አዲስ አበባ፡- መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም ምሽት ከአማራና ሌሎች ክልሎች በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንደገለጹት መደጋገፍ እና መረዳዳት ባህሉ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ሁሉም ዳር እስከ ዳር ሊረባረብ ይገባል፡፡
የፕሮግራሙ ዓላማ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ምክንያት በአማራ ክልል ውስጥ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሁሉንም አቅም አስተባብሮ በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ድጋፍ ማሰባሰብ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም ላይ በመመስረት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ኃላፊነትና አደራም ለመሸከም ነው ብለዋል፡፡ ስልጣኔ በገራው አስተሳሰብ እንኳን የሰው ልጅ ይቅርና በብዝሃ ህይወት ውስጥ የሚታቀፉ ፍጡራን ሳይቀር በገዛ ፈቃዳቸው ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወሩበት ሁነት እንጂ በግዳጅ የመኖርያ ቀያቸውን ለቀው የሚፈናቀሉበት ሂደት የለም ያሉት አቶ ደመቀ የኋላ ገመናችንም ጥቁር እንግዳን የማክበር ባህል የነበረን ህዝቦች እንደነበርን አንስተዋል፡፡
ዛሬ ግን ዕርስ በርስ የመደጋገፍ ባህላችን ውሉ ላልቶ አንዳችን ላንዳችን የመከባበር ባህላችን ደፍርሶ እንዲሁም የሰብዓዊነት ሚዛን የውሃ ልኩ ተጥሶ በየጊዜው ቁጥሩ የሚጨምር የተፈናቃይ ወገኖቻችንን ስናስብ እኛው አፈናቃይ፤ እኛው ተፈናቃይ መሆናችን አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡ እነዚህ ዛሬ ዕርዳታ የምናሰባስብላቸው ወገኖቻችን ይህንን ሁሉ መከራ የሚቀበሉበት በራሳችን ድክመትና ጉድለት ብቻ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩ ህዝብን ማዕከል አድርጎ በአብሮነትና በአስተዋይነት ቢያዝ ኖሮ እነዚህ ዜጎች እንደቀድሟቸው ትርፍ አምራች እንጂ ዕርዳታ ጠያቂዎች አይሆኑም ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት እኛ ዛሬ ገንዘባችንን የምናሰባስበው ወገናችንን ይበልጥ ለማበልፀግ፣ ስርዓታችንን ይበልጥ ለማዘመን ፤የተሻለ ህይወትና ምቹ የመኖርያ አካባቢ እንዲኖራቸው፤ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንዲጠቀሙና ሀብት እንዲካፈሉ ለማድረግ መሆን ሲገባው አለመታደል ሆኖ በተግባር የምናየው ድህነትን ለመካፈል ሆኗል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ወደ ከፍታ የሚወስዱ ብዙ ፀጋዎችና ዕድሎች እያሉ ወገን በወገኑ ተፈናቅሎ ወገን ለወገኑ ሲለምንለት ማየት ለአፈናቃዩም፤ ለተፈናቃዩም ትልቅ የልብ ስብራት ነው፡፡
ሌላው ዓለም ስልጣኔ ላይ ልቆ ለመሰልጠን በሚተጋበት ዘመን እና ድህነትን እንደፀጋ እየተካፈልን ዕድሜ ማራዘም አጥፍቶ እስኪያጠፋን መጠበቅም፣ መፍቀድም የለብንም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ሰዎች ነገን የተሻለ ለማድረግ ካልጣሩ፣ ኃላፊነት የማይሰማቸውም ከሆኑ፣ የስልጣኔን ብርሃንም ካላዩ፣ የራሳቸው ፍላጎት ተገዢ ይሆናሉም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የተፈጠረውን የለውጥና የነፃነት ድባብ በአግባቡ ልንጠብቀው፣ በተሟላ ሁኔታ በተግባር ልንተረጉመውና የተያዘውን እጅግ የሚያኮራና ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጉዞ ወደፊት የማራመድና የመዘመን አጀንዳችንን ጠበቅ አድርገን መያዝና መጓዝ ይጠበቅብናል ያሉት አቶ ደመቀ ለዚህም ሁሉንም አቅማችንን ወደ ልማትና ኢንቨስትመንት ማዞር አለብን ብለዋል፡፡
በአገራችን በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ አካባቢዎች አስከፊ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲያጋጥሙ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመን የፈታንበትን መንገድ በማጠናከር በሁሉም አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ወደ ዘላቂ ህይወታቸውና አምራች ቁመናቸው እንዲመለሱ መረባረብ ይጠበቅብናል ሲሉም አሳስብዋል፡፡ የአማራ ክልል ርስሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው አገራችን ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት የሆነችና አብሮ መኖርና መቻቻልን ለዓለም በተግባር ያስተማረች፤ የደማቅ ታሪክና የረቂቅ ጥበብ ባለቤት፣ የነፃነት ፋና ወጊ የጥቁር ህዝቦች ኩራት ብትሆንም የርስ በርስ አለመግባባትና ግጭት በተለያዩ አገራችን ክፍሎች እየተከሰቱ ህዝባችንን ለሞትና እንግልት እየዳረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በተለይ የዜጎች መፈናቀል ዘርንና ማንነትን መሰረት ያደረገ መሆኑ ለሃገሪቱ አደገኛ ቁርሾ፣ ለዜጎቿ የማያቋርጥ ስቃይን የሚያስከትልና የመሪዎችን ድክመት የሚያመላክት በመሆኑ ከወዲሁ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድን ይጠይቃል ያሉት ዶክተር አምባቸው መግባባት፣ መከባበር እና ፍቅር ካለ አገራችን ለኛ ብቻ ሳትሆን ለሌሎችም የምትበቃ ስለሆነች የአገራችን ህዝቦችም እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በቀጣይ እንዳይደገሙ ለማድረግ ተንኳሾችና አፈናቃዮችን በማጋለጥ ለዘላቂ መፍትሔው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ሙሉ መብታቸው ተጠብቆና መብታቸው ተከብሮ ከአማራ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በተለመደው መከባበርና መተሳሰብ አብሮ የመኖር ባህል ተጠብቆ እንዲኖር የክልላችን መንግሥት በቁርጠኝነት ይሠራልም ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ዶክተር አምባቸው እንደገለጹት አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ከምንም በላይ የዜጎች በተደጋጋሚ መፈናቀል፣ ከሞቀ ቤታቸውና ንብረታቸው እየተለዩ ለእንግልት መዳረግ፣ አምራች እጆቻቸው ለልመና መዘርጋታቸው፣ እጅግ አሰዛኝ ሁኔታን እየፈጠረ ነው፡፡
እንደ ዶክተር አምባቸው ገለጻ እንደሃገር በፍቅርና በመቻቻል ከመኖር አልፎ ተጋብቶና ተዛምዶ በመኖር የሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ መጠራጠርና አለመተማመን እንዲያመራ የሚገፋፉ ኃላፊነት የጎደላቸው ትንኮሳዎችና ፀብ አጫሪ ሰበካዎች ይደመጣሉ። በተግባርም ግጭት ሲከሰት፣ ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ንብረት ሲወድምና ክቡር የሰው ልጅ ህይወት ሲቀጠፍ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡
ይህ በፍጥነት ካልቆመና የመፈናቀል ፋይል ካልተዘጋ ለውጡን ማስቀጠልና ተስፋ ማለምለም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ይህ አጥፊ የመገፋፋት ምዕራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዘግቶ ዜጎች በሰላም እዲኖሩ ማስቻል ይገባል፡፡ በዕለቱ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰብ ሂደትም በአጠቃላይ ከ610 ሚሊየን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከፕሮግራሙ አዘጋጆች ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር