
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ገበሬ የሚለው ቃል ክብር ያገኘ ይመስላል። እንደ አያት እና ቦሌ አራብሳ ያሉ አካባቢዎች ስሄድ ‹‹እገሌ ገበሬው፣ እገሌ ገበሬዋ….›› የሚሉ በደማቁ የተጻፉ ማስታወቂያዎች አያለሁ። በፒያሳ ስድስት ኪሎ እና በሌሎች መሃል የአዲስ አበባ አካባቢዎችም ‹‹እገሌ ገበሬው፣ እገሌ ገበሬዋ…›› የሚሉ ያሸበረቁ ማስታወቂያዎች ይታያሉ። ገበሬ መሆን የሚያኮራ መሆኑን እንዲህ ማስተዋወቅ ዘመናዊነት ነው።
መከፋፈል እና ቡድን መፍጠር የሚወደው ኢሕአዴግ የገበሬን ሙያ አርሶ አደር እና አርብቶ አደር በሚል ለሁለት ከፍሎት ነበር። ልብ ብለን ካየነው ግን ገላጭ አልነበረም። ገበሬ ሁለቱንም አቅፎ የያዘ ነው። ለምሳሌ፤ ኢሕአዴግ ‹‹አርሶ አደር›› እያለ ይጠራቸው የነበሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አርብቶ አደርም ጭምር ነበሩ። ፍየል እያረቡ መሸጥ በሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተለመደ ነው። በሬ እያደለቡ መሸጥ በሰሜን እና በመሃል ኢትዮጵያ አካባቢዎች የተለመደ ነባር አሰራር ነው። ገበሬው ተጠቃሚ የሚሆነው ከእህል ብቻ ሳይሆን ከእንስሳትም እርባታ ጭምር ነበር፤ ሲጀመር አንድ ገበሬ እንደ ላም እና በሬ ያሉ የእንስሳት አይነቶች ከሌሉት አርሶ አደር ለመባልም አይበቃም።
ኢሕአዴግ አርብቶ አደር ይለው የነበረው የምሥራቁን የኢትዮጵያ ክፍል እና ታዳጊ የነበሩ ክልሎችን ነው። እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ግን በመስኖም ይሁን በሌሎች አጋጣሚዎች ከእንስሳት እርባታ ውጭ የሆነ የሥራ ዘርፍ አላቸው። ሲቀጥል እንስሳት ማርባት በራሱ ግብርና ነው፤ ስለዚህ ገበሬ የሚለው ቃል ይገልጻቸዋል።
እርግጥ ነው ገበሬ የሚለው ቃል በአዋጅ አልተከለከለም፤ ነውር እና ፀያፍ ቃል ነው አልተባለም፤ እንዳትናገሩት ተብሎም አልተከለከለም፤ ራሳቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትም ገበሬ ይሉ ነበሩ። ዳሩ ግን ትርክት በሂደት ይገነባልና ገበሬ የሚለው ቃል ክብር አጥቶ ነበር፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ መሰደቢያ ቃል ሲሆንም ሰምተናል። ያልሰለጠነ፣ ያልተማረ፣ ምንም የማያውቅ… ለማለት ‹‹ገበሬ!›› እያሉ የሚሳደቡ ሰዎች አሉ። እንዲህ የሚሉት ሰዎች የገበሬውን ያህል ሥነ ሥርዓት የሌላቸው ናቸው፤ አንዲት የፈጠራ ሥራ የሌላቸው ናቸው። ገበሬው ከአካባቢው ከሚገኝ ግብዓት የሚገጣጥመውን ሞፈር እና ቀንበር እንኳን መገጣጠም የማይችሉ ናቸው። ፈረንጅ የሠራውን የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ እንኳን የሚሰጠውን አገልግሎት ያህል በአግባቡ መጠቀም የማይችሉበት ናቸው።
ገበሬ የሚለው ቃል ለምን እንደተሸሸ ባይታወቅም ኢሕአዴግ ግን ‹‹የድሮ ሥርዓት…›› ብሎ በማሰብ ይመስለኛል። አንዳንድ ግምቶችም አሉ። ገበሬ በፊውዳሉ ዘመን ተጨቋኝ ነበር ተብሎ ይነገራል። ገበሬ የሚለውን ቃል ገባር ከሚለው ቃል ጋር የሚያገናኙት አሉ። በፊውዳሉ ዘመን ርቦ (ሩብ) እና ሲሶ (አንድ ሦስተኛ) የሚባል አሰራር ስለነበር በወቅቱ ገባር የነበረው አራሽ ገበሬ ተጨቋኝ ነው በሚል ነው ይባላል። ዳሩ ግን የፊውዳሉን ሥርዓት ያስወገደው የደርግ መንግሥት እንኳን ሳይቀር ገበሬ የሚለውን ቃል አልቀየረውም። ቀበሌ ገበሬ ማኅበር የሚባል ስመ ጥር አደረጃጀት እንደነበር በሕይወት ያሉ ሰዎች ያውቁታል። ስለዚህ ገበሬ የሚለው ቃል ልክ እንደ ሕክምና እና መምህርነት ሁሉ ራሱን የቻለ ተወዳጅ ሙያ ነው። መምህር ወይም ሐኪም ተጨቁኖ ነበር ተብሎ ስሙ አይቀየርም።
ገበሬ የሚለው ቃል በገበሬው ዘንድ በጣም ተወዳጅ ነው። ‹‹ገበሬው!›› ብሎ ስም ማውጣት የተለመደ ነው። ገበሬ የሚለው ቃል ፈሊጣዊ ትርጉም አለው። ታታሪ፣ የሥራ ሰው፣ ቀልጣፋ፣ ፈጣን…. እንደማለት ነው። ወታደር እና ገበሬ የሚሉት ቃላት ሙያን ከመግለጽ ባሻገር የአንድን ሰው ታታሪነት እና ቀልጣፋነት ለመግለጽ የሚያገለግሉ ናቸው። አንድን ጎበዝ ነጋዴ ‹‹ገበሬ እኮ ነው!›› ይሉታል። ሥራው ግብርና እንዳልሆነ ጠፍቷቸው አይደለም፤ ታታሪ ነው ማለታቸው ነው።
ገበሬ የሚለው ቃል በሕዝብ ዜማዎች፣ በሃይማኖታዊ መዝሙሮች እና በሥነ ቃሎች ውስጥ ሰፊ ቦታ አለው። አባቶች የደቦ ሥራ ላይ ሲመርቁ ‹‹በሬውን ከበሬ እርፉን ከገበሬ ያስማማላችሁ!›› ብለው ነው። ማንኛውም መንገደኛ ከገበሬ ቤት አሳድሩኝ ብሎ አድሮ ሲሄድ፣ ወይም የትኛውም ድግስ ላይ አባቶች ሲመርቁ ‹‹አራሽ ገበሬ ሳቢ በሬ ውሎ ይግባ›› ብለው ነው። ገበሬ የሚለው ቃል በዚህ ልክ ከገበሬው ጋር የተዋሃደ ነው።
ቃላት በተጨቆኑ ቁጥር ነውር ትርጉም ያላቸው ሊመስል ይችላል። በእርግጥ ቃል በራሱ ከአንድ ነገር ጋር ተፈጥሯዊ ግንኙነት የለውም፤ የሰዎች ማኅበራዊ ስምምነት ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በዘመን ሂደት ተቃራሚ ትርጉም ሊሰጠው ሁሉ ይችላል። ለምሳሌ፤ ዘበኛ ማለት በአሁኑ ጊዜ ብዙም የማይደፈር ቃል ነው፤ ጥበቃ በሚል ቃል ተተክቷል። ዘበኛ ብሎ መጥራት የጥበቃዎችን ክብር ዝቅ የሚያደርግ መስሎ የሚታየው ሰው ብዙ ነው፤ ምናልባትም ራሳቸው የጥበቃ ሰራተኞችም ቅር ይላቸው ይሆናል። ይህ ሁሉ የሆነው ግን በምንም ምክንያት ሳይሆን በአመለካከት መዛባት ነው።
አንድን ሙያ በስም ማሽሞንሞን የሚወዱ ለሥራ ክብር የሌላቸው ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ፤ ዘበኛ ማለትን እንደ ነውር ወይም የሰዎችን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው ብሎ የሚያምን ሰው ለዘበኝነት ሥራ ንቀት አለው ማለት ነው። አንድ ነገር አዕምሯችን አልቀበለው ሲል ነው ስሙን መቀየር የምንፈልገው። ምናልባትም ባለሙያዎችን የተንከባከብን መስሎን ነው። እንዳይሰማቸው በሚል መሆኑ ነው። ለምንድነው በሙያው የሚያፍረው? ስሙ ስለተቀየረስ ሙያው ላይ ምን ለውጥ ይኖረዋል? በነገራችን ላይ ዘበኛ የሚለው ቃል ቀደም ባለው ዘመን የተከበረ ነበር፤ ይሄውም ከንጉሱ ጠባቂ ክቡር ዘበኛ የመጣ በመሆኑ ይመስላል። ምናልባት ደርግ እና ኢሕአዴግ ቃሉን ጠልተውት ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ግን በተግባር እንጂ ቃል በመቀየር ሙያውን ማክበር አይቻልም!
ከዓመታት በፊት ማኅበራዊ ገጽ ላይ አንድ ሰው የጻፈው ትዝብት ትዝ አለኝ። በሰየው ትዝብት፤ ብዙ ሰዎች የቤት ሰራተኛቸውን ‹‹አጋዤ›› እያሉ ይጠራሉ፤ እንዳይሰማት ማድረጋቸው ነው። ሰውየው ቃል በቃል ሲናገር ‹‹አሽከሬ፣ ባሪያዬ…›› እያልሽ በሚገባ ምግብ በሰጠሻት፣ ትምህርት ባስተማርሻት… ነበር!›› ብሏል። ይሄ ማለት ለሰራተኛዋ የሚጠቅማት ሰዋዊ ነገሮችን ማድረግ እንጂ በስም ማቆለጳጰስ አይደለም ማለቱ ነው። ጸሐፊው የተናገራቸው ቃላት ከበድ ቢሉም (ለማጋነን ሲል ነው) ‹‹አጋዤ›› የሚለው ቃል የመጣው ‹‹ሠራተኛ›› የሚለውን ቃል ከመፍራት የተነሳ ነው። ይሄ ማለት እኮ የቤት ሰራተኝነትን እንደ ዝቅተኛ ሥራ የማየት አመለካከት አለ ማለት ነው። እንደዚያ ካለ ደግሞ ጉዳዩ ያለው ከድርጊቱ (ከሥራው) እንጂ ከስሙ ጋር አይደለም። መሰልጠን ማለት የትኛውንም ሥራ በሥራነቱ ማክበር እንጂ ቃሉን መቀያየር አይደለም። የቤት ሠራተኛ ቤት ውስጥ የምትሠራ፣ የቤት ውስጥ ሥራዎች የምትሠራ ማለት ነው። ልክ የምግብ ዝግጅት (ሼፍ) ሠራተኛ፣ የመንግሥት ሠራተኛ፣ የፋብሪካ ሠራተኛ…. እንደሚባለው ማለት ነው። እንዲያውም ‹‹አጋዤ›› የሚለው ልክ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ሥራ የሌላት፣ ሥራዋ ባለቤቷን ማገዝ ብቻ ሊመስል ይችላል።
ለማንኛውም እንዲህ አይነት የቃላት ቅያሪ ሀሳቦች የሚመጡት ለሙያው የተዛባ አመለካከት ከመያዝ ነው። እንዳይሰማቸው ስሙን እንቀይርላቸው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። ለምንድነው በማያሳፍር ሙያ የሚሰማቸው? መሰራት ያለበት የትኛውም ሙያ እና ሥራ ክቡር መሆኑ ላይ ነው።
ገበሬ በጣም የተከበረ ሙያ እና የተከበረ ቃል ነው። ይህ የተከበረ ቃል በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ‹‹እገሌ ገበሬው፣ እገሌ ገበሬዋ…›› ተብሎ ተጽፎ ማየት ይበል ያሰኛል።
በዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም