አዲስ አበባ የአገሪቱ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲናና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ እንዲሁም ከአንድ መቶ በላይ ዲፕሎማቶች መቀመጫ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከተማዋ በየጊዜው የምታስተናግዳቸው ትላልቅ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ አቀፍ ጉባኤዎችና ስብሰባዎች ከተማዋን የበርካታ የውጭ አገር ዜጎች መዳረሻ አድርጓታል፡፡ በዚህም የተነሳ የአዲስ አበባ ገጽታ በውጭው ማህበረሰብ ዘንድ የአገሪቱ ገጽታ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ይሁን እንጂ በከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዝርፊያና የሌብነት ተግባራት እየተበራከቱ መሆኑንና ይህም የከተማዋን ገጽታ ከማበላሸቱም ባሻገር ህብረተሰቡን ስጋት ላይ እየከተተው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከንቲባ ታከለ ኡማም በቅርብ በተካሄደ አንድ መድረክ ላይ በከተማችን ‹‹የሴቶች ቦርሳዎች ይነጠቃሉ፣ የሞባይል ስልኮች ይዘረፋሉ፣ የተለያዩ ወንጀሎች ይፈጸማሉ›› በማለት ሲገልፁ ተሰምቷል። በአዲስ አበባ እየተስተዋለ ያለው ችግር ሰፊና ውስብስብ ሲሆን በሕገወጥ ድርጊት ተሳትፈዋል የተባሉ በርካታ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውንና ለወንጀል ተግባር የሚያገለግሉ አራት ሺህ የሞተር ብስክሌቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ታውቋል፡፡
ወንጀሎቹ በጠራራ ፀሃይ ከሚፈጸሙባቸው ስፍራዎች ውስጥ አንዱ ደግሞ የባቡር ትራንስፖርት እንደሆነ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁት፤ “የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ኮርፖሬሽን” እና በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ቁልፍ ባለድርሻ አካል የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን እንደሚነግሩን በትራንስፖርት ዘርፉ የሚታዩ ወንጀሎች ቀላል አይደሉም፤ እንደውም እየሰፉ፣ እየረቀቁና እየተወሳሰቡ በመሄድ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባዘጋ ጀው የባለ-ድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ አሰፋ በቪዲዮ አስደግፈው ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደታየው የሚፈፀሙት ወንጀሎች የተለያዩ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ግን ለምን እንደሚፈጸሙ እንኳን ለመገመት የሚያዳግቱ ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል ወሳኝ የሆኑ ቁሶችን፤ ለምሳሌ እሳት ማጥፊያውን ካለበት ቦታ ገንጥሎ በማንሳት ሀዲዱ መሀል መጣል ይጠቀሳል፡፡
በወቅቱ በቀረበው የቪዲዮ ምስል ላይ ማየት እንደተቻለው በአካባቢው ላይ የሚገኝ ንብረትን መውሰድ፣ ኪስ ማውለቅ፣ ሞባይል ምንተፋ የመኪኖች ባቡር መስመር ውስጥ ዘሎ መግባት፣ የአንዳንድ ሰዎች መሀል ሀዲድ ላይ ተኝቶ መገኘት፣ የመኪኖች ዘሎ መግባትና ባቡሩን መግጨት፣ የአንዳንድ ተጓዦች ስርአት አልበኝነት፣ ከፖሊስ ጋር ግብ ግብ መግጠም፣ ወዘተ አይነት ወንጀሎች ይፈፀማሉ። አቶ ጥላሁን አላምረው የቀላል ባቡሩ የዘወትር ደንበኛ ናቸው። የስራ ቦታቸው ስታዲየም በመሆኑ ምክንያት ከሀያት ደርሶ መልስ በቀን ሁለቴ ከባቡሩ ጋር ግንኙነት አላቸው።
“ምን ገጠመኝ አለዎት” ስንል ጠይቀናቸው ነበር። አቶ ጥላሁን “የሞባይል ስርቆት” ካንድም ሁለት ሶስቴ ያጋጠማቸው ሲሆን “የጎረምሶች የርስ በርስ ድብድብ”ም አጋጥሟቸው እንደሚያውቅ ነግረውናል። ከሁሉም ከሁሉም የከፋውና የሁልጊዜ ክስተት የሆነው የወንጀል ተግባር ቲኬት ማጭበርበር ነው። የኮርፖሬሽኑ የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ እንደገለፁት፤ በተወሰኑ የትራንስፖርቱ ተጠቃሚዎች አካባቢ የስነምግባር ችግር የሚታይ ሲሆን ይህም የአጭር ርቀት ቲኬት እየቆረጡ ረጅም ርቀት በመጓዝ፤ ጭራሹንም ሳይቆርጡ በመግባት ኮርፖሬሽኑን ለኪሳራ እየዳረጉት ይገኛሉ፡፡
“የመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት የ”ሁለት፣ አራት እና ስድስት ብር” ታሪፍ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም በመንግስት ድጎማ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ተጠቃሚው ይህን የመንግስት ድጎማ በቅንነት ሊመለከተውና የሚጓዝበት ርቀት የሚጠይቀውን ትክክለኛ ታሪፍ ከፍሎ መጓዝ ይገባዋል።” ሲሉም አሳስበዋል።
ይህንኑ የኃላፊውን አስተያየት የሚጋራው ደግሞ የኮርፖሬሽኑ ባልደረባና በጉዞ ወቅት ቲኬት ተቆጣጣሪ የሆነው ወጣት (ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገ) ሲሆን ሳይቆርጡ እየገቡና ራሳቸው ወንጀለኛ ሆነው ሳለ ቲኬት ሲጠየቁ የሚሳደቡ ብዙዎች ናቸው። ከፖሊስ አቅም በላይ ለመሆን የሚያደርጉት ሙከራ ቀላል አይደለም፤ ለህግ ያለመገዛቱ ነገር፣ ከነሱም ብሶ ግልምጫቸው የሚገርም ነው። እንደ ተቆጣጣሪው አስተያየት “ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ በጣም አደገኛና አሳሳቢ ነው።”
በውይይት መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ እንደተናገሩት፤ ከሆነ ችግሩ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን አጥፊም ስለሆነ ባጭሩ ሊቀጭ ይገባዋል። ተወካዩ እንደዘረዘሩት በርካታ ጊዜያት ባቡር ተሳፋሪ ወንጀለኞችን መያዝ የተቻለ ሲሆን በፍተሻውም 32 ጥይቶች፣ 300 ሽጉጦች፣ ጩቤ፣ ሺሻ፣ ሀሺሽ ወዘተ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኮርፖሬሽንም ችግሩን ለመቆጣጠር ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡ ፡ በዚህም መሰረት ሰሞኑን 240 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች በቁጥጥር ስራው ላይ ማሰማራቱን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
በግርማ መንግሥቴ