የሉሲ 50ኛ ዓመት ከምርምር ባሻገር

ዜና ሐተታ

በ2ኛው የኢትዮጵያ ቅርስ ምርምር ዓመታዊ ጉባኤ ላይ 26 ያህል የምርምር ሥራዎች በሀገር ውስጥ እና በውጭ ተመራማሪዎች ቀርበዋል። የዘንድሮውን ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ ልዩ የሚያደርገው ሉሲ የተገኘችበት (ይፋ የሆነችበት) 50ኛ ዓመት መሆኑ ነው። ሉሲን ካገኙት ተመራማሪዎች አንዷ የሆኑት ፈረንሳዊቷ የ88 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ራይሞንድ ቦኔፍል ደግሞ በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።

ተመራማሪዋ 52 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለው ሲያስታውሱ፤ እርሳቸውን ጨምሮ አምስት ወጣት ተመራማሪዎችን የያዘ ቡድን በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 1973 ቅሪተ አካል ይገኝበታል። ወደተባለው የኢትዮጵያዋ ምድር አፋር ሃዳር አቀና። ሦስቱ ከፈረንሳይ እና ሁለቱ ከአሜሪካ የተውጣጡበት ይህ የምርምር ቡድን ምርምሩን ሲያካሂድ ከቆየ በኋላ በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 1974 (በኢትዮጵያ በህዳር ወር 1967 ዓ.ም) ሉሲን ማግኘቱን አረጋግጧል።

እነሆ ኢትዮጵያም ምድረ ቀደምት መሆኗ ተረጋገጠ።

እነሆ ዘንድሮ ግማሽ ክፍለ ዘመን ሆነው። የታሪክ ተመራማሪው እና የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዓመታዊ የኢትዮጵያ ቅርስ ምርምር ጉባኤ ማድረግ ያስፈለገው ከእዚህ በፊት በነበሩት ዘመናት ራሱን  የቻለ የምርምር ዘርፍ ስላልነበረው ነው። ከእዚህ በፊት ይደረግ የነበረው ምርምርና ጉባኤ ሳይንሳዊ እውቀትን ለማሳደግ ብቻ ነው።

ራሱን የቻለ ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ ከተጀመረ በኋላ ግን ዘርፉን በማስፋት ክብካቤ እና ጥገና ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል ብለዋል።

“ወደፊት ቨርቹዋል ውይይትና ገለጻ እንዲኖር ይደረጋል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ በሥነ ሕይወት ከ160 ሚሊዮን ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸው ቅሪተ አካላት ያሏት ሀገር ናት ። በእዚህ የቅርስ ባለቤትነቷም ከ200 በላይ በሆኑ የቅርስ ፕሮጀክቶች ከተለያዩ ሀገራት የምርምር ተቋማት ጋር እየሠራች ትገኛለች፤ የቅርስ ተማራማሪዎችም የምርምር ቦታቸው ኢትዮጵያ ናት ነው ያሉት።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሉሲን በተለያዩ ሀገራት የማሳየት እና የኢኮኖሚ ምንጭ የማድረግ ሥራ ይሠራል። በምርምር ዘርፉም ሳይንቲስቶችን የሚያሳትፍ የፓንቶሎጂ ቤተ ሙከራ አዲስ አበባ ውስጥ ይገነባል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በዓመታዊ የምርምር ጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ ያለፉት አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የሽግግር እና የማንፀባረቅ ዓመታት ናቸው። የባለሥልጣኑ አመራሮች እና ባለሙያዎች ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመጣ አቅጣጫ ውይይት አድርገው ተቋሙን እንደገና የማዋቀር ሥራ ተሠርቷል። በተደረገው ውይይት ከተገኙ ክፍተቶችም አንዱ በተቋሙ ውስጥ የምርምር ክፍል መደቦች አለመኖር ነበር። በቅርስ ተቋም ውስጥ ጥልቅ የምርምር ዘርፍ ከሌለ ቅርስን መጠበቅ አደገኛ መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹ባለሥልጣኑ ከሁለት ዓመታት በፊት በአምስት ክፍሎች የምርምር ዘርፍ አደራጅቷል›› ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ አንደኛው እና ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቅርስ ምርምር ጉባኤዎች የእዚህ ለውጥ ውጤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። አሠራሩን ምቹ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ሶፍትዌር እንደሚዘጋጅና ተመራማሪዎች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ይደረጋል ነው ያሉት።

ሶፍትዌሩ ወጣት ተመራማሪዎችን ለማምጣት እና ተመራማሪዎች በቀላሉ ሥራዎቻቸውን ተደራሽ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

የቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ያላት ተፈጥሯዊና ባሕላዊ የቅርስ ሀብት የሚገባውን ያህል ለኅብረተሰቡ ጥቅም አላስገኘም። መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት መስጠት የጀመረው በቅርብ ዓመታት ነው። በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት ለቅርስ ሀብት ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቷል፤ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘትም እየተሠራ ነው።

እንደ አንድነት ፓርክ እና የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ሙዚየም የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በሚቀጥሉት ወራት እና ዓመታትም ሌሎች የቅርስ ቦታዎች ይከፈታሉ ብለዋል።

“ያለ ሳይንሳዊ ምርምር ቅርስን መጠበቅ አይቻልም” ያሉት ሚኒስትሯ፤ ላለፉት 70 ዓመታት የኢትዮጵያ ቅርስ ሲያገለግል የነበረው እርባና ቢስ ለሆነ የአካዳሚ ጥናት ብቻ ነበር ብለዋል። በ1950ዎቹ በፈረንሳይ ተመራማሪዎች መሠረት የጣለው የቅርስ ምርምር ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት አሳድጎ ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ መጀመሩ ዘርፉን ለማሳደግና ኅብረተሰቡንም ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚውል ነው የገለጹት።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የምርምር ጉባኤው ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውል የሚያደርግ ነው፤ ወጣት ተመራማሪዎችን የሚያሳትፍ ነው። የምርምር ዘርፉም ኢትዮጵያን እና ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችን የሚያስተሳስር ይሆናል። በተለይም የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና የፈረንሳይ የምርምርና አካዳሚክ ተቋም ግንኙነት የተጠናከረ ነው ብለዋል።

የሚሠሩ ጥናቶችና የሚደረጉ ውይይቶች ለአካዳሚያዊ ግብዓትና ለእውቀት ብቻ ከመዋል አልፈው ለኢኮኖሚው ዘርፍ አበርክቶ እንዲኖራቸው መሠራት አለበት ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ አሳስበዋል።

ከ26 በላይ የምርምር ጽሑፎች የቀረቡበት ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቅርስ ምርምር ዓመታዊ ጉባኤ “ምርምር ለቅርስ ጥበቃ እና ልማት” በሚል መሪ ቃል ግንቦት 14 እና 15 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሂዷል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You