች፣ አካታች የኢኮኖሚ እድሎችን መፍጠር የሚችሉ ፖሊሲዎች እንደሚያስፈልጉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በመንግሥታት፣ በልማት አጋሮች፣ በሲቪክ ማኅበራትና በግሉ ዘርፍ መካከል ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
የዓለም ሥራ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፋንፋን ራዋንዪንዶ ካይራንጓ በበኩላቸው፤ በጉባኤው የተነሱት ሃሳቦች አካታችና አስተማማኝ የሆነች እንዲሁም ለችግሮች የማትበገር አፍሪካን እውን ለማድረግ አቅጣጫ የጠቆሙ የጋራ እሳቤዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ቴክኖሎጂን ያማከለ የሥራ ፈጠራ ሥርዓት በመዘርጋት የአፍሪካን የምጣኔ ሀብት አካታች፣ ዘላቂና ለችግሮች የማይበገር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ሥራ ከመፍጠር ባሻገር ለችግሮች የማይበገሩ ማኅበረሰቦችን የመገንባት ሥራም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዛምቢያ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን 21ኛውን የዓለም የሥራ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ጉባኤ እንድታስተናግድ እንደተመረጠች ታውቋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም