ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገር በሚጠበቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እውን መሆን ጉልህ ድርሻ ያላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ለሥራ ዝግጁ እየሆኑ ይገኛል። ሆኖም ፓርኮቹን ከመገንባትና አስመርቆ ለሥራ ክፍት ከማድረግ በተጓዳኝ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ አገር ውስጥ ማምረት እንደሚገባ ምሑራን ይገልጻሉ፡፡
አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያና የፌርፋክስ አፍሪካ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየመጡ ከሚገኙ ስኬቶች አንዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሰፊው ሥራ ላይ መዋል መጀመራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ እስከአሁን ለምረቃ ከበቁት ሰባት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኤክስፖርት ማድረግ ጀምሯል፤ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ሐዋሳን ጨምሮ በቅርቡ እየተከፈቱ ወደ ሥራ የገቡትም በርካታ የውጭ ባለሀብቶችን ስበዋል። በዚህ መልኩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተስፋፉ መሄድም ራሱን የቻለ ዓለምአቀፍ የኢንዱስትሪ መንደር መፍጠር ነው፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የገቡትም ሆኑ ወደፊት የሚገቡት በሚሠሩት ሥራ ስኬታማ እንዲሆኑና ቀጣይነት ያለው ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችሉ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን ማከናወን ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ አንደኛ፣ ችግሮች እንዳያጋጥሟቸው ቀድሞ መሥራትን፤ ሁለተኛም፣ ችግሮች ካጋጠሟቸው በኋላ በተቀላጠፈ መልኩ መፍትሔ የሚያስገኙ አሠራሮችን መዘርጋትና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ይፈልጋል፡፡
ይሄን ሃሳብ የሚጋሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባትና ተመርቀውም ወደሥራ መግባት ለኢኮኖሚ ሽግግሩ ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ የቻይናን ኢኮኖሚ ያሸጋገሩትና ማህበራዊ ለውጥም ያመጡት የኢንዱስሪ ፓርኮች እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመገንባትና መርቆም ለሥራ ዝግጁ ከማድረግ ባለፈ ኢንዱስትሪዎቹ የሚጠቀሟቸውን የጥሬ ዕቃዎች ግብዓት አገር ውስጥ ማምረት የሚቻልበት መንገድ መፍጠር ይገባል፡፡
ለምሳሌ፣ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ጥጡን፣ መስፊያ ክሩንም ሆነ ቁልፉን ከውጭ የሚያመጡት ከሆነ ከአገር ውስጥ የሚገኘው ሠራተኛው ብቻ ይሆናል፡፡ በተለይ ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ጥጥ ወሳኝ እንደመሆኑ ጥጥን በአገር ውስጥ ማምረት ብቻ ሳይሆን በምርምር ታግዞ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚቻልበትን ዕድል መፍጠር ይገባል፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በአመዛኙ በግብርና ምርቶች ላይ የተመሰረቱ እንደመሆናቸው ኢንዱስትሪዎቹ በገቢ የግብዓት ምርቶች ላይ እንዳይንጠለጠሉ የግብርናውን ዘርፍ ከተለመደው አካሄድ በማላቀቅና በማዘመን ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም ተገቢ ይሆናል፡፡ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን መጠቀምም ይገባል፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ ሊታረስ ከሚችለው መሬት ውስጥ 14 በመቶው ብቻ ነው እየታረሰ ያለው፤ በየዓመቱ 122 ቢሊዬን ሜትር ኪዩብ ውሃ ከሚያመነጩ የኢትዮጵያ ወንዞችም ለመስኖ መዋል የቻለው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ለምሳሌ፣ በሶማሌ ክልል ሰፊ የእርሻ መሬት ብቻ ሳይሆን ይሄን ሊያለሙ የሚችሉ ወንዞችም ይፈስሳሉ፡፡ እናም መንግሥት እነዚህን ሀብቶች እንዴት መጠቀም እና ይሄንን ማልማት የሚችሉ አካላትንም እንዴት ማምጣት እንደሚቻል በሚሠራበት ሂደት ላይ አተኩሮ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ሌሎች የፋብሪካ ምርቶችንም በአገር ውስጥ አቅም መሸፈን የሚቻልበት ዕድል ሊፈጠር ይገባል፡፡ ስኳር ፋብሪካዎችም ለምግብና ከረሜላ ፋብሪካዎች ስኳር በማቅረብ ትልቅ ሚና ስላላቸው የተጓተቱ የስኳር ፋብሪካዎችም በተመሳሳይ ፍጥነት ሊሠራባቸው ያስፈልጋል፡፡
ኢንቨስትመንቱን ከማበረታታት፣ በዘርፉ የተሰማሪ ባለድርሻዎችና የመንግሥት ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጡ፣ ክትትልም እንዲያደርጉ ማስቻል፤ እንዲሁም የደህንነት ስጋት የሌለበት ሰላማዊ እንቅስቃሴን መፍጠር በሚቻልበት ሂደት ላይም በትኩረት መሥራት ይገባል፡፡ ይሄም የአካባቢውን ህዝብ ጭምር ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ መሄድን ይጠይቃል፡፡
አቶ ዘመዴነህ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በሴክተር ተከፋፍለው የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች በመጀመሪያ እየተሠሩና ጥሩ እየሄዱ ነው፤ አሁን ደግሞ የአግሮ ፕሮሰሲንግና የመድሃኒት ፓርኮች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። ኢትዮጵያ ቡና፣ ሰሊጥና ሌሎችም የግብርና ምርቶች በጥሬው ወደ ውጭ ትልካለች። ለአብነት፣ ቡና በጥሬው በዓመት 800 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ኤክስፖርት ይደረጋል፤በእነዚህ ፓርኮች እሴት ሲጨመርበት ግን በዓመት ከሁለት እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ውጤት የሚገኘው ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚፈልጉትን ግብዓት በአገር ውስጥ አምርቶ ማቅረብ ሲቻል ነው። ኢትዮጵያም ከአፍሪካ ከፍተኛ ስንዴ አምራች አገር ብትሆንም ስንዴን ከውጭ ታስገባለች፤ በተመሳሳይ ሰፊ የእንስሳት ሀብት እያላት የቆዳና የስጋ ኢንዱስትሪዎች የግብዓት እጥረት እንዳለ ያነሳሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በኢንፖርት ግብዓት ላይ እንዳይንጠለጠሉ መሥራት፤ ግብርናውን በማዘመንና የበለጠ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታማነቱን ማሳደግ፤ ምርቶቹንም በጥራትና በብዛት ማቅረብ ይገባል። ለውጤቱ ዘላቂነትም ኢንዱስትሪዎቹን መሰረት ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወን ያስፈልጋል።
አቶ ዘመዴነህ እንደሚገልጹት፤ ይሄንን ሐላፊነት የሚወጣ በመንግሥት በኩል አንድ ጠንካራ ተቋም መፍጠር ይጠይቃል፡፡ ይህ ተቋም በአንድ በኩል ቃል ተገብቶላቸው የመጡበት እንዲፈጸምላቸው የሚደግፍ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ባለሀብቶቹ ቃል ገብተው የመጡበትን በሥራ ላይ እያዋሉ ስለመሆናቸው የሚከታተል መሆን አለበት፡፡ በተመሳሳይ እነዚህ ፓርኮች ቀጣይነት ያለው ስኬት እንዲያስመዘግቡ ለእነዚህ ፓርኮች የሚሆን የሰው ሐይል ስልጠናና የቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ ተግባርም ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት ይገባል፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው እንደ ሚሉት፤ ኢትዮጵያ እስከአሁን በአነስተኛ መሬት ላይ በሚከናወን ግብርና ላይ ቆይታለች። ይህ ሂደት ለዘላቂ ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም፤ ሰፋፊ እርሻ በሌለበት አንድ አገር ራሷን መቀለብ አትችልም፡፡ ለምሳሌ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ወደ 770 ሚሊዬን ዶላር ወጥቶ ስንዴ ተገዝቷል፡፡ በተመሳሳይ ህዝቡ የሚፈልገው የምግብ ዘይት በአገር ውስጥ እየተመረተ ያለ ቢሆንም፤ ሁሉም ነገር በአንዴ ተቀይሮ ፓልም ዘይት ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ መደረጉ ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ በደርግም የነበሩና ኢህአዴግም ፕራይቬታይዝ ያደረጋቸው ኢንዱስትሪዎችን በሙሉ ገድሏል፡፡
ይሄን መሰል አካሄድ መታረም ስለሚገባው፤ አሁንም ኢንዱስትሪዎችን ከመገንባትና ለሥራ ዝግጁ ከማድረግ ጎን ለጎን፤ ኢንዱስትሪዎቹ ተወዳዳሪነታቸውና ውጤታማነታቸው እን ዲጎለብት ከግብዓት ጀምሮ አሽጎ ለመላክ እስከሚያስችሉ ዕቃዎች ድረስ ያሉ ነገሮች ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። ይሄን ማድረግ ካልተቻለ ግን ኢንዱስትሪዎቹ ይቆማሉ ማለት ባይቻል እንኳን፤ በገቢ ምርት ላይ ስለሚንጠለጠሉ ውጤታማነታቸውና ተወዳዳሪነታቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ይህ ደግሞ የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ሽግግር የመፍጠር ሚናቸውን ይጎዳዋል። በመሆኑም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለሥራ ዝግጁ የማድረግ ሂደቱ ፋብሪካዎቹ በግብዓትነት የሚጠቀሟቸውን ጥሬ ዕቃዎች በተገቢው መልኩ ለማቅረብ የሚያስችሉ የአቅርቦት ሰንሰለቶች በአግባቡ ተፈትሸው ሊሠራባቸው ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 /2011 ዓ.ም
ወንድወሰን ሽመልስ