በጎደለ ነገር ላይ ከመብሰልሰል …

“ሊቀ ሕሩያን በላይ መኮንን በ2006 ዓ.ም “ጥቁሩ ቅመም” በሚል ርዕስ ለንባብ ካበቁት ልቦለድ መጽሃፍ የመታሰቢያነት ገጹ ላይ የሰፈረው ሃሳብ እኔነቴን አበጅቶታል” ይላል የዛሬ እንግዳዬ ማዕበል እንዳሻው፤ እኔም የትናንት ኑረቱን፣ የዛሬ ሕይወቱንና የነገ ሕልሙን ለማወቅ የነበረኝ ጉጉቴ አይሎ የተባለውን መጽሃፍ ካሮጌ ተራ በስንት መከራ አፈላልጌ በማግኘት እሱነቱን የሠራውን ፍሬ ነገር ጨልፌ አቋድሳችሁ ዘንድ እንካችሁ ብያለሁና በሰላ ምናብ በጠንካራ ሃሳብ ከልቦናችሁ ማኅደር እንድትከትቡት አደራ በማለት የብዕሬን ዳና ነፍሱን ይማርና በሰለሞን ተካልኝ ሙዚቃ ቃኘሁት።

“ቼ ብያለሁ ቼ ቼ፣

ሃሳብ ላይ ወጥቼ።

ሱ ብያለሁ ሱ ሱ፣

ሃሳብ ነው ፈረሱ።”

አንድ ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር ባለሁለት ፎቅ ቤት ቢኖረው መልካም ነው። በምድር ቤቱ ውስጥ ከወላጆቹ የወረሰውን ሃብትና ንብረት ያስቀምጥበታል። በአንደኛው ፎቅ ላይ እሱ ራሱ ይኖርበታል። በሁለተኛው ፎቅ ላይ እንግዳ ያሳርፍበታል። ይህም ምሳሌ ነው። በምድር ቤቱ የትናንት ታሪክና ማንነት፣ በአንደኛው ፎቅ የዛሬ ሕይወት፣ ሁለተኛው ፎቅ ደግሞ የነገው ተተኪ ትውልድ ነው። አንድም ቤቱ ዘመን ነው። በዘመን ቤት አሠራር ውስጥ ትናንት መሰረት ሲሆን ዛሬ ግርግዳ፣ ነገ ጣሪያ ነው፤ እናም ከልጅነት እስከ ዕውቀት ከውልደት እስካሁኗ ሕይወት ድረስ ያለውንና በውጣ ውረዶች የተፈተነውን የኑሮ ሂደቱን እያነሳን ቆይታ ልናደርግ ፈቃዱን ሰጥቶኝ ወግ መሰለቅ ጀምረናል።

በምስራቅ ሐረር ኮንቦልቻ ወረዳ መልካ ራፉ ከአባቱ አቶ እንዳሻው ጽጌና ከናቱ ከወይዘሮ አባይነሽ ደምሴ በወርሃ ሰኔ 1983 ዓ.ም ለቤቱ የመጨረሻ ልጅ የሆነው ማዕበል እንዳሻው ተወለደ። ቤተሰቦቹ ጎጇቸውን ያቆሙበት የፎቶ ቤት ሥራ ዛሬ ላለበት የኪነጥበብ ሕይወት እርሾ እንደሆነው ማዕበል ይናገራል። ከኒኮላስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ አዳማ ቴክኒክና ሞያ የማሽነሪ ቴክኖሎጂ ተማሪነት፣ ከልጅነት ኑረት እስከ ባቢሎናውያን መጽሃፍትነት ድረስ የተጓዘው መንገድ ልዝብ የመሆኑ ሚስጥር በንባብ የተቃኘ ልቦና፣ በመልካም እሴቶች የተገራ ሕሊናና በሰብአዊነት የቀና ሞራል የታጠቀ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ከሃሳብ ትሩፋት ከሕይወት መዛግብት የበረበርኳቸው ምዕራፎች ማዕበል ከክሪስቲ ብራውን ጋር ያወዳጁት ያህል ተሰምቶኛልና “ማይ ሌፍት ፉት [ግራ እግሬ”] ከተሰኘው መጽሃፉ የወግ ማሟሻ ይሆን ዘንድ ከብዙ በጥቂቱ ማሳያ አንቀጾችን እነሆ።

አየርላንዳዊ ደራሲና ሰአሊ ክሪስቲ ብራውን በልጅነት ጊዜው የደረሰበት ያካል ጉዳት የፈጠረበትን የተሳሳተ አመለካከት በሥነጥበብ ያረቀ ታላቅ ሰው ነው። ገና ሲወለድ ሴሬ ብራል ፓልሲ በተባለ ያንጎል በሽታ የተጠቃው ክሪስቲ ከግራ እግሩ ውጪ የተቀረው አካሉ መንቀሳቀስ ካለመቻሉ የተነሳ የአእምሮ እድገቱ እክል እንደገጠመውና መማር እንደማይችል ተደርጎ ተቆጥሮም ነበር፤ ነገር ግን ፈጣሪዋ ላይ እምነቷ ያልነጠፈ፣ በልጇ እምቅ ችሎታ ተስፋዋ ያልረገፈ እናቱ በፍቅርና በትግስት እየተንከባከበች ብታሳድገው የክሪስቲ ምትሃተኛ ግራ እግር መጻፍና መሳል ተምሮ የናቀውንና ያገለለውን የማኅበረሰብ ቀልብ ሰቅዞ ያዘ። ይህ ጥረቱም ኋላ ላይ ወደፊልም የተቀየረውን “ማይ ሌፍት ፉት [ግራ እግሬ”] የተሰኘ መጽሃፉን በመድረስ ለመላው ዓለም ከመግፋት ይልቅ ማቅረብን፣ ከማግለል ይልቅ ማቀፍን ሰብኮበታል።

ማዕበል እንዳሻውም እንዲሁ “ባቢሎናውያን” በሚል ርዕስ ባስነበበው መጽሃፉ ጥላቻን ለዘሩበትና ደባን ለሸረቡበት ሰዎች ተግሳጽ ነው የሰጠበት። ቴክኒክና ሞያ በማሽነሪ ቴክኖሎጂ የሁለት ዓመት ቆይታውን ጨርሶ ከአዳማ ወደ ሐረር በመመለስ ወላጆቹ በከፈቱት መዝናኛ ክበብ ካገለገለ በኋላ የዘወትር ሕልሙ ኢትዮጵያን መዞር ነውና ከቤተሰቡ ጋር ተማክሮ መንጃ ፍቃድ በማውጣት የተገዛለትን ምኒባስ መዘወር ጀመረ።

ከሹፍርና ሥራው ጎን ለጎን በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ትምህርቱን ለመቀጠል ሽቶ ኑሮውን አዳማ ያደረገው ማዕበል ሕይወት በከፊል ፈገግታ ተቀበለችው።

በወርሃ ሕዳር 2005 ዓ.ም የሕይወቱ ሁለተኛ ምዕራፍ መጀመሪያ የፈጣሪ ድንቅ ሥራ መታያ የሆነው ክስተት በነበረው ኢትዮጵያን የመዞር ሕልሙ በኩል የመከራ እጁን ሰደደ። የትምህርት ማስረጃውን ሰንዶ ወደ ዝዋይ በመጓዝ ላይ እንዳለ እጁን የፈታበት ምኒባስ ሶስት ጊዜ ተገለባብጦ ለከባድ ያካል ጉዳት ዳረገው። ከረጂነት ወደተረጂነት ያደረሰው የሕይወት ዛቢያ ሆስፒታል ውስጥ በተኛበት አጋጣሚ የሚሰማቸው ተስፋ አስቆራጭ ቃላት ከሁኔታው ይልቅ ይበልጡን አመሙት፤ ይሁን እንጂ የመጣበት ሂደትና አስተዳደግ ለችግሮች በቀላሉ እጅ እንዲሰጥ አላደረገውምና ሞትን የማሸነፍ ያህል የሚያስወድስ ገድል ፈጸመ። ድንገተኛ ክፍል ገብቶ ቀዶ ጥገናውን የሚሠሩ ዶክተሮች ሁኔታውን ሲታዘቡ በሰውኛ ሚዛን በቀቢጸ ተስፋ ፍርድ የተረዱትን ሃሳብ ለቤተሰቡ ተናገሩ። ቅንጣት ተስፋ አለ ቢባል እንኳን ከሰመመን ለመንቃት የሶስት ወር እድሜ እንደሚፈጅበትና ውሃ የሚያነሳ መላ ምታቸው በሕይወት የመትረፍ እድሉ ጠባብ በመሆኑ ግዚያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን እንዳያባክኑ የሚመክር ነበር፤ ማዕበል ግን ዘመድ አዝማዱ ፊቱ በንባ ርሶ ሃዘን ሲያቆራምተው ሰርጀሪ ከተሰራለት ጥቂት ሰዓታት በኋላ “ስልኬስ?” አለ ዙሪያ ገባውን ባይኑ እየቃኘ።

ባድራጎቱ ግር ተሰኝተው ሲመለከቱት በነርቭ መጎዳት የሠራ አካሉ ተቀይዶ መንቀሳቀስ ባይችልም እንደክሪስቲ ብራውን ሁሉ መጽናኛ ነበረውና ባውራ ጣቱ እየጠነቆለ ስልኩ ላይ የመጽሃፍ ውጥኑን ማስፈር ቻለ። ሃኪሞቹ ሲጨናነቅ በገዛ ፈቃዱ ሞቱን እያፋጠነው እንደሆነ ቢቆጡትም እሱ ግን “የሰው ልጅ የሚሞተው የሕሊናውን መንገድ ዳዋ ሲወርሰው ያምሮውን ሞረድ ድንቁርና ሲያዶለዱመው ነው” አለ ብሩህ ገጹ እያበራ። አንደኛው ዶክተር ፊቱን ከስክሶ በመቅረብ ከዚህ በኋላ እንዳሻው የሚሆንበት ሳይሆን እነሱ ባዘዙት መሰረት ሊኖር እንደሚገባ ቢገልጽለትም ማዕበል ፈገግ ብሎ “ከአንድ ሺህ ሰዎች መሃል አንዱ አለመቻልን ሊችል ይችላል የሚል አባባል አለ አይደል?” በማለት አዙሮ ጠየቀው። ዶክተሩም ባዎንታ ራሱን ነቀነቀ። ማዕበል ቀበል አድርጎ “እንግዲያውስ አንተ እድለኛ ነህ፤ ከነዚያ አንድ ሺህ ሰዎች መሃል አለመቻልን የቻለውን አንዱን እኔን አግኝተሃልና” አለው ካልጋው ለመነሳት የዛለ አካሉን እያስተባበረ። በከፍተኛ ቁጣ የረገፈ አካሉ ሳይጠና ራሴን እችላለሁ እንዳይል ቢያስጠነቅቀውም ማዕበል ግን የማለዳዋን ጮራ ማየት ናፍቆ ስለነበር ዊልቸር አስመጥቶ ወደውጭ ወጣ። በንዴት የጋለ የዶክተሩን ፊት እያስተዋለ “ግድ የለህም አትስጋ ዶክተር፤ በፈጣሪ ላይ ያለኝ እምነት የጸና ስለሆነ በቅርቡ ወደ አንድ ገዳም የግር ጉዞ እንደሚኖረን ተስፋ አድርግ” አለው ከጨረቃ በሚልቅ ብርሃን ጸዳሉ እየፈካ።

አንደበቱ ዲዳ ሆኖ መናገር የተሳነውን ጀርመናዊውን ዴሞስቴንን አስታውሶ ማዕበል በጥረቱ መግፋት እንዳለበት አመነ፤ ያሟረቱበት የሞራል ውድቀትና የሸበበው ተስፋ መቁረጥ ከላዩ ላይ ይገፈፍ ዘንድ። ዴሞስቴን ለሶስት ዓመታት ያህል ከሰው ተገልሎ በአፉ ጠጠር ይይዝና ቃላትን ለማውጣት ይለማመድ ነበር፤ ገደል ማሚቶም መልሶ ድምጹን እያስተጋባ ለውጡን ያሳየዋል፤ ይህ ጥረቱም ዓለም በአንደበተ ርቱእነቱ ተማርካ ሳትወድ በግዷ እዝነልቦናዋን ከፍታ አይነህሊናዋን ገልጣ አንቱታን ትቸረው ዘንድ እጅ አስነስቷታል።

ማዕበል እንዳሻው ዛሬም ድረስ የሚጎርሰው፣ የሚለብሰውና ምንም ነገር የሚያከናውነው በሰው ድጋፍ ቢሆንም በሚታዘዝለት ብቸኛ አውራ ጣቱ የሚጽፋቸው ያምሮ ውጤቶቹ እጹብ ድንቅ ከማስባልም በላይ ሥራዎቹን ለማንበብ ስግብግብ ያደርጋሉ። በኮሮና ምክንያት አዳማና አዲስ አበባ የነበረውን ቆይታ ወደሐረር ቤተሰቦቹ ጋር የመለሰው ማዕበል ከመጀመሪያው አካላዊ ጉዳት በበለጠ የገጠመው የከፋ የስነልቦና ችግር ከራሱ አልፎ የወላጆቹንም ህይወት መቀመቅ አወረደው፤ ይሁን እንጂ ማንነቱን ሳይሆን ምንነቱን በማስቀደም የመከራን ቀንበር ለጫኑባቸው ሰዎች “ባቢሎናውያን” በተሰኘው የብዕር ልጁ በኩል ይቅርታ እንዳደረገላቸው ሲገልጽ የኢትዮጵያ ሕዝብ እጁን ባፉ ጫነ።

በዘር ጉንፋን የታመሱ ጥቂት ሰዎች በፈጠሩት ግጭት የቤተሰቡ ሃብትና ንብረት መውደሙ ሳያንስ ከዊልቸር ተላቆ በራሱ ለመቆም የሚፍጨረጨረውን ማዕበልን ከቁማቸው በመጣል በወደቀበት ክፉኛ ሲደበድቡት ጥቂትም ቢሆን የተሻለው ጤናው አገርሽቶ ከበፊቱ ለባሰ ጥገኝነት ዳረገው፤ እሱ ግን አብሮነትን የሚንዱ እኩይ ተግባራትን በመገሰጽ፤ከትናንት ፈተና ይልቅ የዛሬን የነፍሱን ጥሪ አሻግሮ በማየት የደረሰበትን ጥላቻ ሽሮ ባሳየው የይቅርታ ልብ ብዙዎች እንዲማሩ ምሳሌ ሆነ።

ቤተሰቡ በሞላ ከሐረር ተፈናቅሎ ኑሮውን አዳማ ሲያደርግ ማዕበልን እንቅልፍ አልወስድህ አለውና መፍትሄ ፍለጋ ከራሱ ጋር መከረ። ለጋስ የነበሩት እጆች ዛሬ ላይ ተመጽዋች ሆነው ማየቱ እጅጉን ነክቶት መሪር ሃዘን እያነባ አዲስ አበባ በመምጣት በተለያዩ ሚዲያዎች በኩል ቤተሰቡ የደረሰበትን አደጋ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲገልጥ ቅን ልቦች አጽናኝ እጆች ተዘረጉላቸውና “እፎይ” አለ እስከመቼ ድረስ በእንዲህ ሁኔታ እንደሚቀጥሉ ባለማወቁ ሃሳብ እየገባው።

ለሕክምና በሚል የተላከለት ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑ ምን ማድረግ እንዳለበት ሲያወጣ ሲያወርድ “ባቢሎናውያን” ከአይነሕሊናው ተሳለና እሱን በማሳተም የኔ የሚለው ሥራ ለመጀመር ወሰነ። መጽሃፉ ታትሞ ገበያ ላይ በዋለበት ጊዜ ከሊቅ እስከደቂቅ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን አድናቆታቸውን በተግባር ገለጡለት። ውርጭና ንፋሱ ጸሃይና ዝናቡ ሳይበግረው መጽሃፉን ለመሸጥ መሃል መገናኛ ተቀምጦ ባገኘሁት ሰዓት ራሱን ለመቻልና ጠንካራ የሥራ ሞራል እንዳለው መታዘብ ችያለሁ። አሁን ላይ ለማስታወቂያ ሥራ የንግድ ፍቃድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሲሆን በሕትመቱ ዘርፍም “ኔፍሊማውያን” የተሰኘ ሁለተኛ መጽሃፍ ጨርሶ ለማሳተም በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ማዕበል እንዳሻውን አካል ጉዳተኝነቱ የፈጠረበት ተጽኖ እንዳለ ይነግረኝ ዘንድ በማሰብ በጠየኩት ወቅት ሁሉም ልብ ውስጥ የተስፋ ጮራን የሚፈነጥቅ ሃሳብ አቀበለኝ። አትኩሮቱን በጎደለው ነገር ላይ ጥዶ ከመብሰልሰል ይልቅ ባለው ጸጋ ላይ ተመስርቶ ነገውን እንደሚሠራ አጫወተኝ። መልካም ስብዕናን ከተላበሰው አስተዳደጉም በላይ በኪነጥበቡ ዓለም ውስጥ መሆኑም ለጥንካሬው አቅም እንደሆነው አያይዞ ገለጸልኝ። ትልቁ ጉዳት የመንፈስ መዛልና የሕሊና መሻከር ሲሆን ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ በሚፈጥረው አጋጣሚ የሚከሰቱ አካላዊ ጉዳቶች ግን በጠንካራ ሞራልና ዘመኑን በዋጁ ስልጡን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጉድለቱ ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም ጫናውን መቀነስ እንደሚቻል ባጽንዖት ይናገራል።

አካል ጉዳተኝነት መቼና እንዴት ሊመጣ እንደሚችል ስለማይታወቅ ከሁሉም ነገር አስቀድሞ በቂ ግንዛቤ በመውሰድ የሥነልቦና ዝግጁነት ሊለየን እንደማይገባ ከራሱ ገጠመኝ ተነስቶ ምክረ ሃሳቡን ለግሷል። ዛሬ ላይ ሆኖ ትናንት የቦረቀባቸውን መስኮች፣ እየሮጠ ያደገባቸውን ጋራ ሸንተረሮች ባየ ቁጥር እንቅስቃሴው መገደቡ ቅር ቢያሰኘውም ባለመቻል ውስጥ መቻልን ችሏልና ዙሪያውን ከሸበበው የማማረር መንፈስ ወጥቶ ልቡን በማጽናት ሕልሙን ከሚያቀነጭሩ ጎታች አመለካከቶች አርቆ የስኬቱን ሰንደቅ ዓላማ ከተራራው አናት በመስቀል ሕይወቱን ከመጠውለግ መታደግ ብቻ ሣይሆን በስነጽሁፉ ዘርፍም ስሙን ላይደበዝዝ አድምቆታል። መጽሃፉን እየዞረ በመሸጥ ላይ እንዳለ መጽሃፉን በመግዛት ከማበረታታት ይልቅ አልፎ አልፎ ርጋፊ ሳንቲም እየሰጡ የሥራ ሞራሉን የፈተኑትም እንዳሉ ሳይሸሽግ አጫውቶኛል፤ “ከዚህ መረዳት የምንችለው አንዳንድ ብኩን ሰዎች እነሱ ሙሉ አካል ሆነው ያልሠሩትን አንተ ሰርተኸው ሲያዩ ያሳነስካቸው መስሎ ስለሚሰማቸው ቀርበው ጽናትን ከመማር ይልቅ አለመቻልህንና አካል ጉዳተኝነትህን ሊነግሩህ ይፈልጋሉ፤ ስለሆነም የለመለመ ተስፋችን እንዳይከስም ሩቅ ሕልማችን በቅርብ አዳሪዎች እንዳይገታ ልንሸሻቸው ይገባል” በማለት እሳቢያዊ ሕጸጾችን አሳይቶናል።

እኔም በጽሁፌ ማብቂያ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወት መጽሃፍ በመሆኑ በውጫዊ ሽፋኑ መዝነን ከመራቅ ይልቅ ቀርበን የውስጣዊ ጸጋ ሀብቱን እናንብብ።

በሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You