
ዜና ሐተታ
ኢትዮጵያ አይዲ ፎር አፍሪካ 2025 ዓለም አቀፍ ጉባኤን አሰናድታ በስኬት አጠናቃለች። በእዚህም ለሀገራዊ ዲጅታላይዜሽን ሽግግር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለውን የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ለተሳታፊዎች አጋርታለች።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊ፣ አካታች እና መሠረታዊ የዲጂታል ማንነት መለያ ሥርዓት ዘርግታለች፡፡ ይህም ዜጎች በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ዲጂታል ማንነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ፋይዳ የዲጂታል ማንነት ሥርዓት ካርድ ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችን ግላዊ መረጃዎች ምሥጢራዊነት በመጠበቅና አስፈላጊ የሆነውን ብቻ በማጋራት ማንነትን የሚያረጋግጥ ልዩ መለያ ቁጥር ነው፡፡ በፋይናንስ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ቴሌኮምን ጨምሮ በሌሎችም የሕዝብ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር ዜጎች ለሚፈልጉት አገልግሎት መደላድል ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
እንደ ፋይናንስ፣ ጤና እና ትምህርት ባሉ ቁልፍ ዘርፎች የተቀናጀው ፋይዳ፣ 9 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ብር በዲጂታል ግብይት እንዲዘዋወር እያገዘ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ፋይዳ መታወቂያ የዲጅታል ክፍያ ሥርዓት፣ የዳታ መለዋወጫና ማጋሪያ ሥርዓቶችን በማቀናጀት የኢትዮጵያን የዲጅታል ትራንስፎርሜሽንን ለማሳለጥ ያግዛል፡፡
ኢትዮጵያ የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀርጻ ስትተገብር መቆየቷን አስታውሰው፤ በሀገር ደረጃ የተቀናጀ አመራር እና ያልተቋረጠ ግምገማ ሥርዓት በመከተል ውጤታማ መሆን ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ግልጽ እና አሳታፊ ስትራቴጂ፣ ሀገራዊ ቀዳሚ አጀንዳዎችን በመለየትና አስቻይ የሕግ ማሕቀፎች መቀረጻቸው እንደ የዲጅታል ኢትዮጵያ ስኬት መሠረቶች መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በቀጣይነትም ባለፉት ዓመታት የተገኙ ልምዶችን እና ውጤቶችን፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ እድገቶችና አዳጊ ሀገራዊ ፍላጎቶችን እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ ዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እንደሚተገበር አብራርተዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ሽግግርን ለማፋጠን እና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እንደ ሀገር የዲጂታል ካውንስል በማቋቋም ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ፣ የዳታ መለዋወጫ ፕላትፎርም ግንባታ፣ የይፋዊ ቁልፍ መሠረተ ልማት እንዲሁም የዳታ ማዕከሎች ግንባታ ዲጂታል ካውንስሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ካሉት ውስጥ ተጠቃሽ እንደሆኑም ገልጸዋል።
በዲጂታል መሠረቶች የዜጎችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የኤሌክትሮኒክ ንግድ ሥርዓትን ማመቻቸት፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ እና አቅርቦትን ማሳለጥ ለሀገሪቱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡
የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ የሥራ ድግግሞሽን በማስቀረት የሀብት ብክነትን እንደሚቀንስ አመልክተው፤ አካታች የሆነ የዲጅታል ሽግግር ለማድረግ የዲጂታል መታወቂያ ወሳኝ ሚና አለው፡፡የዳታ መለዋወጫ ሥርዓት መገንባቱም በመንግሥት ተቋማት፣ በግሉ ዘርፍ መካከል መረጃዎችን በቀላሉ መለዋወጥ በማስቻል መረጃን መሠረት ያደረገ የውሳኔ ሰጪነት ሥርዓት እንደሚፈጠር ገልጸዋል፡፡
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከልን በማቋቋም የመንግሥት አገልግሎቶች በአንድ ቦታ እየተሰጡ መሆኑን ገልጸው፤ በእዚህም የዲጂታል መሠረተ ልማቶች ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ውጤታማ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ለዲጂታል ሽግግሩ መሠረታዊ የሆኑ ተግራት ሲከናወኑ ለደህንነት ቅድሚያ በመስጠት እየተተገበረ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም ሊፈጠሩ የሚችሉ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነቶችን በመቀነስ ምስጢራዊነትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ያስችላል።
ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር መሠረት ለሆኑት የዲጂታል መታወቂያ፣ የክፍያ ሥርዓት እና ይፋዊ ቁልፍ መሠረተ ልማት ላይ ጠንካራ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል ሥነ-ምህዳር ለመፍጠር የሚያስችል የሳይበር ደህንነት የቅድመ ጥንቃቄ ሞዴል መተግበሩን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባና የመኖሪያ አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ፤ አዲስ አበባ ከተማ አካታች የዲጂታል ማንነት ሥርዓትን ለመገንባት እየሠራች ነው፡፡በእዚህ የመታወቂያ ሥርዓትም የአገልግሎት አሰጣጥና የተቋማት ተዓማኒነት ማደጉን ጠቅሰዋል።አዲስ አበባ ስማርት ከተማ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መሠረት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያሰናዳችው አይዲ ፎር አፍሪካ 2025 ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከግንቦት 12 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን፤ ኮትዲቧር የ2026 አይዲ ፎር አፍሪካ ጉባኤ አዘጋጅ ሆና ተመርጣለች፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም