በአፋር ክልል በ10 ወራት በሌማት ትሩፋት 324 ሚሊዮን ሊትር ወተት ተገኘ

ሰመራ፦ በአፋር ክልል በ10 ወራት የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ትግበራ 324 ሚሊዮን ሊትር ወተት መገኘቱን የክልሉ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም መሐመድ አሊ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ 86 በመቶ የክልሉ ማኅበረሰብ የኑሮ መሠረት እንስሳት ናቸው። በስታስቲክስ መረጃ መሠረት አሁን ላይ በክልሉ 16 ሚሊዮን 958 በላይ የእንስሳት ሀብት ይገኛል። የእንስሳቱ ሀብት በክልሉ ላለው ማኅበረሰብ በነፍስ ወከፍ ሲካፈል ከ40 እስከ ሃምሳ ይደርሳል። ይህን እምቅ የእንስሳት ሀብት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን በመለየት እና ስትራቴጂክ ፕላን በመቅረፅ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በእንስሳት መኖ አቅርቦት፣ በእንስሳት ጤና ጥበቃ አገልግሎት እና በዝርያ ማሻሻል ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ በበጀት ዓመቱ 5ሺህ ሄክታር መሬት የእንስሳት መኖ ለማልማት ታቅዶ ባለፉት 10 ወራት ብቻ 4ሺህ 800 ሄክታር መሬት ላይ የእንሰሳት መኖ ማምረት መቻሉን ጠቁመዋል ።

የእንስሳት ጤና ጥበቃ በሽታን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አመላክተዋል። በዘመቻ መልክ የቅድመ በሽታ መከላከል ክትባት ላይ በተሠራ ሥራ በክልሉ ካሉት ጠቅላላ እንስሳት ወደ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት መከተባቸውን ገልጸዋል።

በዝርያ ማሻሻል ላይም እንዲሁ የወተት እና የሥጋ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ሰፊ ሥራዎች እንደተሠሩ አስረድተዋል። የሌማት ትሩፋት ኢንሽየቲቭን መነሻ በማድረግ ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውንም አቶ ኢብራሂም አስታውቀዋል።

የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቩ ምርትን የሚያትረፈርፍ፤ ሰዎች ወተትን፣ እንቁላልን፣ ማርን፣ በአካባቢያቸው በሚገባ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል። በበጀት ዓመቱ ክልሉ በሌማት ትሩፋት 400 ሚሊዮን ሊትር የወተት ምርት ለማሳካት ማቀዱን አስታውሰው፤ በ10 ወራት ብቻ 324 ሚሊዮን ሊትር የወተት ምርት ማግኘቱን ገልጸዋል።

በአፋር ክልል ለሚገኙ ነባር የወተት ላሞች በሌማት ትሩፋቱ ተገቢውን እንክብካቤ በመስጠት እስከ 10 ሊትር ወተት መስጠት እንዲችሉ መደረጉንም ጠቁመው፤ በክልሉ የግመል፣ የላም፣ የፍየልና የበግ ወተት ምርት ላይ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ከተለመደው አሠራር ወጣ ባለ መንገድ፤ የወተት መንደሮችን በማቋቋም፣ በአንድ መንደር በላም ወተት እስከ 120 ቤተሰብ፣ በግመል 35 ቤተሰብ፣ በፍየል እስከ 50 ቤተሰብ፣ በማደራጀት ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በክልሉ ዶሮ የማርባት ልምድ ያልነበረ መሆኑን አውስተው፤ በዚህ ዓመት 38 ሺህ የሥጋ እና የእንቁላል ዶሮች እየረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከሚድሮክ 52ሺህ እናት ዶሮዎችን በመውሰድና ወጣቶችን በማደራጀት የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ አስረድተዋል። በተመሳሳይ በክልሉ ሰሜናዊ ዞን አካባቢ 800 ዘመናዊ የንብ ቀፎ ተዘጋጅቶ እየተሠራ እንዳለና 20 ወረዳዎች ላይ ዘመናዊ የማር ምርት በማምረት ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ገልጸዋል።

በእርሻ ቦታዎች፣ በኩሬ ውስጥ፣ የዶሮ ኩስና ሌሎች ተመጋጋቢ መኖዎችን በማቅረብ ዓሣን ለማምረት እየተሞከረ መሆኑንም ገልጸዋል። የዶሮ ኩስን ከበቆሎ ጋር በመፍጨት ለበሬ ማደለቢያነት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአፋር ክልል 4 ተፈጥሯዊ እና አራት ሰው ሠራሽ ሐይቆች እንዳሉ ጠቅሰው፤ በስምንት ወረዳዎች ላይ የዓሣ ምርት በስፋት እየተሠራ እንዳለ እና ወጣቶችን በማደራጀት በ8 ወረዳዎች ሁለት፣ ሁለት ዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎች በጠቅላላ 16 የሞተር ጀልባዎች የተሰጡ መሆኑን ኃላፊው አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል።

በበኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You