
ኢትዮጵያ የብዙ ስመ ጥር ግለሰቦች ሀገር መሆንዋ የታወቀ ቢሆንም ታሪካቸው በአግባቡ በወረቀት ላይ ተፅፎ የተመዘገበው የጥቂቶቹ ብቻ ነው። በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኙአቸው ዕድሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዕውቀት የቀሰሙ ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ እሠራርንና አስተሳሰብን በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መሰጠት የደረሱ ፋና ወጊ ምሁራን እንደ ነበሩ ታሪክ ይነግረናል።
ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደህንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልነበሩም። በውትድርና፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ኢትዮጵያውያን ብዙዎች ናቸው።
በሀገር ውስጥም ደምቀው የሚታዩ እና ሥራዎቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ሆኑ ኢትዮጵያውያንም በየዘርፉ ይገኛሉ። ዛሬም ባለውለታነታቸውን ለመዘከር የተነሳነው ዕውቁን የህክምና ባለሙያ ሀኪም ወርቅነህ እሸቴን ነው።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሀኪም የሆኑት ሀኪም ወርቅነህ በ 1857 ዓ/ም በጎንደር ከተማ ጎንደር አደባባይ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ተወለዱ። በወቅቱ በአጼ ቴዎድሮስ የመጨሻዎቹ የሥልጣን ዘመን ላይ በውስጥ ፖለቲካ ምክንያት በመቅደላ አምባ ለእስር የሚጋዙ በርካቶች ነበሩ።
በወቅቱ ሀኪም ወርቅነህ ገና የሦስት ዓመት ጨቅላ ሳሉ ከወላጆቻቸው ጋር በመቅደላ አምባ ለእስር በመደረጋቸው ምክንያት በ 1860 ዓ/ም የእንግሊዝ ጦር መቅደላን ሲይዝ በተፈጠረው እረብሻ የሞተው ሞቶ የተቀረው እግሬ አውጪኝ ሲል ከተገኙት ሕጻናት መካከል የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁና ሕጻን ወርቅነህ በእንግሊዝ ወታደሮች ተማርከው ከወራሪው ጦር ጋር ጉዞ ጀመሩ።
ከባሕር ወደብ ሲደርሱ ልኡል ዓለማየሁና ሕጻን ወርቅነህ ሊለያዩ ግድ ሆነ ሮበርት ናፔር ልዑል ዓለማየሁን ይዞ ወደ እንግሊዝ ሲያቀና ሕጻን ወርቅነህ ግን ከኮሌኔል ቻርለስ ቻምበርሊን ጋር በመሆን በወቅቱ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ወደ ነበረችው ሕንድ ተጓዙ። ሕጻን ወርቅነህ በሕንድ ሀገር ለአራት ዓመት እንደተቀመጡ አሳዳጊያቸው ቻርለስ በሞት ስለተለዩ ኮሎኔል ማርቲን የተባለው ሰው ተቀብሎ ከአንድ የሚሽን ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርት እንዲቀጥሉ አደረገ።
ብሩህ አእምሮ የነበራቸው ወርቅነህ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፑጃብ በምትባለው ከተማ ተከታትለው ሲጨርሱ ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ ውጤት ስለነበራቸው በፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ለማጥናት ተመዘገቡ። ከዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ የሚነገርላቸው እኚህ ሰው የሕክምና ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀው ከተመረቁ በኋላ በዛው በህንድ ሀገር ረዳት የቀዶ ጥገና ሀኪም በመሆን ለሁለት ዓመት አገለገሉ።
በሕንድ የሁለት ዓመት አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ከፍተኛ የህክምና ትምህርት ለመከታተል እ.ኤ.አ በ1889 ዓ/ም ወደ እንግሊዝ አቀኑ። በዚያም በኤደንብራና በግላስኮው ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ተምረው በቀዶ ጥገና ሙያ በማዕረግ ተመረቁ። በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት የሀኪሞች ማሕበር ‘’የበቃ ጥቁር ሀኪም ‘’ የሚል ሽልማት የተበረከተላቸው ሀኪም ወርቅነህ እ.ኤ.አ በ1891 በሀኪምነት ተመድበው በወቅቱ በሕንድ ግዛት ስር ስትተዳደር ወደነበረችው ወደ በርማ ተላኩ።
በርማ እያሉ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርጉ ቆይተው በአጼ ምኒልክ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት በ1891 ዓ/ም በልጅነት የተለዪዋት ሀገራቸውን ለማየት በቁ።
ከቀሪ ዘመዶቻቸውም ጋር ተዋወቁ። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጡ ቆይተው በ1895 ዓ/ም እንደገና ወደ እንግሊዝ የተመለሱ ሲሆን ከዚያን ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሀገራቸው በመምጣት የተለያዩ ተግባራት ያከናወኑ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ በመጡበት ወቅት ከወ/ሮ ቀፀላወርቅ ቱሉ ጋር ትዳር በመመስረት ትዳራቸው ሰምሮ አምስት ወንዶችና ስምንት ሴት ልጆችን አፍርተዋል።
በሕንድ ሀገር በሕክምና ሙያቸው አንቱታን ያተረፉት እኚህ ሰው በተለይ በበርማ ከሕክምና ዳይሬክተርነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን በደረሱበት አገልግሎት ከፍተኛ ተወዳጅነትን እና ከበሬታን አትርፈዋል። በሕንድና በበርማ ለ32 ዓመታት አገልግሎት ከሰጡ በኋላ በ1919 ዓ/ም ጠቅልለው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
ሀኪም ወርቅነህ ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ የፍቅን እና አገልግሎት ማህበር የተባለ ድሃ ልጆችን እና ነጻ የወጡ ባሮችን በአዳሪነት እየተቀበለ የሚያስተምር የበጎ አድራጎት ድርጅት አቋቋሙ። በ1920 ስለ ጣና ጉዳይ ወደ አሜሪካ መንግሥት ተልከው መልዕክታቸውን በመልካም ሁኔታ ፈጽመው ተመልሰዋል።
በ1920 ዓ.ም በጥር ወር አዛዥ ተብለው በልዩ የቆመው ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆኑ። በ1922 ዓ.ም ወደ ህንድ አቅንተው ከቦምቤይ በአስተማሪነት እና በልዩ ልዩ ሙያ የሚያገለግሉ 21 ህንዳውያንን አምጥተው ኢትዮጵያ የነበሩባትን የባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍ ጥረት አድርገዋል።
ሀኪም ወርቅነህ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ፋሺስት ኢትዮጵያን እስከወረረበት ድረስ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሳትፈዋል። ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፍልውሃ ድርጅት አቋቁመዋል፣ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፣ የየካቲት 12 ሆስፒታል (የቀድሞው ቤተሳይዳ)፣ የጅማ መንገድ እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲቆሙ የበላይ ተቆጣጣሪ ሆነው ሠርተዋል።
በ1927 ዓ/ም በዓባይ ወንዝ ላይ ለሚገነባው ግድብ ርዳታ ለማሰባሰብ ወደ አሜሪካ የተጉዋዘውን ቡድን መርተዋል ፣ በ1920 ዓ/ም ለቆመው ዘመናዊ ፍርድቤት አዛዥ ተብለው በተሰጣቸው ሹመት በቅንነት አገልግለዋል፣ የጨርጨር አውራጃ ገዢ በመሆን የሠሩ ሲሆን ኢትዮጵያ በነበረባት የተማረ የሰው ኃይል እጥረት የተለያዩ ሙያ ያላቸው 21 ህንዳውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሠሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
በ 1928 በጄኔቫ የመንግሥታቱ ማሕበር የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው የተላኩት ሀኪም ወርቅነህ በዛው እያሉ ኢትዮጵያ በፋሺስት እጅ በመውደቋ ወደ እንግሊዝ በማቅናት የተለያዩ የዲፐሎማሳዊ ሥራዎችንና በማከናወን በፋሽስት ወረራ ምክንያት ጉዳት የደረሰባት ሀገራቸውን ለመርዳት የሚያስችሉ ዝግጅቶችን በማደራጀት በወቅቱ ከኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያ ወዳጆች ከፍተኛ ርዳታ እንዲገኝ ሚና ተጫውተዋል።
በጊዜው በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ሀኪም ወርቅነህ ለወቅቱ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሳሙኤል ሃዋር ፤ ብሪታኒያ ወረራውን እንድታወግዝና ለጦርነቱ ወጪ የሚሆን 20 ሚሊዮን ፓውንድ ብድር ለኢትዮጵያ እንድትሰጥ ጠይቀው ነበር ሆኖም ግን እንደታሰበው አልሆነም።
ሀኪም ወርቅነህ እሸቴ ከወራት ቆይታ በኋላ ምንም ምላሽ ባለማግኘታቸው ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ለጋዜጠኞች ይፋዊ መግለጫ ሰጡ። “ኢትዮጵያ ለጦርነቱ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ትሻለች ፤ ሀገሪቷ በሀብቷ ተጠቃሽ ስትሆን ፍላጎት ላላቸው ሀገራትና ግለሰቦች የነዳጅና የማዕድን ሀብቷን በሊዝ ለመስጠት ትስማማለች” በማለት ለጋዜጠኛች አሳወቁ። ከቀናት በኋም የብሪታንያ መንግሥት ለኢትዮጵያም ሆነ ለኢጣሊያ የጦር መሣሪያ ግዢ እንደማትሰጥ በግልጽ አሳወቀች።
ሀኪም ወርቅነህ በዚህ ትግላቸውና ድርጊታቸው የተቆጣው ፋሺስት አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩት ዮሴፍና ቢንያም የተባሉ ልጆቻቸውን ቢገሉባቸውም በዓላማቸው ፀንተው ኢትዮጵያ ከፋሺስት ነጻ እስክትወጣ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ከነጻነት በኋላ በ1934 ዓ/ም በ77 ዓመታቸው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ሀኪም ወርቅነህ በሽምግልና ዘመናቸው ሳይቀር በሙያቸውና በሌሎች አገልግሎቶች ሁሉ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሁለተኛው ሺህ ዓመት ካፈራቸው በጣት ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የስኬት ፈርጦች መካከል አንዱ ሆነው ይጠቀሳሉ። በሕይወት ዘመናቸው በገጠማቸው መከራ እና ችግር ሳይንበረከኩ፤ ለዓላማቸው ከግብ መድረስ ፀንቶ በመቆም አስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ የዜግነት ድርሻቸውን የተወጡ የሀገር ልጅ ናቸው።
የኢትዮጵያ የዘመናዊ ህክምና ታሪክ በተነሳ ቁጥር ባለታሪኩ የነበራቸው ጉልህ የፋና ወጊነት ሚና ይታወሳል። በቀሰሙት ዘመናዊ ትምህርት ታግዘው በሀገር ውስጥ በተጫወቱት የፋና ወጊነት ሚና፤ በተሰለፉባቸው የተግባር መስኮች በፈፀሟቸው አኩሪ ሥራዎቻቸው ሊዘከሩ ከሚገባቸው ጥቂት የስኬት ፈርጦቻችን መካከል አንዱ ሀኪም ወርቅነህ እሸቴ መሆናቸው ታሪካቸው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ሀኪም ወርቅነህ እሸቴ ወይም ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቻርልስ ደብልዩ ማርቲን በኢትዮጵያ ሁለተኛ ሺህ ዓመት ታሪክ ውስጥ በፋና ወጊነት ከሚጠቀሱ፤ በመልካም ሥራቸው ከሚወደሱ፤ በአርአያነቸውም ከሚታወሱ የሀገር ልጆች መካከል አንዱ ናቸው።
ከነገሥታት ወገን መወለድ ብቻውን ላቅ ያለ ዋጋና ክብር ያሰጥ በነበረበት በዚያ ቅርብ ዘመን ከምንም ተነስተው በጥረታቸውና በተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ስምና ሥራቸውን ለታሪክ አብቅተው፣ አርአያነታቸውን ለትውልድ አኑረው ያለፉ ስመ ጥር ኢትዮጵያዊ ናቸው፣ ሀኪም ወርቅነህ እሸቴ።
እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ በተወለዱ በ 88 ዓመታቸው ጥቅምት 11 ቀን 1945 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ቀብራቸውም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው በየካ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሲፈጸም ብዙ ኢትዮጵውያን በቦታው በመገኘት ሽኝት አድርገውላቸዋል።
እኛም በዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ እውቁን የህክምና ባለሙያ ሀኪም ወርቅነህ እሸቴን ላበረከቱት ዘመን ተሻጋሪ ሥራ አመሰገንን። ሰላም!
ይህንን ጽሁፍ ስናዘጋጅ የተለያዩ ድረ ገጾችን እና የጋዜጠኛ በልሁ ተረፈን የአቢሲኒያ ፈርጦች መጽሐሀፍን በምንጭነት ተጠቅመናል።
በእስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም