በአንድ የመዝናኛ ስፍራ የተሰባሰቡት ባልንጀሮች ከአንዱ ጓደኛቸው ሞባይል ባገኙት መረጃ በእጅጉ ተመስጠዋል።ይህ ከልብ የተማረኩበት ጉዳይ ከማስገረም አልፎ እያመራመራቸው ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ የተባለውን ጉዳይ ለመሞከር ጭምር ሳያስቡ አልቀሩም። ከአንዱ ወደ አንዱ እየተቀባበለ ዳር የደረሰው ሞባይል ለሁለተኛ ዙር ቅኝት እንደገና መሸጋገሩን ቀጥሏል።
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ከመሀላቸው አንደኛው ድምጹን ከፍ አድርጎ አስገራሚውን ማስታወቂያ መሰል መልዕክት ለሶስተኛ ጊዜ አነበበው። መረጃው «ለክቡራን ደንበኞቻችን »ሲል ሀሳቡን ይጀምራል።
« እርስዎ በብድር መልክ የሰጡት ገንዘብ ባለመመለሱ ምክንያት እያዘኑ ይሆን? እንግዲያውስ በፍጹም እንዳይከፉ…ለዚህ ችግር ምላሽ የሚሆን መፍትሄ በእጃችን ይገኛል» ይላል
ጉድ ፈላ! መላና መፍትሄ የተባለው ምን ይሆን? በእርግጥም እንደ ማስታወቂያው መፍትሄ ከተበጀ ብዙዎች ለችግራቸው መልስ ሊያገኙ ነው። የተወሰኑት ሰዎች ገንዘብ ሲበደሩና ሲመልሱ ስሜታቸው አንድ ሆኖ አያውቅም። ሲወስዱ እግር ላይ ወድቀው ፣አማላጅ ልከው፣ በእንባና በአሳዛኝ ገጽታ አሳምነው ነው። ሲመልሱ ደግሞ ተለምነው፣በተራቸው አማላጅና መልዕክተኛ ተልኮባቸው ጭምር ይሆናል።
ይህ የሚሆነው ደግሞ ስልካቸውን ካነሱ፣ አልያም መንገድ አሳብረው ካልተደበቁና ፊት ለፊት ለመነጋገር ጊዜና ፍላጎቱ ካላቸው ብቻ ይሆናል።በጣም የሚገርመው እንዲህ አይነቶቹ ተበዳሪዎች ቀድሞ የነበረው የማስተዛዘኛ ገጽታቸው አብሯቸው ያለመዝለቁ ነው። ብድሩን ከወሰዱና ጉዳያቸውን ከሞሉ በኋላ ብድሩ ለማግኘት ደጋግመው ደጋግመው የጠየቁትን ያህል በተራቸው ቢጠየቁ ውስጣቸው አይረበሽም።
የማስታወቂያ አስነጋሪዎቹ መልዕክት ለእንዲህ አይነቶቹ «በልቶ ካጆች» የተዘጋጀ መፍትሄ ይመስላል። «ለክቡራን ደንበኞቻችን ሲል ሀሳቡን መጀመሩም ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ብድር የማስመለስ ልምድ ስለመኖሩ አመላካች ያደርገዋል። ምን አልባትም አበዳሪዎች በቂ መረጃና ምስክር ካላቸው ደግሞ የተበደራቸውን ሰው ብሩን በአግባቡ ለማስመለስ ቀላል እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም። ለእነዚህ ብድር አስመላሽ ነን ባዮች ደግሞ ይህ አይነቱ እርሾ በእጅጉ ይጠቅማል።
ወዳጆቼ! እናንተም እንደእኔ ከብድር አስመላሾቹ ይህ አይነቱን እውነታ ገምታችሁ ከሆነ ተሳስታችኋል። መቼም ዘንድሮ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል አይታይ አይሰማ የለም።«ነጩን ጥቁር እናደርጋለን» ባዮች በርክተዋል። ፍጹም አይሞከሬ በሆኑ ጉዳዮች ጠልቀው «ተአምር እንፈጥራለን» የሚሉም በዝተዋል። የእነዚህ ብድር አስመላሽ ነን ባዮች ድርጊትም ከዚሁ የራቀ አይደለም።
ሰዎቹ የአንዳንዶች ስሜትና ችግር በእጅጉ ገብቷቸዋል። ይህን ማወቃቸው ደግሞ መላና መፍትሄ ለሚፈልጉት ሁሉ በቂ ምላሽ እንደሚሆን አልጠፋቸውም።በእነሱ የአሰራር ልማድ ገንዘብ አበድሮ ካልተመለሰለት ሰው ምንም አይነት ማስረጃን አይፈልጉም። ምስክር መኖር ያለመኖሩም ፈጽሞ አያስጨንቃቸውም። ብድሩን ለማስመለስ የሚያሻቸው ቢኖር የአበዳሪው ቃልና እማኝነት ብቻ ይሆናል።
በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ ይህ መሆኑ ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ሂደት የሚከወነው በመለኮታዊ ስጦታችንና በተሰጠን ጸጋ ላይ ነው የመባሉ ጉዳይ እንጂ። እንዲህ አድራጊዎቹ መፍትሄን ለሚሻው አበዳሪ ገንዘቡን የሚያስመልሱለት ማስረጃዎችን ተንተርሰውና በውሉ አጣርተው አይደለም። ተሰጥቶናል በሚሉት ችሎታና በተቸሩት መንፈሳዊ ጥበብ ተጠበው እንደመሆኑ በራሳቸው የሚያሳድሩት አመኔታ ጭምር የገዘፈ ይሆናል።
ይህ «እናውቃለን» ባይነታቸውም ከቤት ከጓዳቸው አውጥቶ ለአደባባይ ማስታወቂያ ሲያበቃቸው ከዚህ በስተጀርባ ስለሚያገኟቸው ደንበኞችና ስለሚቆጥሩት ረብጣ ገንዘብም ማለማቸው አይቀሬ ነው።ያበደሩትን ገንዘባቸው በአጭር ጊዜ ያላገኙ አንዳንዶችም በአቋራጭ ለመድረስና ከእነሱ እግር ስር ለመውደቅ ጊዜን አይፈጁም።
እንዲህ አይነቶቹ የዋሆች የቀደመው ችግራቸው ሳያንስ ለተጨማሪ ኪሳራ መዳረጋቸው በእርግጥም ያሳዝናል። ደጋግመው የመበደላቸው ልማድ ከእድለቢስነት ጎራ ቢያሰልፋቸውም የሚያስገርም አይሆንም።ሁሌም ቢሆን አርቆ አስተዋይነትን ማስቀደም ያልቻለ ሰው ደግሞ እንዲህ በጠራራ ጸሀይ አይኑ ተሸፍኖ መታለሉ አይቀርለትም። ለዚህ ድርጊት ግን ባለቤቱ ራሱ ግማሽ መንገድ ተጉዞ ድርሻን አበርክቷልና በሌሎች ብቻ መፍረዱ የሚያስኬድ አይሆንም ።
ወዳጆቼ! እንዲህ አይነቶቹ ሰዎች ገንዘብን ለማግኘት የሚጠቀሙበት ዘዴ በዚህ ብቻ አያበቃም።ለእኔ ደጋግሞ ያስገረመኝና ቆይቶም ከልብ ያሳቀኝ ጉዳይ ግን ለየት የሚል ነው። እነዚህ ልማደኞች በተለመደው ማስታወቂያ መሰል ልፈፋቸው ‹‹አይናችውን ጨፍኑ እናሞኛችሁም›› ይላሉ።
«ክቡራን ደንበኞቻችን እኛ ዘንድ ድንቅ የሚባል ግርማ ሞገስ በእጃችን ይገኛል። ማንኛውም ሰው ግርማ ሞገስን መላበስ ፈልጎ በራችንን ካንኳኳ ያሰበውን ልናደርግለት ተዘጋጅተናል»
በጣም ይገርማል! በእነዚህ ሰዎች አባባል ግርማ ሞገስን ማላበስ ማለት ያልታሰበን ሁሉ በቀላሉ እንደማስፈጸም ይቆጠራል። በእነሱ ጥበበኛ እጆች ሞገስን የተቀባ ሰው በየሄደበት ሁሉ ነገሮች ይሳኩለታል።ይህ የሚሆነው ደግሞ ከሌሎች የበለጠ እርሱ በተለየ ትኩረትና አክብሮት ከዓይን ስለሚገባ ነው። ከዓይን ለመግባቱ ዋንኛ ሚስጥርም የግርማ ሞገሱ መገኘትና በእጅጉ መቀባት ብቻ ይሆናል።
የእነዚህ ጥበበኛ ተብዬዎች ዕውቀት የደረሰው ደንበኛ ታዲያ ቀልበ ቢስ ፣ ቀትረ ቀላል፣ትከሻው መና ተብሎ አይፈረጅም። ከዚህ አስቀድሞ በእነዚህ ምልክቶች ቢታወቅ እንኳን ስያሜው ይፋቅለታል። በየሄድበት በየደረሰበት ስፍራ ሁሉ እሱን አክብረው ከመቀመጫቸው የሚነሱ ይበረክታሉ። በንግግሩ ተስበው ጆሯቸውን የሚሰጡትም ይበዛሉ።
ባለግርማ ሞገሱ ሰው ሁሌም ቢሆን ክብርና ዝናው የናኘ እንደሆነ ይቀጥላል። በጥበበኞቹ እጅ ዳግመኛ ታንጿልና የጠየቀውን ሁሉ አይከለከልም። ማንም ቢሆን የተናገረውን በአግባቡ ያዳምጥለታል። አክባሪዎቹና አድናቂዎቹም ያለዝናው ዝናን አላብሰው፣ በክብር ተቀብለው በክብር ይሸኙታል።
እንግዲህ ይህን ሁሉ በረከትና ሲሳይ «እናላብሳለን»የሚሉት ፈላስፎች ስለሚያደርጉት ውለታ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለመቀበል ወደ ኋላ የሚሉ አይሆኑም። «እናደርጋለን» ወይም «አድርገናል» ስላሉት ተአምራዊ ድርጊት ግን ማረጋገጫ ይሁን መተማመኛን እንደ ማሳያ አያስጨብጡም።
ወዳጆቼ! መቼም ዘንድሮ ስለገንዘብ ሲባል የማይታይ፣ የማይሰማ ጉድ አይኖርም። ሆኖም የጎመራ ፍሬ ሁሉ ጣፋጭ እንደማይሆን መገመት ደግሞ የግድ ይላል።ክፉውን ከደጉ ማመዛዘን የሚችለው ህሊናችንም እንዲህ አይነቱ ጉዳይ ሲገጥመው ቆም ብሎ ሊያስብና ሊያመዛዝን ይገባዋል።ለምን? ካሉ ደግሞ የብድርን ገንዘብ በቀላሉ ተቀብሎ መቁጠር እንደማይቻል ሁሉ ግርማ ሞገስንም እንደ ገበያ ካፖርት ገዝተው የሚደርቡት አይደለምና ከአጭበርባሪዎች ጠንቀቅ ማለት ይበጃል።
መልካምሥራ አፈወርቅ