እስራኤል በዌስት ባንክ ከፍተኛ ሰፈራ እያስፋፋች መሆኑን አስታወቀች

እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ በአስር ዓመታት ውስጥ ታላቅ የተባለውን ሰፈራ እያስፋፋች መሆኑን አስታወቀች። የእስራኤል ሚኒስትሮች 22 አዳዲስ የአይሁድ ሰፈራዎች እንዲመሠረቱ አጽድቀናል ብለዋል። ከባለሥልጣናቱ ፈቃድ ውጭ ከዚህ ቀደም የተገነቡ ሰፈሮች በእስራኤል ሕግ መሠረት ሕጋዊ ይሆናሉ። ሌሎቹ ሰፈራዎች ግን አዲስ እንደሚሆኑ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ እና የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች ገልጸዋል።

ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ቢሆንም እስራኤል ይህንን ባለመቀበል በኃይል በያዘችው የፍልስጤሟ ዌስት ባንክ አይሁዳውያንን እያሰፈረች ትገኛለች። ካትዝ ይህ ርምጃ “እስራኤልን አደጋ ላይ የሚጥለው የፍልስጤም በሀገርነት መመሥረትን ይከላከላል” ብለዋል። የፍልስጤም ፕሬዚዳንት ሁኔታውን “አደገኛ” ሲሉ ጠርተውታል።

የእስራኤል ጸረ-ሰፈራ ድርጅት የሆነው ዋችዶግ ፒስ ርምጃውን በ30 ዓመታት ከፍተኛው እንደሆነ ገልጾ፤ “ዌስትባንክን ግዛት እንደሚቀይረው እና ወረራውን የበለጠ ያጠናክረዋል” ብሏል። እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምስራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ። አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል እያደረገችውን ሰፈራ በዓለም አቀፉ ሕግ መሠረት ኅ ገወጥ ነው ሲል ይኮንናል። እስራኤል ግን ይህንን አትቀበልም። በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ከሶስት ዓመት ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ። የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል።

በዌስት ባንክ የእስራኤል መንግሥት ፖሊሲን የሚተገብረው የሲቪል አስተዳደር ከፍተኛ እቅድ ኮሚቴ ኃላፊዎች እና አክራሪ የሚባሉት ሁለቱ የእስራኤል ሚኒስትሮች እስራኤል ካትዝ እና ቤዛሌል ስሞትሪች ከሁለት ሳምንት በፊት በመንግሥት ጸድቋል ተብሎ የሚታመነውን የሰፈራ ውሳኔ በይፋ አረጋግጠዋል። የሲቪል አስተዳደሩን በበላይነት የሚቆጣጠሩት የቀኝ አክራሪው ፖለቲከኞች መግለጫ 22 አዳዲስ ሰፈራዎች ማጽደቃቸውን ጠቅሶ፣ “በሰሜናዊ ምዕራብ ባንክ፣ ሰማርያ ሰፈራውን እንደገና ማሳለጥ እና እንዲሁም በምስራቃዊ ግዛት በኩልም የእስራኤልን ግዛት ማጠናከር” ይላል።

አዳዲሶቹ ሰፈራዎች ትክክለኛ ቦታ ባይጠቀሱም ነገር ግን የተሰራጩ ካርታዎች የዌስት ባንክን ግዛት ሙሉ በሙሉ ሊነኩ እንደሚችሉ ነው። በአውሮፓውያኑ 2005 እስራኤል ወታደሮቿን እና ሰፋሪዎቿን ከጋዛ ስታስወጣ በተመሳሳይ ጊዜ በሰሜናዊ ዌስት ባንክ የሚገኙት ሆሜሽ እና ሳ ኑር ተመሳሳይ ርምጃ የተወሰደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሁለቱ ሚኒስትሮች እነዚህ ስፍራዎች “ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ” ተመልሰዋል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛው ፍርድ ቤት “እስራኤል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች መቀጠሏ ሕገወጥ ነው” ብሏል። ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በተጨማሪም የእስራኤል ሰፈራዎች “ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ የተቋቋሙ እና አሁንም እየጣሱ ያሉ ናቸው” እንዲሁም እስራኤል “ሰፋሪዎቿን በሙሉ ማስወጣት” አለባት የሚል ውሳኔን አስተላልፏል። ኔታንያሁ በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ “ሐሰተኛ ውሳኔ” እንዳስተላለፈና “የአይሁድ ሕዝብ በገዛ መሬታቸው ላይ ወራሪዎች አይደሉም” ማለታቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You