
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የባዮሜካኒክስ ማዕከል ለማቋቋም በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ። አካዳሚው አስረኛውን ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባዔ ትናንት በሃዋሳ ባካሄደበት ወቅት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አንበሳው እንየው ባደረጉት ንግግር እንደጠቆሙት፣ የባዮሜካኒክስ ማዕከሉ ስፖርተኞችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመመርመር እና የአካል እንቅስቃሴያቸውን ለማሻሻል ወሳኝ ነው። ይህም በስፖርት የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል፣ የአፈጻጸም ደረጃን ለማሳደግ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመረዳት ያስችላል ብለዋል። ይህንን ታሳቢ በማድረግም አካዳሚው በ2017 ዓ.ም የበጀት ዓመት የባዮሜካኒክስ ማዕከል የማቋቋም ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ የአካዳሚው የስፖርተኞች የማገገሚያ ማዕከል አዘጋጅቶ ማጠናቀቂያ ሂደት ላይ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ የጠቆሙ ሲሆን፣ የማገገሚያ ማዕከሉ መጠናቀቅ ለአትሌቶች እና ለሌሎች ታካሚዎች አስፈላጊውን የህክምና እና የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል። ይህም ጉዳት የደረሰባቸው ስፖርተኞች በፍጥነት ወደ ስፖርታቸው ወይም ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ እንደሚረዳ አብራርተዋል።
አቶ አንበሳው በንግግራቸው በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ አካዳሚው ያከናወናቸውን አበይት ጉዳዮች የጠቀሱ ሲሆን፣ ለአካዳሚው አስፈላጊ የሆኑ የላብራቶሪ መሣሪያዎችን እና የቁሳቁሶችን ግዢ በማከናወን፣ አስፈላጊ በሆኑ እና በተሟሉት ቁሳቁሶች በመጠቀም ምርመራዎች እና ሙከራዎችን መስጠት መቻሉን ገልፀዋል። የመሣሪያዎቹ እና የቁሳቁሶቹ መሟላት አካዳሚዎቹን ብቁ እና ውጤታማ ከማድረግ በተጨማሪ ለሌሎች በስፖርት መስክ ለተሰማሩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት የስልጠና እና የራስን የማብቂያ በማድረግ የተሻለ ሥራ በመሠራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እንደ አቶ አንበሳው ገለፃ፣ አካዳሚው የሚያደርገው የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በቴክኖሎጂ በማዘመን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል በ2015 ዓ.ም ያስመረቀውና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ የስፖርት ጆርናል (Ethiopian Journal of Sport Sience) ድረ-ገፅ በማበልፀግ፣ የሀገሪቱ የስፖርት ተመራማሪዎች እንዲጠቀሙበት አድርጓል። በዚህም የዘርፉ ተመራማሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
አካዳሚው በ2017 ዓ.ም ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንደኛው የጆርናል እውቅናን ከትምህርት ሚኒስቴር ለሶስት ዓመታት ማግኘቱን የጠቆሙት አቶ አንበሳው፣ ይህም እውቅና የጆርናሉን አካዳሚያዊ ጥራት እና ተቀባይነት የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ ለተመራማሪዎች ሥራዎቻቸውን ለማሳተም አስተማማኝ መድረክ ከመፍጠሩም ባሻገር የአካዳሚውን የምርምር አቅም እና ገጽታ ከፍ ያደርጋል ብለዋል።
አካዳሚው የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ሞዴልን አዘጋጅቶ ማጠናቀቁንም አቶ አንበሳው ገልፀዋል። ይህ ሞዴል ለሀገሪቱ የእግር ኳስ እድገት ወሳኝ የሆነ ሳይንሳዊ መሠረት የሚጥል ሲሆን የአሰልጣኞችን እና የተጫዋቾችን አፈጻጸም በማሻሻል የስፖርቱን ጥራት ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል። በተመሳሳይ አካዳሚው በ2016 ዓ.ም የ5000 ሜትር ሩጫ እና የ3ህ ሺ ሜትር መሰናክል ሩጫ የታለንት/ተሰጥኦ ልየታና የልማት ሥርዓትን ተቋማዊ ስታንዳርድ አዘጋጅቶ በማሳተም ማሰራጨቱ ይታወቃል፡፡ በዚህም የዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም አካዳሚው ሁለት ትልልቅ ሀገራዊ ጥናቶችን እና ማስፈፀሚያ ስልቶቹን በማጥናት ለሚመለከተው አካል ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ማስረከቡን አክለዋል። አካዳሚው ባለፉት ዓመታት አሳትሞ ያወጣቸውን የጥናት እና ምርምር ውጤቶች በስፖርቱ ዘርፍ መደርደሪያ ላይ ከመታየት ይልቅ፣ በስፖርቱ ዘርፍ ለውጥ እንዲመጣ በግብዓትነት እንዲጠቀሙበት ለማድረግ የሚመለከታቸውን ስለተግባራዊነቱ በክትትል እና ድጋፍ በማረጋገጥ፤ በስፖርቱ ዘርፍ የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት ስፖርት ከማንኛውም ልማት እኩል ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራበት፣ የተቀመጠውን የመንግሥት አቅጣጫ ውጤታማ እንዲሆን የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም የሚመለከታቸው የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ተገቢውን ትኩረት በመስጠትና አቅጣጫ በማስቀመጥ ሊረዱ እንደሚገባ አቶ አንበሳው አስገንዝበዋል።
ለአንድ ቀን በተካሄደው የጥናትና ምርምር ጉባዔ በተለያዩ ርዕሶች ከተጠኑ 13 ጥናቶች መካከል የተመረጡ 7 ጥናቶች ቀርበው፣ በጉባዔው በታደሙ ባለድርሻ አካላት የማስተካከያ ሃሳብና አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።
በቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም