– በቋሚነት ድጋፍ እየቀረበ መሆኑንም አመልክቷል
አዲስ አበባ:- በጌዲኦ ዞን ለተፈናቀሉና ለድርቅ ለተዳረጉ ተጎጂዎች መረጃው እንደደረሰ 48 ሰዓት ሳይሞላ እርዳታ ማድረስ መቻሉን የብሄራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። በቋሚነት ድጋፍ እየቀረበ መሆኑንም አመልክቷል።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ኮሚሽኑ አደጋ የትም ቦታ ሲከሰትና በወረዳ፤ በዞን በክልል ደረጃ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አልሳካ ብሎ መረጃው ሲደርሰው በ72 ሰዓታት ድጋፉን ያደርሳል። በጌዲኦ ለተከሰተው ችግር ግን ቦታው (ዲላ) ቅርብ በመሆኑ 48 ሰዓት ሳይሞላ እርዳታውን ማድረስ ተችሏል።
እስካሁን በጌዲኦ ዞን በቋሚነት 208 ሺ 275 ተረጂዎች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህም ቀደም ሲል ተፈናቅለው ከነበሩት 860 ሺ 56ት ተረጂዎች ከፊሎቹ ወደ ቀያቸው ሲሄዱ የቀሩት ናቸው። ተረጂዎቹ ቤታቸውም ከሄዱ በኋላ እስከ አንድ ዓመት እስኪያገግሙ ድጋፉ የሚቀርብላቸው ሲሆን ኮሚሽኑ ማስታገሻ ከሰጠ በኋላ በቋሚነት ድጋፍ እያቀረበ ያለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ህብረት ነው።
በተጨማሪም መጋቢት አንድ ቀን 2011 ዓ.ም ለኮሚሽኑ በተፃፈ ደብዳቤ የፀጥታ ስጋት ያለባቸው 54 ሺ 858 ዜጎች በአዲስ መልክ መፈናቀላቸውን ለኮሚሽኑ ደርሷል።
በጌዲኦ ዞን በገደብ ጎቲቺ 38 ሺ 252፣ በገደብ ከተማ 7ሺ263፣ በዲላ ዙሪያ (ጫጩ) 9ሺ343 ዜጎች በቋሚነት የሚረዳው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ህብረት ነው። እሱ እስከሚረከባቸው ድረስ ግን ብሄራዊ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን 200 ኩንታል ብስኩት 200 ኩንታል አተር ክክ 200 ኩንታል ዱቄት 2000 ሊትር ዘይት እንዲሁም ከተረጂዎች መካከል 35 በመቶው አጥቢ እናቶችና ነፍሰ ጡሮች ይሆናሉ ተብሎ ስለታሰበ 200 ኩንታል አልሚ ምግብ ተልኳል።
መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ 48 ሺ 357 ተረጂዎች እንደ አዲስ ተፈናቅለው የመጡ መሆናቸውን ከክልሉ መረጃ ደርሷል። በመሆኑም አስፈላጊው ድጋፍ የሚላክ ይሆናል። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ህብረት በቀጣይ በወር 8 ሺ 260 ኩንታል እህል 24 ሺ 700 ሊትር ዘይት 823 ኩንታል አልሚ ምግብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ደብዳቤ ተጽፏል፤እነሱም ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ ስምንት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የምግብ እህል ተረጂዎች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በግጭት የተነሳ የተፈናቀሉ ሲሆን ቀሪዎቹ በድርቅ የተጎዱ ናቸው። ለእነዚህ ተረጂዎች ድጋፍ የሚደረገው በሶስት የተለያዩ አካላት ሲሆን መንግሥት አምስት ሚሊዮን፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሱማሌ ክልል ያሉትን አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ፤ ቀሪዎቹን ደግሞ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ህብረት ይሸፍናል። በየአካባቢው ያሉ ዜጎች የሚደርጉትም ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2011
በ ራስወርቅ ሙሉጌታ