ስሜት ለእውቀት ይታዘዝ

ከጊዜ ወደ ጊዜ ውስብስብ እና እርስ በርስ በተሳሰረ ዓለም ውስጥ የአንድን ሰው ስሜት የመቆጣጠር ችሎታ እጅግ አስፈላጊ እና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ይህ ስሜት መቆጣጠር ችሎታ፣ የስሜት ልህቀት ወይም ራስን መግዛት በእንግሊዘኛው (ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ) ተብሎ ይጠራል።

ደካማ የስሜት ቁጥጥር ያለው ግለሰብ እራሱን ብቻ ሳይሆን ከግል ግንኙነቶቹ ጀምሮ እስከ ሙያዊ የሥራ አካባቢዎቹ ድረስ ኑሮውን እና ሕይወቱን ሁሉ ያመሰቃቅላል። ይሄንን የስሜት ቁጥጥር ማነስ እንደ ሕብረተሰብ የሚከሰት ችግር ሲሆን ደግሞ ቀውሱ ብዙ እና ውስብስብ ነው።

ስሜትን የመቆጣጠር ችሎታ ብቻውን የሚመጣ እና የሚከወን ሳይሆን እራስን ከማወቅ፣ ራስን ከመቆጣጠር፣ እራስን ለመግዛት ከሚኖር ተነሳሽነት፣ ለሰዎች ከሚኖረን ማሰብ እና ከተለያዩ የማኅበራዊ ችሎታዎች ጋር በማቆራኘት የሚከወን ነው።

በዚህ መስክ የሥነ-ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዳንኤል ጎልማን የስሜት ልህቀት ለምን ከአይኪው (IQ) ወይም በጥልቀት ከማሰብ አቅም የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል (Emotional Intelligence: Why It Can Matter More Than IQ) በሚለው መጽሐፋቸው፣ በተለያዩ የሕይወት ዘርፎች ስኬትን ለመወሰን ስሜትን የመቆጣጠር ችሎታ (ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ) በጣም አስፈላጊ ነው። ስሜቱን መግዛት የማይችል ሰው በማኅበራዊ ኑሮው ስኬትን ሊያጣ ወደ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ሊያመራ እንደሚችል በግልጽ ያስቀምጣል።

ልንቆጣጠራቸው የማንችላቸው ስሜቶች መዘዞቻቸው እጅግ አስከፊ ነው። በሕብረተሰብ ደረጃ፣ የስሜትን የመቆጣጠር እጦት ለወንጀል፣ ለቤት ውስጥ ብጥብጥ እና በሥራ ቦታ ለሚደርስ ትንኮሳ ከባድ አስተዋፅዖ ያደርጋል።

ለምሳሌ፣ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የስሜት መቃወስ ወይም የስሜት መቆጣጠር ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ጥቃትን የማድረስ እድላቸው ከፍተኛ ነው። 75 በመቶ የሚሆኑ ወንጀለኞች ስሜታቸውን የመቆጣጠር ችግር ያለባቸው መሆናቸውም በጥናቶች ተመላክቷል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ በጂኤምኦዎች አስፈላጊነት ወይም ጉዳት ላይ ያተኮረ ክርክር ላይ ተገኝቻለሁ። ዝግጅቱ የፕሮፌሰሮች እና የዶክተሮች ጋጋታ የበዛበት ነው። ከእነዚህ ምሁራን ሲሰማ የቆየውም ለአካዳሚክ እውቀታቸው ያላቸው ቀናይነት እና ጥብቅና ነው። ከዚህ ቀደም እኔ እንደማስበው ሰው በትምህርት እውቀት ከፍ እያለ እድሜውም እየጨመረ ሲሄድ የስሜት ቁጥጥር አቅሙ ከፍ እንደሚል ነው። በዚህኛው ክርክር ግን ያየሁት ይሄንን አይደለም።

ተከራካሪዎች አቅላቸውን የሳቱ እስኪመስል እራሳቸውን እና ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ከነሱ ተቃራኒ ሀሳብ የያዘውን ሰው ሀሳብን ሳይሆን የሀሳቡን ባለቤት ሲዘልፉ፤ ፍጹም አክብሮት በጎደለው ንግግር ‹‹ሀሳባቸውን›› ሲገልጹ ተመልክቼ ፍጹም ተስፋ እንድቆርጥ አስገድደውኛል። (ሀሳባቸውን የሚለው ቃል በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያስገባሁት ሀሳብ ከሚለው ይልቅ ስድብ የሚለው በትክክል የሚገልጸው ቢሆንም ለአንባቢያኖቼ ክብር ቃሉን የተጠቀምኩት መሆኑ ይታወቅልኝ)።

ሁኔታው በምዕናባችሁ እንዲከሰትም የነበረውን እንደሚከተለው አብራራለሁ። ከፊል አዳራሹ በተማሪዎች፣ በመምህራን እና ለቀረበው የክርክር ጭብጥ ፍላጎት ባላቸው ግለሰቦች እና ጋዜጠኞች ተሞልቷል። ታዳሚውም በዘርፉ ልምድ እና በቂ ምርምር ያደረጉ ግለሰቦች ተገኝተዋል በመባሉ ስለ የዘረመል ምህንድስና የግብርና ምርት (ጂኤምኦዎች) ላይ ጠቃሚ ውይይት ለመስማት ጓጉቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀሳቡ ጭብጥ ብዙ ክርክር የሚቀርብበት በመሆኑ እኔም በወቅቱ ክርክሩ እንደተጀመረ፣ በጥናት እና በመረጃ የተደገፈ ጠንካራ የሃሳብ ልውውጥ እንደሚደረግ ገምቻለሁ። ይሁን እንጂ ግምቴ ሳይሰምር የውይይቱ ቃና ከደቂቃዎች በኋላ ተለውጦ አግኝቼዋለሁ።

በክርክሩ ወቅት የተወሰኑ ተሳታፊዎች ክርክሩን በምርምር ውጤታቸው እና በንባባቸው አስደግፈው ከመሞገት ይልቅ ወደ ግል ጥቃት ወስደውት ለክብራቸው እና ለስማቸው የማይመጥን ንግግርን አድርገዋል። ይህ አይነቱ ንግግር የክርክሩን ታማኝነት ከመሸርሸር ባለፈ ለተገኙት ተማሪዎች መጥፎ ምሳሌን የሚሆን ነው። ስሜትን መቆጣጠር (ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ) ባልነበራቸው ተከራካሪዎች መሃከል የተሰነዘሩ ሀሳቦች አንዳንዶቹ ንቀትን ያዘሉ በመሆናቸው ለተማሪዎቻቸው አዘንኩ።

ይህንን ሁኔታ እየተመለከትኩ፣ በተገኙት ተማሪዎች ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ስሜት ለማሰላሰል ተገደድኩ። አርአያ መሆን ያለባቸው ሰዎች በሲቪል ዲስኩር (ክርክር) ላይ እራሳቸውን ገዝተው ስሜታቸውን ተቆጣጥረው መሳተፍ ካልቻሉ ለቀጣዩ ትውልድ ምን መልእክት ያስተላልፋል?

ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ የአስተማሪዎቻቸውን እና አብረዋቸው የሚውሏቸውን ሰዎች ባህሪ እንደሚወርሱ ጥናቶች ያሳያሉ። አስተማሪዎች ደካማ የስሜታዊ ቁጥጥርን ሲኖራቸው (ሎ ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ) ሲኖራቸው፣ ተማሪዎችም እንደዚሁ አይነት ተመሳሳይ ባህሪን ያሳያሉ።

ያላከበርከው ተማሪ ሊያከብርህ አይችልም። ሰውን ስትዘልፍ ያሳየኸው ትውልድ ነገ እንደማይዘልፍህ ማስረጃ የለህም። ራስህን መቆጣጠር ያልቻልክ ግለሰብም ሌላውን ልትቆጣጠር አትችልም። ምናልባት ዛሬ ሳይችል ቀርቶ ለንቀትህ ምላሽ ባይሰጥም ነገ ቀን ጠብቆ ከራራልህ እንደናቅከው ይነግርሃል ካልራራልህ ደግሞ ንቀትህን ይደግምልሃል።

የአካዳሚክ ሥነምህዳሩ ብዙውን ጊዜ የስሜት መቃወስን ወይም ራስን አለመቆጣጠርን ሊያባብሱ በሚችሉ ግፊቶች የተሞላ ነው። ውሻ በበላበት እንደሚጮኸው ሁሉ አጥኝዎች በስፖንሰር አድራጊዎቻቸው ሀሳብ ነገር ግን በነሱ አፍና ምላስ ይጮሃሉ። የሚያውቁትን እውነት ሊክዱ ወይም ሊያጣምሙ እና ሊያኮስሱ ይደፍራሉ።

ምሁራን ምሁር መሆናቸውን የሚመጥነው እራሳቸውን መግዛት ሀሳባቸውን በማደራጀት ማስረዳት፤ ከተቻለም በሰርቶ ማሳያዎች በማስደገፍ መሞገት እንጂ በሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ፊት መዘላለፍ አይመጥናቸውም። አንድ ወዳጄ እንደነገረኝም ተማሪ እያለ እጅግ አስቸጋሪ ሰው ነበረ።

ነገር ግን የማያስቸግርበት ክፍለግዜ ቢኖር ዐይነስውር የግብረ ገብ መምህሩ ሲያስተምሩ ብቻ ነው። ሁኔታውንም ሲያስረዳኝ ‹‹በሳቸው ክፍለ ግዜ የማልረብሸው ወድጄ ሳይሆን ሼም ይዞኝ ነው›› ምክንያቱ ደግሞ ስበጠብጥ መምህሩ ስሜን ጠርተው ‹ምነው የኔ ልጅ ጨዋ አልነበርክ? ዛሬ ምን ተገኘ? ተባረክ ጌታዬ አትረብሽ› ብቻ ነበር የሚሉኝ። ሌላው በኩርኩም ሲያነደኝ እንደማልረባ ሲነግረኝ ለወዲያ ብተውም ለስድባቸው እና ለኩርኩማቸው ምላሽ የሚሆን ተንኮል ስሸርብ ነበር የምቆየው›› ይላል።

እኝህ የግብረገብ መምህር ያደረጉት ነገር ቢኖር ልጁ ልጅ እንደሆነ እና ጥሩ ሰው ሊሆን የሚችል መሆኑን በመንገር እራሳቸውን ገዝተው እራሱን እንዲገዛ ነበር የሚያደርጉት። በአካዳሚው ዘርፍ ውስጥ ሚኖር የስሜት ቁጥጥር ማነስ ወይም አስተማሪዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር የማይችሉበት ደረጃ ሲደርሱ አስቸጋሪ የትምህርት አካባቢን ይፈጥራሉ። ተስፋ የቆረጡ ተማሪዎችንም ቁጥር ያበዛሉ።

ጥናቶች እንደሚያሳዩትም በትምህርት ክፍሎች ውስጥ የሚኖር ጥሩ አውድ ለተማሪዎች የውጤት መሻሻል አወንታዊ አስተዋጾ አለው። በአንጻሩ፣ በአሉታዊነት እና በግጭት ውስጥ ያሉ የመማሪያ ክፍሎች ለተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት መመዝገብ እና ለተማሪ ትምህርት መቋረጥ ምክንያት ይሆናል።

አንድ ራሱን መግዛት ያቃተው መምህር ሴቶች ላይ በሚያደርሰው ትንኮሳ የተማሪዎች ሕይወት ይበላሻል። መምህራን ለተማሪዎቻቸው ተቀዳሚ አርአያ ናቸው። ስለዚህ፣ ስሜት ልህቀታቸው ወይም ስሜታዊ ውሳኔዎቻቸው የተማሪዎቻውን በስሜት መብሰል ሊወስን ይችላል።

ተማሪዎችም የአካዳሚክ ውይይቶች ወይም ክርክሮች ላይ የሚገቡት ከነሱ የሚሻሉ እና አዳዲስ ሃሳቦች አሏቸው ብለው የሚያስቧቸውን መምህራኖቻቸውን ለመመልከት ነው። ታዲያ በእንደዚህ አይነት ዘለፋዎች መምህራኖቻቸው ሲሰደቡ ወይም ሲሰድቡ መመልከታቸው ምን ሊፈጥርባቸው እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም።

ከፍተኛ እራስን የመቆጣጠር ወይም ስሜትን መግዛት አቅም ያለው ሰው የተሻለ ግንኙነትን ማስቀጠል፣ በትብብር የመሥራት እና ግጭቶችን የመፍታት ጥበቡ የላቀ ይሆናል። አንድ የትዳር አጋር ያለው ግለሰብ እራሱን የሚገዛ እና ስሜቱን የሚቆጣጠር ከሆነ እንብዛም ትዳሩ በፍች አይጠናቀቅም።

አንድ ልጆች ያሉት አባት እራሱን የሚቆጣጠር ስሜቱን የሚገዛ ከሆነ እብሪተኛ ልጆችን አያሳድግም። ክብደት እየጨመርኩ ነው ለጤናዬ ያሰጋኛል ምትል እንስት እራሷን ከምግብ ፍላጎት ስሜቷ መቆጣጠር ካልቻለች፤ በመድሃኒት የምትቆጣጠረው በሽታን ታተርፋለች።

አንዲት ብልህ ሴት እራሷን ምትገዛ ስሜቷን የምትቆጣጠር እና እንደመጣላት የማትናገር አስተዋይ ከሆነች ጥሩ ትዳር፣ ጥሩ ሥራ እና ጥሩ ከባቢ ይኖራታል። በተመሳሳይ ለእውቀት ልህቀት (ለአይኪው) የሚጨነቅ ብቻ ሳይሆን ለስሜት ልህቀቱ (ኢሞሽል ኢንተለጀንስ) በትኩረት የሚሠራ መምህር የእውቀት ብቻ ሳይሆን የሕይወትም መምህር ይሆናል።

እንደዚህ እንደዚህ እያልን በማኅበረሰብ ደረጃ የስሜት ልህቀት፣ ራስን የመግዛት ጥበብ ወይም ስሜትን የመቆጣጠር አቅም ማዳበር የምንችል ከሆነ ሰላማዊ አካባቢን በመፍጠር፤ ከግጭት የጸዳች ሀገር እንዲኖረን ያስችለናል። የሰዎችን ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ሰዎቹንም ከመውቀስ የምንጀምር ከሆነ መግባባት ያቅተናል።

መነጋገር እና መስማማት ይሳነናል። ለተፈጠረው ጥቂት የሀሳብ ልዩነት ጠመንጃ ለማንሳት ይዳዳናል። ቆም ብሎ ማሰብ ሲሳነን አንድም ከፊደል ‹‹ሀ›› ብሎ አንድም ከመከራ ‹‹ዋይ›› ብሎ ይማራል እንደሚባለው ከ‹‹ዋይ›› ተማሪዎች እንሆናለን። ከ‹‹ዋይም›› ለመማር ግን የስሜት ልህቀት፣ ቆም ብሎ ማሰብ እና ስሜቱ የሚነዳው ሳይሆን ስሜቱን ሚቆጣጠር ሰው በመሆን የሚገኝ ትምህርት ነው።

ታዲያ ስለስሜት ልህቀት ወይም ስሜትን መቆጣጠር መቻል ይህንን ሁሉ ካልን እንዴት እራሳችንን እንቆጣጠር ወይም እንዴት እራስን መግዛት እንማር የሚለውን አለማንሳት ተገቢ አይሆንም። የመጀመሪያው እራስን የመግዛት ችግር ካለብን ችግሩ እንዳለብን አምኖ መቀበል ዋነኛው ነው። ‹‹እኔ እኮ ከአያቴ የወረስኩት ሀይለኝነት አለብኝ። በዘራችን ነው አባቴም ብልጭ ይልበታል›› አለማለት። አያትህ እና አባትህ የሚወረስ ጠቃሚ ንብረት ካላቸው እሱን ብትወርስ የተሻለ ነው።

እነ ነውር ጌጡ ሳትሆን ጥሩ ያልሆነውን ችግርህን ጥሩ አይደለም ብለህ ለነገሩ እውቅና በመስጠት መጀመር ተገቢ ነው። ከዚያም ችግሩ የሚያስከትለውን መዘዝ ማገናዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት በዚሁ ባህሪህ ስንት ግንኙነቶች ተበላሹ፣ ስንት ሥራ ተበላሸ?፣ ስንት ሰውን ጎዳን? ስንቱን አሳመምን? የሚለውን ማሰላሰል እና በቀላሉ ሊያልፉ በሚችሉ ነገሮች የማያልፉ ጠባሳዎችን እንዳሳደርን ማስተዋል ተገቢ ነው።

ይሄንን ካስተዋልን በኋላም ችግሮቹ ሲመጡ ልንሰጥ ስለሚገባው ምላሽ መዘጋጀት፤ ነገሩ ከቁጥጥራችን ውጭ እንዳይሆን ቆም ብሎ ማሰብ እና ማገናዘብም ጠቃሚ ነው። ያደቆነ ሰይጣን… የሚባለውን ተረትም በመተው፤ ያደቆነን ሰይጣን እንቢኝ ልቀቀኝ አልፈልግህም ብሎ መታገል እና በየግዜው ለምናመጣቸው ለውጦች እውቅና እየሰጠን ከትላንት ተሽለን ለነገ ደግሞ የላቅን ለመሆን ራሳችን ላይ መሥራት ይገባናል።

ስሜትን የመቆጣጠር ችሎታ የድክመት ምልክት ሳይሆን ጥልቅ ጥንካሬ መሆኑን ማገናዘብና ማስተዋልም ይገባል። በስሜት ቁጥር የተሻልን ለመሆን የምንችለውን ሁሉ ማድረግም ለነገ የማይተው ዛሬ ሊታረም የሚገባ መሆኑንም ማገናዘብ ያስፈልጋል። የከፋ እና የባሰ ነገርም ካለ የሥነልቦና ባለሙያ ማማከር ይበጃል።

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ለመምህራኖች እና ለሠራተኞች የስሜት ቁጥር ሥልጠናዎች በቅድሚያ መስጠት አለባቸው። የሚቀጥሯቸው መምህራን ለሚያስተምሯቸው ተማሪዎች አርአያ መሆን እንዲችሉ የመማር ማስተማር ሥራውም እንዲቃና ፕሮግራሞች በማዘጋጀት ስልጠና መስጠት አስፈላጊ ነው።

ለምሳሌ በፈረንጆቹ 2001 በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በኢሞሽናል ኢንተለጀንስ ስልጠና ላይ የተሳተፉ መምህራን ጭንቀትን መቋቋም እና ግጭቶችን የመቆጣጠር አቅማቸው 20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ለማወቅ ተችሏል። እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና አስተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን የተማሪዎችን አጠቃላይ የአካዳሚክ እውቀት እና ሥነምግባርን የሚያሳድግ በመሆኑ ሊለመድ ይገባል እላለሁ። ለዛሬው አበቃሁ።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You