መረጋጋት የተሳነው የእንቁላል ገበያ

የእንቁላል ዋጋ አነጋጋሪ መሆኑ ቀጥሏል። በተለይ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ ዜጎች እንቁላል ለመግዛት ተቸግረዋል። ወላጆች ለልጆቻቸው እንቁላል መሠረታዊ ምግብ መሆኑን አስበው ለመግዛት ቢፈልጉም፤ እንዳልቻሉ እየተናገሩ ይገኛሉ።

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 አካባቢ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ከሚከናወኑባቸው ድንኳኖች አቅራቢያ እንቁላል ስትገዛ የነበረችው ወይዘሮ ራሔል አጥሌ እንደምትናገረው፤ የእንቁላል ተለዋዋጭ ዋጋ እና ጭማሪ አስደንጋጭ ሆኖባታል። በአቅሟ በየሳምንቱ አስር የሚደርሱ እንቁላሎችን ለልጆቿ ትገዛ ነበር። ዋጋው ከ12 ብር ወደ 17 ብር ሲያድግ ሰባት እንቁላሎችን መግዛት ጀመረች። አሁን ዋጋው እስከ 25 ብር በመድረሱ አራት እና አምስት እንቁላል ብቻ ለመግዛት ተገደደች።

ወይዘሮ ራሔል፤ ምንም እንኳ ሁለት ልጆች ቢኖሯትም በሁለት ቀን አንድ ቀን አንዳንድ እንቁላል ለመመገብ ተቸግራለች። ይህንን ተከትሎ እንደአማራጭ የወሰደችው እንቁላሉን በመቀቀል ለሁለት እያካፈለች መስጠት ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በአነስተኛ ብር ይሸጣል የሚል ወሬ መስማቷን ተናግራ፤ በየክፍለ ከተማው ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲኖር እና ዜጎች በተሻለ ዋጋ እንቁላል መግዛት እንዲችሉ መንግሥት ነጋዴዎች ላይ ርምጃ ሊወስድ ይገባል ትላለች።

በእዚሁ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 አካባቢ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ከሚከናወኑባቸው ድንኳኖች አቅራቢያ መሬት ላይ እንቁላል የምትሸጠዋ ምስጋና ሞገሴ በበኩሏ፤ በእዚሁ ዓመት እንቁላል ሲረክስ እስከ ስምንት ብር የሸጡበትን አጋጣሚ በማስታወስ፤ አሁን ደግሞ በውድ የገዙትን በርካሽ ለመሸጥ እንደሚቸገሩ ትናገራለች። ዋጋው አንድ ጊዜ እየጨመረ ሌላ ጊዜ እየቀነሰ የሚረጋጋበት አጋጣሚ መጥፋቱን ታብራራለች።

‹‹በ19 እና በ20 ብር ገዝተን፤ የሚሠበሩ እንቁላሎች አሉ። የትራንስፖርት ወጪ አለ። በእዛ ላይ ፀሐይ እና ዝናብ ላይ ቆመን ከአንድ እንቁላል አንድ ብር ማትረፍ ካልቻልን እኛስ እንዴት መኖር እንችላለን ?›› ስትል ትጠይቃለች።

እንደ ነጋዴዋ ምስጋና ገለጻ፤ የእንቁላል ዋጋ የጨመረው ከሚመጣበት ከአምራቾቹ ነው። አምራቾቹ ደግሞ ምክንያታቸው መኖ እና ግብር የሚል ነው። መኖ አቅራቢዎቹ ደግሞ ሌላ የራሳቸው ምክንያት ይኖራቸዋል። ከእዚህ ውጪ ነጋዴም ሆነ አምራች እንቁላል ከቆየ የመበላሸት ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሌላው ዕቃ ማከማቸት አይችልም። ዋጋው እየጨመረ ለገበያ የቀረበበት ምክንያት ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ሳቢያ ነው ብላለች።

ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ሲሆን፤ ለውጦችም እየታዩ ናቸው የሚሉት በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ ናቸው። እሳቸው እንደሚናገሩት፤ ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ቢሮው ሰፋፊ ሥራዎችን ይሠራል። በተለይ የገበያ ትስስር ላይ በመሥራት ለሸማቹ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አንፃር ብዙ ተግባራትን ያከናውናል። ከእዚህ ውስጥ አንደኛው የእንስሳት ተዋፅኦ ላይ አተኩሮ መሥራት ሲሆን፤ እንቁላል ዋነኛው ነው።

ይሁንና ሀገሪቷም ሆነች ከተማይቷ የነፃ ገበያ ፖሊሲን የሚከተሉ ናቸው። እንቁላል የድጎማ ምርት አይደለም። በመንግሥት እንደሚደጎሙ የስኳር ወይም የዘይት ምርቶች ውስን የገበያ ዋጋ ይኑረው ማለት አይቻልም። እንቁላል አንዱ ክፍለ ከተማ ላይ በጣም ቢረክስ፤ ሌላ ክፍለ ከተማ ላይ፤ ‹‹ከእዚህ በላይ መሸጥ አትችሉም›› ብሎ ማስገደድ አይቻልም።

የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ የእንቁላል ዋጋ በየጊዜው መጨመር እና አልፎ አልፎ መቀነስ የሚታየው ለምንድን ነው? በሚል ሸማቾች ለሚያነሱት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በዘርፉ በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ተመስርቶ ከዶሮ አርቢዎች ጋር ለመነጋገር ባደረጉት ጥረት ዋነኛ ምክንያት ሆኖ የቀረበው የመኖ ጉዳይ ነው። ይህ የሆነበት የራሱ ምክንያት ቢኖርም፤ ለእንቁላል መወደድ ዋነኛው ምክንያት መኖ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም ይላሉ።

ቢሮው ባካሔደው የማጣራት ሥራ፤ በእንቁላል ገበያ ላይ የምርት ዋጋ መዋዠቅ የሚከሰትበት ዋነኛው ምክንያት የፋብሪካ ምርት የሆነው የዶሮ መኖ ላይ የዋጋ ልዩነት በመፈጠሩ ነው። የመኖ ዋጋ በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት ታይቶበታል።

መኖ እንደዋነኛ ምክንያት የተወሰደው በኪሎም ሆነ በኩንታል ዋጋው በእጥፍ መጨመሩን ተከትሎ ነው። የዶሮ መኖ ደግሞ የፋብሪካ ምርት በመሆኑ፤ ከመኖ አምራቾች ጋር በዋናነት የሚሠራው የኢንዱስትሪ ቢሮ መሆኑን ያስረዳሉ። መኖ በምክንያትነት በመቅረቡ የኢንዱስትሪ ቢሮ ይህንን እንደሚመለከተው አንድ አካል ችግሩን ለመፍታት ጥረት እንዲያደርግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል ይላሉ።

ሆኖም ንግድ ቢሮ አምራቾችንም ለማነጋገር መሞከሩን በመጠቆም፤ ይሁንና አምራቾቹ እንደሚያነሱት፤ ከውጪ የሚያስገቧቸው የዶሮ መኖ ማምረቻ ግብዓቶች ዋጋቸው ጨምሯል። በሀገር ውስጥ ግብዓት የሚመረቱ መኖዎችም የትራንስፖርት ዋጋ መጨመሩን እንደምክንያት የሚያነሱ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ዋናው ጉዳይ የአቅርቦት መጠን መብዛት ገበያውን እንደሚያረጋጋው አያጠያይቅም። በቂ ምርት ገበያው ላይ መገኘቱ አማራጭ የሚያሰፋ በመሆኑ፤ ሁሉም ቦታ ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ያስችላል የሚል እሳቤ ተይዟል። ይህን ተከትሎ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተመጣጣኝ ዋጋ እንቁላል እንዲሸጥ ቢሮው አምራቾችን እና ሌሎች ባለድርሻዎችን የማነጋገር እና ምርት እንዲለቁ እና ወደ ከተማ በስፋት እንዲገባ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው ይላሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በዋናነት ለንግድ ቦታዎች ምቹ ሁኔታ የመፍጠር እና አምራች እና ነጋዴዎችን የማስተሳሰር ሥራ ተሠርቷል። እንዲሁም ዋጋ ማረጋጋት ቢያንስ የቅዳሜ እና የእሁድ ገበያዎች ላይ በቂ ምርት እንዲኖር ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋርም ወጣ ብሎ እየተነጋገረ የትስስር ሥራ ሠርቷል። በተጨማሪ ከእንቁላል ጋር ተያይዞ የከተማ አስተዳደሩ የሌማት ትሩፋትን ተከትሎ ሰፋፊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

በከተማዋ የምርት እጥረት እንዳይኖር፣ ከኦሮሚያ ክልል ከሸገር አካባቢዎች እና ከሌሎችም ክልሎች ምርት ወደ ከተማዋ እንዲገባ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ይገኛል። በተጨማሪ እስከ ባህርዳር በመሄድ እዚያ የሚመረተውን እንቁላል ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት እየተሠራ ነው።

ይህ ሥራ ለእንቁላል ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ምርቶች የሚከናወን ሲሆን፤ ከሶማሌ እና አፋር ክልል እንዲሁም ከደቡብ ክልል አርባምንጭ አካባቢ የዋጋ ጥናት ተደርጎ አትክልት እና ፍራፍሬን ጨምሮ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ያብራራሉ። ከሌማት ትሩፋት ጋር ተያይዞ ከአልሚዎች ጋር በመነጋገር በቂ ውይይት ተካሂዶ አነስተኛም ቢሆን የዋጋ ቅናሽ ተደርጓል ይላሉ።

በተሠራው ሥራ ገበያ ላይ በቂ እንቁላል መኖሩ እና የአቅርቦት ችግር እንደሌለ ታውቋል። ሆኖም ከፍተኛ ቅናሽ ባይኖረውም፤ እስከ 26 ብር ይሸጥ የነበረው የአንድ እንቁላል ዋጋ ወደ 20 እና 21 ብር ወርዷል። ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተሠራው ሥራ ዋጋው ቀንሷል ለማለት ያስደፍራል ብለዋል።

ሆኖም በአጠቃላይ የእንቁላል ዋጋ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ የሚለው፤ በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አሁን ደግሞ ፆም መግባቱን ተከትሎ የበለጠ ዋጋው የሚቀንስበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸው ይጠቁማሉ።

አያይዘውም ቢሮው ምርቶች ወደ ከተማዋ እንዲገቡ መሥራት ብቻ ሳይሆን፤ የሽያጭ ማዕከላት አካባቢ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ክትትል ከማድረግ ባሻገር በየክፍለ ከተማው የሽያጭ ማዕከላት እንዲዘጋጁ እና እንዲሠሩ ጥረት አድርጓል በማለት ቢሯቸው የሠራውን ሥራ አብራርተዋል።

ከግብር ጋር ተያይዞ የተነሳውን ሃሳብ በተመለከተ፤ ከገቢዎች ጋር ተያይዞ ሥራዎች የሚከናወኑት ቀደም ሲል እንደነበረው በሕግ እና በደንብ በመመራት ነው። ከእዚህ ውጪ ተጨማሪ ግብር ስለመጣ እንቁላል ጨመረ የሚል ምንም ዓይነት መረጃ የለም። ‹‹ግብር ከእንቁላል ዋጋ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። በእዚህ በኩል ያገኘነው ምንም ዓይነት መረጃ የለም። ይሁንና ከተጨማሪ እሴት ታክስም ሆነ ከግብር ጋር የተያያዘ ነገር ካለ ቢሮው ከገቢዎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነው።›› ብለዋል።

ቢሮው ሲሠራ የነበረው ከኢንዱስትሪ ቢሮ ጋር እንጂ የግብር ሰብሳቢ አካልን አላነጋገረም ሲሉ የተናገሩት አቶ አሸናፊ፤ ከግብር ጋር ተያይዞ የእንቁላል ዋጋ ጨምሯል የሚል መረጃ አለመኖሩን አመላክተዋል።

እሳቸው እንደሚናገሩት፤ እንቁላል በሀገር ውስጥ ሊመረት የሚችል ቀላል ምርት ነው። ከውጪ የሚገባ የውጪ ምንዛሪ ጉዳይ የሚያሳስበው ምርት አይደለም። ይሁንና በዋናነት በቂ ምርት እያለ አልፎ አልፎ አሻጥር የሚሠሩ ነጋዴዎች ይታያሉ። በአቋራጭ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚሞክሩ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው። ነጋዴው የሚሸጠው በቂ ምርት እያገኘ ከሆነ፤ ኅብረተሰቡን እያገለገለ ሥራውን ማካሔድ አለበት።

በተጨማሪ ከሌማት ትሩፋት ጋር ተያይዞ ምርቱ ላይ የአቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም ማድረግ ተችሏል። የመኖ ችግር ጉዳይን ለማቃለል ከኢንዱስትሪ ቢሮ ጋር በመወያየት የኢንዱስትሪ ቢሮውም ከአምራቾች ጋር ውይይት አካሂዷል። የመኖ ቅናሽም የተደረገ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪ ቢሮ አመቻችቶ መኖዎች ከሌሎች አካባቢዎች እንዲመጡ የተደረገበት ሁኔታ አለ። ይህ ተደማምሮ ውጤት እየመጣ መሆኑን ማረጋገጥ አይከብድም ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲሁም በከተማ ግብርናና በሌማት ትሩፋት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። በዋናነት ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ነው። በእዚህም ተጠቃሚ የሆኑ አካላት አሉ። በቂ ቦታ ያላቸው ሰዎች የራሳቸው ቦታ ላይ ቢሠሩ ጥሩ ነው ያሉት አቶ አሸናፊ፤ አምራች ሆኖ ትስስር ያላገኘ ማንኛውም አካል ቢሮውን ቢያገኝ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ሙሉ ፈቃደኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ከእንቁላል አንፃር የከተማ አስተዳደሩ የሌማት ትሩፋትን ተከትሎ ሰፋፊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በዋናነት ቢሯቸው ለንግድ ቦታዎች ምቹ ሁኔታ የመፍጠር እና አምራች እና ነጋዴዎችን የማስተሳሰር ሥራ መሥራቱን አስገንዝበዋል።

ጥቆማዎች ሲኖሩ ቢሮው 24 ሰዓት የሚሠራ ‹‹8588›› የስልክ መሥመር ላይ በመደወል መረጃ መስጠት ይቻላል ሲሉ የተናገሩት አቶ አሸናፊ፤ በእዚህ በኩል ያለውን ለመሥራት ቢሮው ፈቃደኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ዋናው ጉዳይ የአቅርቦት መጠን መብዛት ገበያውን እንደሚያረጋጋው አያጠያይቅም። በቂ ምርት ገበያው ላይ መገኘቱ አማራጭ የሚያሰፋ በመሆኑ፤ ሁሉም ቦታ ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ያስችላል የሚል እሳቤ ተይዟል። ይህን ተከትሎ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተመጣጣኝ ዋጋ እንቁላል እንዲሸጥ ቢሮው አምራቾችን እና ሌሎች ባለድርሻዎችን የማነጋገር እና ምርት እንዲለቁ እና ወደ ከተማ በስፋት እንዲገባ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው ይላሉ

በምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You