አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737-8- ማክስ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በደረሰበት አደጋ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈው ኢትዮጵያውያን ስርዓተ ቀብር ትናንት በቅድስት ስላሴ ካቴድራልና ኮልፌ በሚገኘው የእስላም መካነ-መቃብር ተፈፀመ።
በስርዓተ ቀብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ ሌሎች የአየር መንገዱ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ የሟች ቤተሰቦች እና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኀዘንተኞች ተገኝተዋል።
ስርዓተ ቀብሩ በሁለት የመካነ-መቃብር ስፍራዎች የተከናወነ ሲሆን የ16ቱ አስከሬን በቅድስት ስላሴ ካቴድራል፤ የአንዱ ደግሞ ኮልፌ በሚገኘው የእስላም መካነ-መቃብር ተፈፅሟል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በስርዓተ-ቀብሩ ላይ ተገኝተው ቃለ-ቡራኬ ያሰሙ ሲሆን የሌሎች ሃይማኖት አባቶችም ተገኝተው የኀዘኑ ተካፋይ ሆነዋል።
በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙ የኀዘኑ ተካፋዮች እንደገለጹት የደረሰው አደጋ እጅግ መራርና አስከፊ ከመሆኑም በላይ የሟቾች ሁኔታም እጅግ አሳዛኝ ነው። በስርዓተ-ቀብሩ ላይ ያገኘነውና ያነጋገርነው ወጣት ብሩክ እዝራ እንደገለጸልን ኀዘኑ የቤተሰቦቻቸውና የዘመድ አዝማድ ብቻ ሳይሆን የሀገር ኀዘን ነው። «እኔ እዚህ የመጣሁት ዘመድ ወይም የማውቀው ሰው ሞቶብኝ አይደለም። ሁኔታው እጅግ አሳዛኝ እና የሀገር ኀዘን ስለሆነ ነው፣ እግዚአብሄር ነብሳቸውን ይማር» ሲልም ተናግሯል።
በአደጋው 18 ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ 157 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 /2011 ዓ.ም
ግርማ መንግስቴ