
– በበጀት ዓመቱ ከ11 ሺህ 600 በላይ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ተገነቡ
አዲስ አበባ፡-በኦሮሚያ ክልል በ2017 በጀት ዓመት እየተገነቡ ካሉ ፕሮጀክቶች 78 በመቶ የሚሆኑት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ገለጹ።
የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ የፕሮጀክቶች አፈጻጸምን አስመልክቶ ትናንትና በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በዘንድሮ ዓመት በክልሉ እየተገነቡ ካሉ 34 ሺህ 912 ፕሮጀክቶች 78 በመቶ የሚሆኑት ተጠናቀው ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
አጠቃላይ ከሚገነቡት ፕሮጀክቶች 27 ሺህ 280 ማለትም 78 በመቶ የሚሆኑት መጠናቀቃቸውን ገልጸው፤ በዘንድሮ ዓመት በክልሉ የሚገነቡት ፕሮጀክቶች ወጪ አጠቃላይ 244 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል። ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁ ፕሮጀክቶች ወጪ 212 ቢሊዮን ብር መሆኑን አመልክተዋል።
የፕሮጀክቶቹ ግንባታ 73 በመቶ የሚሆነው በኅብረተሰብ ተሳትፎ መገንባቱን አንስተው፤ በርካታ ግለሰቦች ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ በገንዘብ፣ በአቅም እና በተለያዩ ነገሮች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ከተገነቡት ፕሮጀክቶች 90 በመቶ ያህሉ ሰው ተኮር መሆናቸው ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ የመምህራን መኖሪያ ቤት፤ የቅድመ አንደኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ የአቅመ ደካሞች ቤቶች ግንባታ እና የእድሳት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።
አቶ አወሉ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ከ11 ሺህ 600 በላይ የመምህራን መኖሪያ ቤት፤ ከ4 ሺህ በላይ ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች እና 876 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል።
በክልሉ 140 ሺህ ያህል ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች የመገንባት እና የማደስ ሥራ የተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከሦስት ሺህ 400 በላይ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ካለፉት ዓመታት ትምህርት በመውሰድ በብዛትም ሆነ በጥራት እና በጊዜ ከማጠናቀቅ አንጻር የተሻለ ውጤት የታየባቸው መሆኑን በመግለጽ፤ ለዚህም ስኬት በክልሉ ከኅብረተሰቡ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተሠሩ ሥራዎች አንጻራዊ ሰላም መምጣት በመቻሉ ነው ብለዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የተቀመጠው የአምስት ዓመት ግብ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጠናቀቅ አመልክተው፤ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት አራት ዓመታት በክልሉ ከ71ሺህ 647 በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለሕዝብ ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል። በአራት ዓመታት በተሠሩ ፕሮጀክቶች ግንባታ የሕዝብ ተሳትፎ 70 ከመቶ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በበጀት ዓመቱ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በሁለት ምዕራፍ እንደሚመረቁ በመጠቆም፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ ሁለተኛው ምዕራፍ ከሐምሌ አጋማሽ እስከ ነሐሴ አጋማሽ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች በሰላም፤ በልማት ሥራዎች እና በመሠረተ ልማት ግንባታዎች አቅጣጫ ተይዞ ሲሠራ መቆየቱን አውስተው፤ በተሠሩ ሥራዎችም የተሻለ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ለተገኘው ውጤት የኅብረተሰቡ ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ምስጋና አቅርበዋል።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም