የማህበረሰቡን ጤናና የአካባቢ ደህንነትን የሚያስጠብቁ 34 ደረጃዎች ጸደቁ

አዲስ አበባ፡- የማህብረሰቡን ጤናና የአካባቢ ደህንነትን የሚያስጠብቁ 34 አዲስና የተከለሱ ደረጃዎችን ማጽደቁን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ (ዶ/ር) ፤ የደረጃዎች መጽደቅን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት:: ኢንስቲትዩቱ በአምስት ዘርፎች 63 ደረጃዎችን አውጥቶ ለቦርዱ አቅርቧል:: ቦርዱም ከቀረቡለት 64 ደረጃዎች ውስጥ 34ቱን አጽድቋል ብለዋል።

በአካባቢ ጤናና ደህንነት ዘርፍ 10 አዲስና 9 የተከለሱ ዳረጃዎች ጽድቋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በግብርናና ምግብ ዘርፍ 9 አዲስና 6 የተከለሰሱ ደረጃዎችን ማጽደቁንም አመልክተዋል።

ከጸደቁ 34 ደረጃዎች ውስጥ 18 ደረጃዎች አስገዳጅ  ናቸው ያሉት መሰረት (ዶ/ር)፤ የጤና ተቋማትን የሚመለከቱ 3 አዲስ ፣ 9 የተከለሱና የአካባቢን ጽዳትና ንጽህና የሚያስጠብቁ ደግሞ 6 አዲስ አስገዳጅ ደረጃዎች እንደሚገኙበት አብራርተዋል።

የጸደቁ ደረጃዎች የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል፤ የአካባቢ ንጽህናንና ጤናን ለማስጠበቅና የንግድ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንዳላቸው አመልክተው፤ እነዚህ ደረጃዎች ተግባር ላይ እንዲውሉም ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

እነዚህ የፀደቁ ደረጃዎች ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት የፀደቁ እና ሥራ ላይ ከዋሉ ደረጃዎች በተጨማሪ የዝግጅት ሂደታቸው ተገምግሞ ያለፉ ከጥራት፣ ከሰውና ከእንስሳ ደህንነት፣ ከአካባቢ ጥበቃ እና ንግድን ከማቀላጠፍ አኳያ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ የታመኑ ናቸው ብለዋል::

በተለይ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪና የንግድ ተወዳዳሪነትን አቅም ለማጎልበት እንደሚረዱ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል::

ደረጃው የህብረተሰቡ ጤናና ደህንነት ከማስጠበቅ በተጨማሪ ክህሎትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው አመልክተው፤ የአካባቢ ጥበቃ ለማጠናከር እና የሸማቾች ጥቅም ለማስጠበቅ ፤ ተቆጣጣሪ አካላት ክትትል እና ድጋፍ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ሲሉ ገልፀዋል::

አምራች እና አስመጪዎች ደረጃዎቹ መኖራቸውን በመረዳት፤ በመጠቀም እና የምርቶቻቸውን ጥራት በማሻሻል እንዲሁም ጥራታቸውን ያሟሉ ሸቀጦች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ወይም ወደ ውጪ በመላክ ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::

ማህበረሰቡም በሚጠቀማቸው ምርቶች ላይ የደረጃ ምልክቶችን አይቶ በመጠቀም ረገድ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል::

በሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You