
የአንድ ምርጫ ስኬታማነት የሚለካው ከቅድመ ዝግጅቱ ጀምሮ ነው፡፡ በቂ ቅድመ ዝግጅት የተደረገበት ምርጫ ከወዲሁ ከግማሽ መንገድ በላይ በስኬት ጎዳና እንደተጓዘ ይቆጠራል፡፡
ምርጫ የዜጎችን መጻዒ ዕድል የሚወስን ጉዳይ በመሆኑ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በልዩ ትኩረት የሚከናወን ዓበይት ጉዳይ ነው፡፡ ምርጫ ውጤት ቢሆንም ለውጤቱ ማማር ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ያሉ ሂደቶች ወሳኝ ናቸው፡፡ ምርጫ ፍትሐዊ፤ ተዓማኒ እና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚከናወኑ ቅድመ ዝግጅቶች የማይተካ ሚና አላቸው፡፡
ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ከወዲሁ እንቅስቃሴ ጀምራለች፡፡ ሰሞኑንም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በዘመናዊ መልኩ ለማከናወን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አዲስ አሠራር ይፋ አድርጓል፡፡
በ2018 የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ነፃ፤ ፍትሐዊ፤ እና ሰላማዊ ለማድረግ እንዲሁም ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ ኢትዮጵያዊ በሙሉ እንዲሳተፍ ለማስቻል 50 በመቶ የሚሆነው መራጭ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመመዝገብ ዝግጅት ማጠናቀቁን አብስሯል፡፡ ምርጫ ቦርድ ወደ ሥራ የሚያስገባው ይሄው የመራጮች መመዝገቢያ ቴክኖሎጂ ዘመናዊ እና ከግለሰቦች ጣልቃ ገብነት የፀዳ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ተሰጥቶበታል፡፡
ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ስድስት ሀገር አቀፍ ምርጫዎችን ያካሄደች ሲሆን በሁሉም ምርጫዎች ሥራ ላይ የዋለው የመራጮች ምዝገባ ሂደት ካርድን እና መዝገብን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መራጮች ባሉበት ቦታ ሆነው የመራጭነት ካርድ እንዳይወስዱ ተግዳሮት ከመሆኑም በላይ የመዝገብ መጥፋት፤ መሰረዝ እና መደለዝ የመሳሰሉት ችግሮችን ሲያስከትል መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡
ይህ ተለምዷዊ አካሄድም የምርጫውን ፍትሐዊነት እና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ከማስገባቱም ባሻገር በጊዜ መጣበብ እና በቦታ ርቀት ምክንያት የሚጠበቀው ያህል ዜጋ እንዳይመዘገብ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡
እነዚህን ችግሮች በመገምገም ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተዓማኒነትን ያተረፈ እና በመራጮች ተሳትፎ የደመቀ እንዲሆን ከወዲሁ የተጀመሩ ተግባራት ተስፋ የሚሰጡ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ለመምረጥ ብቁ ከሆነው ዜጋ ውስጥ ግማሽ ያህሉን (50 በመቶ) በቴክኖሎጂ በመታገዝ መመዝገብ ከተቻለ እንደ ሀገርም ትልቅ ስኬት ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያ የተከተለችው የዲጂታል አብዮት በሁሉም ዘርፍ ውስጥ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተጨማሪ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
በተለይም ምርጫ የዲሞክራሲ ስኬት ትልቁ መለኪያ እንደመሆኑ መጠን በ2018 ዓ/ም የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በቴክኖሎጂ ታግዞ ወደ ተግባር መገባቱ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገው ጉዞ በእጅጉ የሚያግዝ ተግባር ነው፡፡
ምርጫ ቦርድ ራሱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማደራጀት እያደረገ ያለው ጥረትም ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ካለፉት ስድስት ምርጫዎች በሕዝብ ተሳትፎም ሆነ በተዓማኒነት ረገድ የተሻለ እንዲሆን በር የሚከፍት ነው፡፡
ቅድመ ምርጫ አብዛኛው የምርጫ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት ወቅት ሲሆን ይህም ከምርጫ ቀን በፊት ያለውን ጊዜያት ያጠቃልላል። በቅድመ ምርጫ ወቅት የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት፣ ማቀድ እና መተግበር፣ በጀት መመደብ፣ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅትና ምዝገባ፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፣ ሥልጠናና ምደባ፣ የምርጫ ክልል የማካለል ሥራዎች፣ የመራጮች ምዝገባ፣ ሥርዓተ ፆታ አሳታፊነት፣ የብዙኃን ማኅበራት አሳታፊነት፣ የሥነዜጋና መራጮች ትምህርት እና የመገናኛ ብዙኃን የሥራ እንቅስቃሴዎች በስፋትና በጥልቀት የሚከወኑበት ወቅት ነው።
እነዚህ የቅድመ ተግባራት ሥራዎችም ከወዲሁ እየተከናወኑ መሆኑም ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል፡፡ አብዛኞቹ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶችንም ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እየገመገመ እና እያፀደቀ መሆኑም በጥንካሬ የሚወሰድ ነው፡፡
በአጠቃላይ በመጪው ዓመት የሚካሄደው ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሐዊ፤ ሰላማዊ እና በሕዝብ ተሳትፎ የደመቀ እንዲሆን በበቂ ቅድመ ዝግጅቶች መደገፍ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድም ምርጫ ቦርድ የጀመራቸው ሥራዎች አበረታችና ተስፋ ሰጪ ስለሆኑ ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም