አዲስ አበባ፡- ጥር 20 ቀን 1971 ዓ.ም በአንዲት ምሽት በተገለጸላቸው ህልም ለ40 ዓመታት ዋሻ ሲቆፍሩ መኖራቸውን በሻሸመኔ ከተማ የሚኖሩት አቶ ገመዳ ባይሶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅ ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናገሩ፡፡
በተፈጥሮዬ መቀመጥ አልወድም፤ ሌት ከቀን እሠራለሁ የሚሉት አቶ ገመዳ ባይሶ፤ ሰዎች ሲመጡ ‹‹እውነት አንተ ይህን ዋሻ ቆፍረህ ነው?›› ብለው በመገረም ይጠይቁኛል ሲሉ የሰዎች አድናቆት ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ 22 ዓመት ሲሞላቸው ዋሻውን መቆፈር እንደጀመሩ አስታውሰው፤ ለተከታታይ 40 ዓመታት ዋሻውን ብቻቸውን ቆፍረዋል፡፡
አሁን አቅማቸው በመድከሙና በቤተሰብ ጫና የተነሳ ቁፋሮውን ማቆማቸውን ተናግረዋል፡፡ የዋሻው ባለቤትና ቆፋሪው አቶ ገመዳ ባይሶ የቆፈሩት ዋሻ ስያሜው ‹‹ደነባ ዋሻ›› የሚባል ሲሆን፤ በኦሮሚያ ካሉ ዋሻዎች በትልቅነቱ ሰባተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ አቶ ገመዳ ዋሻውን አሁን ያለበት ደረጃ ለማድርስ በርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ማለፋቸውንም አስታውሰው፤ ሃሳባቸውን ያልተረዱ ሰዎች «መሬቱን ማረስ ሲገባው ዋሻ እየቆፈረ ጊዜውን ያባክናል» እያሉ ከባለቤታቸው ጋር ሊያፋቷቸው ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
ቤተሰቦቻቸውም ‹‹የእርሻውን መሬት ሁሉ ዋሻ በዋሻ አድርገህ እኛ ምን እንብላ?፣ የቱን እንረስ?›› በማለት ከሰዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከሻሸመኔ ወደ ሐዋሳ በሚያመራው መንገድ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ‹‹ደነባ ዋሻ›› አርባ ዓመታት ቢደክሙበትም አሁንም የሚጠበቀውን ያህል ጎብኚዎች ስለማይመጡ በቂ ገቢ ሊያገኙ እንዳልቻሉ አቶ ገመዳ ይናገራሉ፡ ፡ የሻሸመኔ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮም ሆነ ኦሮሚያ ክልል መንግሥት ይህን ለትውልድ የሚተላለፍ ሥራዬን ዓይተው ቢያግዙኝ መልካም ነው ሲሉም ተማፅነዋል፡፡
አቶ ገመዳ፤ ሁለት ሚስቶች ያላቸው ሲሆን፤ ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው 50 ደርሰዋል። ዋሻው በአጠቃላይ ውስጣዊ ስፋቱ 200 ሜትር የሚሸፍን ሲሆን አልጋ፣ መኝታ ክፍሎች፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ እርቅ የሚከናወንባቸው ስፍራዎች፣ የአባ ገዳ መቀመጫዎች፣ መዝገብ ቤትና ሌሎች ክፍሎችን ያካተተ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ የአቶ ገመዳ ባይሶ ታሪክና አኗኗር ብሎም ስለ ዋሻው ሰፊ መረጃ በሌላ አዲስ ዘመን ቅዳሜ ዕትም በቅርቡ እናቀርባለን፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር