
አዲስ አበባ፡- በማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል ሲኖር የነበረው ወጣቱ ዓይነ ስውር በዳሶ መሐመድ ከማዕከሉ የተባረርኩት ትረብሻለህ፤ የአዕምሮም ሕመም አለብህ በሚል ሰበብ ይሁን እንጂ የአዕምሮ ሕመም የለብኝም ሲል ተናግሯል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ ተደራራቢ ችግር በመፍጠሩ ከማዕከሉ እንዲወጣ ተደርጓል ብሏል።
ወጣት በዳሶ፣ ከምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ከደረሰበት ጉዳት የተነሳ የማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከልን ተቀላቅሎ መኖር የጀመረ ነው። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በማዕከሉ ውስጥ ችግር እየፈጠርክ ነው በሚል ምክንያትና የአዕምሮ ሕመም አለብህ በሚል ሰበብ ወደ ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ እና ማገገሚያ ማዕከል እንድሔድ አድርገው ከማዕከሉ አስወጥተውኛል ሲል ቅሬታውን ያቀርባል።
በ2009 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ የሚናገረው በዳሶ፤ እንደ አጋጣሚ ወድቆ በደረሰበት አደጋ ለጉዳት ተዳርጎ መቆየቱን ተናግሯል።
በተደረገለት ድጋፍም በጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምናውን ተከታትሎ ጨርሷል። ከሆስፒታል በወጣበት ጊዜ የሚረዳው ሰው ስላልነበረው በረንዳ ላይ መኖር መጀመሩን አስታውሶ፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ወረዳ ዘጠኝ በመሄድ ሕክምና ሲከታተል መውጣቱንና የአካል ጉዳተኛና የሚረዳው ዘመድ ባለመኖሩ መጠለል የሚችልበት ስፍራ እንዲተባበሩት መጠየቁን አስረድቷል።
እርሱ እንዳለው፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ ጠያቂነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ችግሩን ተገንዝቦ በቢሮው ስር ወደሚተዳደረው ወደ ማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል እንዲገባ አድርጎታል። በማዕከሉም አንድ ዓመት ያህል ከተቀመጠ በኋላ አባረውታል። የመባረሩም ምክንያት ‹‹ትረብሻለህ፤ የአዕምሮ ታማሚ ነህ›› በሚል ሰበብ ነው ሲል ይገልጻል።
እኔን ካስወጡኝ በኋላ ማስወጣታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፈው ለከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ላኩ ያለው በዳሶ፣ ጉዳዩ ወደ ቢሮ መድረሱን በመስማቱም ወደዚያው አቅንቶ ጉዳዩ በትክክል ለማስረዳት ቢሞክርም ኃላፊዋ፣ ‹‹ሁለተኛ ወደ እኔ ቢሮ እንዳትመጣ›› ብላ አባረረችኝ ሲል ተናግሯል። እኔ የተባረርኩበትን ምክንያት ዘርዝሬ ሳልነግራትና ምክንያቱን ሳትረዳኝ ‹‹ሂድ›› አለችኝ ብሏል።
ይሁንና የቢሮው አማካሪ ዘንድ ገብቶ “እኔ በአሁኑ ጊዜ በረንዳ እያደርኩ ነው፤ ችግሬንና ምክንያቴን ሊረዳኝ የፈለገ ሰው የለም ብሎ በማስረዳቱ አማካሪው፣ ማዕከሉን ወደሚመሩት ሥራ አስኪያጅ ደውለው ስላለው ሁኔታ ካነጋገሯቸው በኋላ ‹‹ሂድና ግባ›› ስላሉት በቀጥታ ወደ ማዕከሉ መግባት መቻሉን አስረድቷል።
ይሁንና በማዕከሉ እየኖረ ሳለ ‹‹የአዕምሮ ሕመም አለብህና ወደ ጌርጌሴኖን ሔደህ መታከም አለብህ›› በሚል ከማዕከሉ አስወጥተውኛል ብሏል። አለመታመሙን ቢነግራቸውም ካልታመምክ ተመልሰህ ትመጣለህ፤ በዚያውም ለዓይንህ ሕክምናም ታገኛለህ” እንዳሉት ተናግሯል። ከጌርጌሴኖን ቆይታ በኋላ ወደ ነበረበት ማዕከል ለመመለስ ቢሞክርም፤ “አንዴ ከማዕከሉ የወጣ ሰው ተመልሶ ወደ ማዕከሉ መግባት አይችልም” የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ተናግሯል።
ወደ ማዕከሉ መግባት መከልከሉ ብቻ ሳይሆን ‹‹በፍጹም ያልፈጸምኩትን ነገር ፈጽመሃል መባሌ ሰላም ነስቶኛልና እውነታውን ፈጣሪ ያውጣልኝ እንጂ እኔ አቅም የለኝም›› ብሏል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የምርመራ ዘገባ ቡድን፤ ስለ ወጣቱ በዳሶ ጉዳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የማኅበራዊ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ቅጣውን በጠየቀበት ወቅት እርሳቸው እንዳሉት፤ በዳሶ ማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል ውስጥ ከሚኖሩ ተገልጋዮች መካከል አንዱ ነው፤ ተደጋጋሚ ችግሮችን ተገልጋዮች ላይ ሲያደርስ ቆይቷል። የሌሎችን ተገልጋዮች መብት ይጋፋል። በግቢው ውስጥ ያሉ ተማሪዎች እንዳያጠኑ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ገብቶ ይጮሃል። ሞግዚቶችን የምግብ ቤት ሠራተኞችን ያስቸግራል። እነዚህን ችግሮቹን ብዙ ጊዜ በምክር ለማለፍ ሞክረናል።
በእራሱ አንደበትም “እኔ የአዕምሮ በሽተኛ ነኝ” ሲሉ መደመጡን ኃላፊዋ ተናግረዋል።
በመረበሹ የተደረገው ነገር ቢኖር ወደ ጌርጌሴኖን መሔድ እንዲችል ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ወደ ጌርጌሴኖን እንዲሄድም የተደረገውም በማዕከሉ ያለው የጤና ባለሙያ በሰጠው ሙያዊ ሀሳብ መሠረት ነው። ይሁንና በዳሶ፣ ጌርጌሴኖን ከደረሰ በኋላ የአዕምሮ በሽተኛ አይደለሁም ሲል መናገሩን ጠቅሰው፤ ከዚያ ወጥቶ ጎዳና ላይ ሲወድቅ ዓይነ ስውር ነውና ወደ ማዕከሉ ይመለስ በሚል መመለሱን አውስተዋል።
ሆኖም በማዕከሉ የተወሰነ ከቆየ በኋላ ሴቶችን መተናኮል ይባስ ብሎ በዊልቸር የሚጠቀሙ ወጣት ሴቶችን እራሳቸውን እንኳ በአግባቡ ከጥቃት መከላከል የማይችሉትን ወደ መተናኮል መግባቱን ተናግረዋል።
ሌሎቹን ማዳን ስለሚያስፈልግ ከተቋሙ መውጣት አለበት ወደሚለው ውሳኔ መመጣቱ የተናገሩት ኃላፊዋ፣ የመጨረሻው ውሳኔ ከተቋሙ እንዲወጣ ማድረግ ነበርና እሱ ተግባራዊ ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፤ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያ ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አበራ ቅሬታ አቅራቢው በዳሶ መሐመድ በቢሮ በኩል ወደ ማዕከሉ በመምጣት እንደማንኛውም ማኅበራዊ ተጎጂ ተቀብለን ሲገለገል የቆየ ነው። በልጁ ላይ የምናያቸው በርካታ በጐ ያልሆኑ ሥነምግባር ድርጊቶች መኖራቸው አመልክተዋል። ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ እናቴን ጠይቄ ልምጣ ብሎ በመጀመሪያ ዙር አስፈቅዶ ሂዶ ጊዜውን ጨርሶ መጣና እናቴ በጣም ታማለችና ድጋሚ እነሱን ማስፈቀድ ስለማልችል አሁን አንተ ፍቀድልኝ ብሎ ጠይቋል። በጥያቄው መሠረት ተፈቅዶለታል። በዚህም ከሁለት ወር በላይ ቆይቶ ከመጣ በኋላ ከንግግሩ ጀምሮ ሁሉም ነገሩ ተለወጠ፤ የማጨስ፣ የመቃምና መጠጣት ባሕሪ አንፀባረቀ። ይሁን እንጂ ድርጊቱን በማየት በምክር አገልግሎት እንዲተው ድጋፍ ተደርጎለታል። ራሳቸውን መቋቋም በማይችሉ የማኅበራዊ ተጎጂዎች አረጋውያን ላይ ድብደባ ይፈጽማል። ሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት ለማድረስ ሙከራ አድርጓል ሲሉ ያብራራሉ።
በማኅበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያና ልማት ማዕከል ውስጥ የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች እንደገለጹት፤ በዳሶ የሚያሳያቸው አንዳንድ ድርጊቶቹ ከሱስ ጋር ተያይዞ የመጣ ይመስለናል፤ በዳሶ ሱስ አለበት። አንዳንዴ የሚታዩበት ምክንያቶች የጤነኛ አይደለም። አንዳንዴ ደግሞ የሚያወራው ትክክለኛ ነገር ነው። በእኛ እይታ የበዳሶ ሁኔታው ከሱስ ጋር በተያያዘ የሚመጣ የአዕምሮ ችግር ነው ብለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተሮች
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም