ሰላም የአለም ፍጥረት ሁሉ መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ የሰው ዘር ፣ በጫካ የሚኖሩ እንስሳት፣ በሰማይ የሚበሩ አእዋፋትና በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት በሙሉ የሰላም መኖር ከህልውናቸው ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ አጥብቀው ይሹታል፡፡
ሰላም ለሁሉም የሚያስፈልግ መሰረታዊ ጉዳይ የመሆኑን ያህል፤ ሁሉም ለሰላም መስፈን የድርሻውን ማበርከቱም ተጠባቂ ነገር ነው፤ እንደ ግዴታም መወሰድ አለበት፡፡ በተለይ በአገራችን ባለፉት አመታት የሰላም እጦት የፈጠረውን ማህበራዊ ምስቅልቅል፤ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ፤ የዜጎች ሞትና የአካል ጉዳት እንዲሁም መፈናቀል ላስተዋለ ዋጋው ምን ያህል ውድ እንደሆነ ይገነዘባልና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ይወጣ ዘንድ ግድ ይላል፡፡ አገራችንም በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰላም ሚኒስቴር በማቋቋም ዘርፈ ብዙ ኃላፊነቶችን በመስጠት እንቅስቃሴ የጀመረችው ለዚሁ ነው፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከሃይማኖት አባቶች፣ከሚድያ ተቋማት በሰላም ዙርያ ሰሞኑን ውይይት አካሂዷል፡፡ ከትናንት በስቲያ ደግሞ የሰላም እሴትን በመገንባት ረገድ ጉልህ ሚና ከሚያበረክቱት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ምክክር አድርጓል፡፡ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በወቅቱ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ስትከፋና ስታዝን የጥበብ ሰዎች አለንልሽ ሊሏት ይገባል፡፡ የጥበባቸውን ፍሬ ለአገራቸው ሰላም በማበርከት ውስጥ የሚገኘውን ደስታ ማጣጣም አለባቸው፡፡
የኪነ ጥበብ ሰዎች የጥላቻን መጥፎ ዘር በፍቅር፣ በመደማመጥና በመቻቻል ማጥፋት ይችላሉ፡፡ እንደ ኪነጥበብ ባለሙያዎች ሁሉ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙሃን ለሰላም ከመቼውም ግዜ መስራት የሚገባቸው ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ምክንያቱም ሰላም ለሁሉም እጅግ ወሳኝና መሰረታዊ ጉዳይ ነውና፡፡
በእርግጥም ጥበብ በየፈርጁ ስትከወን የሻከሩ ልቦችን በማለሳለስ፤ በጥላቻ የተሞሉ ልቦችን በፍቅር በማራራት፤ በጥርጣሬ ተራርቀው የነበሩትን በማቀራረብና ጠንካራ ጉዳዮችን በማዋዛት የማስተላለፍ እምቅ አቅም አላት፡፡ እናም በየዘርፉ የተሰማሩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተሰጥኦዋቸውን በመጠቀም ስለ ሰላም በብርቱ መንገድ ሊሰሩና ሊያስተምሩ ይገባል፡፡ ይህን ግዴታቸውን ሲወጡ እነርሱም በሚናኘው መልካም የሰላም አየር ጥበብን ሌላ ተልእኮ በመስጠት ለህብረተሰብ ብልጽግና ማዋል ይችላሉ፡፡
ሰላምን በማስፈን ረገድ ቁልፍ ሚና ከሚያበረክቱት መካከል ፖለቲከኞችና ፓርቲዎቻቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህ ወገን ያሉት አካላት የሚራምዱትን አቋም የሚደግፉ እና እስከ መጨረሻው የጉዞ ምዕራፍ አብረን እንሄዳለን የሚሉ በርካታ ተከታዮች አሏቸው፡፡ ስለሆነም ሃሳብን በነጻነት ማንጸባረቅ፤ ሃሳብን አንጸባርቆ ደጋፊ ማፍራት፤ ደጋፊ አፍርቶ ምርጫ መወዳደርና ማሸነፍ የሚቻለው በአገር ሰላም ሲሰፍን መሆኑን በመገንዘብ ከምንም በፊት ስለ ሰላም ዘብ መቆም አለባቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከትናንት በስቲያ ከውጭ አገራት የተመለሱትን ጨምሮ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅትም በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ መንፈስ መወያየትና በሃሳብ ብቻ መሸናነፍ ላይ የተመሰረተ አዲስ የፖሊቲካ ባህል መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ይህም ያስፈለገበት ምክንያት ሁሉንም አንድ የሚያደርግ የጋራ ህዝብና አገር በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ በመልእክታቸው የሰላምና መረጋጋት ጉዳዮች በፍጥነት መፈታት እንደሚገባቸው አጽንኦት የሰጡ ሲሆን፤ ውይይቱም ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በቅድሚያ ሰላም የማስፈኑን ጉዳይ እንዲገነዘቡት የሚጠቁም በመሆኑ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች የመልእክታቸውም መነሻም ሆነ መድረሻ ሰላም መሆን አለበት፡፡ አገሪቱ ከአጋጠማት ወቅታዊ የሰላም መደፍረስ አንጻር የሰላም እሴትን ለመገንባት ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለባቸው እንደመሆናቸው፤ በሃይማኖታዊ አስተምህሮቶቻቸው ምእመናንን መግራት፤ የሚበልጠውንና የሚያቀራርበውን መንገድ ማሳየት የእነርሱ ድርሻ ነው፡፡
መገናኛ ብዙሃንም በሰላም እሴት ግንባታ ረገድ የሚጠበቅባቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ በተለይ የሰላም ጋዜጠኝነት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አለፍ ገደም እያለ ከሚከሰት ግጭት ለመላቀቅ ለሚጥሩ አገራት ሁነኛ መርህ ስለሆነ በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ግንዛቤው ሊሰርጽ ይገባል፡፡
በሰላም ጋዜጠኝነት መርህ አለመግባቶችና ግጭቶችን ብቻ እያነፈነፉ ከመዘገብ ይልቅ በህብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙትን የዳበሩ የሰላም እሴትን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችንም እየነቀሱ በማቅረብ ይተገበራል፡፡ ግጭቶች በሚዘገቡበት ወቅትም የሚያባብሱትን ጥቃቅን ህጸጾች ከማጉላት ይልቅ መፍትሄ አመላካች መሆን፤ ከብዙዎቹ ችግሮች ይልቅ ጥቂት መልካም ሰበዞችን እየመረጡ ማስተጋባትም ተመራጭ ይሆናል፡፡ ስለዚህም የሰላም ጋዜጠኝነት እሴት እንዲጎለብት ጋዜጠኞችን ከሚያሰለጥኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጀምሮ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
ሰላምን ሁሉም እንደሚሻው ሁሉ ሰላም ይሰፍንም ዘንድ የድርሻውን ካበረከተ የበለጸገች፣ ህዝቦቿ የሚሰደዱባት ሳይሆን በፍስሃ እድሜ ዘመናቸውን የሚያሳልፉባት እና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያ በቅርቡ እውን እንደምትሆን ጥርጥር የለውም፡፡