
አዋሽ ሰባት፦ በአፋር ክልል አዋሽ ከተማ ግንባታው ተጠናቆ የተመረቀው የአዋሽ ፊለር ፋብሪካ 97 በመቶ የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች ግብዓትነት እንደሚጠቀም ተገለጸ፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ የተመረቀው ፋብሪካ በሀገሪቱ በዓይነቱ የመጀመሪያና በአፋር ክልል ሊገነቡ ከታሰቡት ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የአዋሽ ፊለር ፋብሪካ 97 በመቶ የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን የሚጠቀም ነው ብለዋል፡፡
ንብረትነቱ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሆነው አዋሽ ፊለር ፋብሪካ ለበርካታ ኢንዱስትሪዎች ግብአቶችን እንደሚያቀርብ ገልጸው፤ፋብሪካው 97 በመቶ የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን እንደሚጠቀም ተናግረዋል።ይህም በፋብሪካው ብቻ ሳይሆን በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ረገድ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ፋብሪካው ተኪ ምርቶችን በማምረት ሀገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ አመልክተው፤ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር በአጠቃላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍ በኩል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በአፋር ክልል በቅርቡም ሌሎች ሁለት ፋብሪካዎችን ለመገንባት ፕሮጀክቶቹ በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በሀገሪቱ ታሪክ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው አዋሽ ፊለር ፋብሪካ ለተለያዩ ምርቶች ግብዓት የሚሆን ምርት እንደሚያመርትም ጠቁመዋል፡፡
በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ በመገኘት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር ሀጂ አወል አርባ፤ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፋብሪካውን አጠናቆ ወደ ሥራ ማስገባቱን አድንቀው፤ ኩባንያው ቃል በገባው መሠረት ወደፊትም በርካታ ሥራዎችን እንደሚሠራ፤ ለሚሠራቸውም ሥራዎች ሁሉ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግለት ገልጸዋል።
አዋሽ ከተማ ከሁሉም አቅጣጫ ማዕከል እንደ መሆንዋ ለኢንቨስትመንት አዋሳኝ መሆኗን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ከተማዋ በወደቦች አካባቢ የምትገኝ በመሆኗ የኢኮኖሚ እና ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ፊለር ፋብሪካው በካልስየም ካርቦኔት የበለፀገ ኮትድ ምርት እንደሚያመርትና ይህም ምርት ለፒፒሲ፣ ለወረቀት፣ ለጫማ ሶል፣ ለቀለም እና ተያያዥ ምርቶች ግብዓት እንደሚሆን ተገልጿል።
ይህ ፋብሪካ በአዋሽ ከተማና በአካባቢው ለሚገኙ ማህበረሰቦች ተጨማሪ የሥራ እድል የሚፈጥር ከመሆኑም በተጨማሪ ለአዋሽ ከተማም እድገት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ተመልክቷል።
በፋብሪካው የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ሀጂ አወል አርባ፣ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ ሥነሥርዓቱም በክልሉ ባሕል መሠረት በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት መጀመሩ ታውቋል፡፡
ግርማ መንግስቴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም