አዲስ አበባ፡- በሀሰተኛ የትምህርት ተቋም በማቋቋም በተጠረጠሩት እነ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ስምንት ተከሳሾች የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ወንጀል ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ምስክር እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጠ።
ተከሳሾቹ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ብርጋዴር ጀኔራል ጥጋቡ ፈትለ፣ ሻለቃ ገብረስላሴ ገብረጊዮርጊስ፣ ሻለቃ ፋሲል አበራ ሃይሉ፣ መቶ አለቃ ቶማስ ደረሰ፣ ወሰንየለህ ኃይለሚካኤል፣ ህድአት ወልደተንሳይ እና ዶክተር መኮንን ገብረሚካኤል ናቸው።
በችሎት የቀረቡት ተከሳሾች ትናንት ፍርድ ቤቱ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ አዝዞ እንደ ክሱ አቀራረብ ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም፤ ጥፋተኛም አይደለንም።›› ብለው ክደዋል።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ተከሳሾቹ መብታቸውን በመጠቀም ክደው በመከራከራቸው ማስረጃ አቅርቦ ለማሰማት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ችሎቱን ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ ዐቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ ምስክሮችን አቅርቦ እንዲያሰማ ለግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ተከሳሾቹ በአሜሪካንም ሆነ በኢትዮጵያ የማይታወቅና ከብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የትምህርትና ስልጠና አፈፃፀም መመሪያ ውጭ ‹‹ካሊፎርኒያ ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ›› በሚል ሀሰተኛ የትምህርት ተቋም
ማቋቋማቸውን ይጠቅሳል። ከኮርፖሬሽኑ የውል ስምምነት እንዲፈፀምና ክፍያው በውጭ ምንዛሬ እንዲሆን ማድረጋቸውንም አትቷል። ድርጊቱም በኢትዮጵያ መንግስት እንዳይታወቅ መምህራን በቱሪስት ቪዛ ከውጭ በማስመጣት ትምህርት ሳያስተምሩ ዲግሪ በመስጠት እንዲሁም በማስተማር ሽፋን የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ወደ ውጭ በማሸሽ ወንጀል መጠርጠራቸውንም አስረድቷል።
‹‹ካሊፎርኒያ ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ›› በታዳሽ ሀይልና በኦፕሬሽን ማኔጅመንት በማስተርስና በፒ.ኤች.ዲ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት ተከሳሾቹ በሶስት የተለያዩ የትምህርት መስኮች በአሜሪካንም ሆነ በኢትዮጵያ ዕውቅና ካልተሰጠው የፈጠራ ተቋም ትምህርት ለመስጠት አራት ውሎችን እንደተዋዋሉም ጠቁሟል።
ለሀሰተኛ ተቋሙ በድምሩ 3 ሚሊዮን 901 ሺ 140 ነጥብ 35 ዶላር (ሶስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ አንድ ሺ አንድ መቶ አርባ ዶላር) ወይም 75 ሚሊዮን 114 ሺ 030 ነጥብ 99 ብር (ሰባ አምስት ሚሊዮን አንድ መቶ አስራ አራት ሺ ብር) አሜሪካን ሀገር በተከፈቱ የሂሳብ ቁጥሮች ገቢ ማድረጋቸውን የተሻሻለው የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2011
በዘላለም ግዛው