
በድሬዳዋ እየተካሄደ የሚገኘው 13ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና 4ኛው ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከዕድሜ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቅ አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ ታይቶበታል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለዚህ አሳሳቢ ችግር አንዱ ምክንያት ነው ተብሎ የታመነበትን የተወዳዳሪ ክለቦች፣ ክልሎችና ሌሎችም ተሳታፊዎች የዋንጫ ሽልማት ዘንድሮ እንዲቀር በማድረግ ጥሩ ርምጃ ወስዷል። ያም ሆኖ አንዳንድ ክለቦች (ከሽልማት አኳያ) ትርጉም ለሌለው ቻምፒዮናም በሕገ ወጥ መንገድ የማሠልጠኛ ተቋማትና የአካዳሚ ስፖርተኞችን ነጥቀው የራሳቸው ከማድረግ እንዳልተቆጠቡ ማየት ተችሏል።
ለሰባት ቀናት በሚካሄደው የወጣቶቹ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ገና በመጀመሪያዎቹ ቀናት አምስት አትሌቶች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለሌሎች ክለቦች ተወዳድረዋል ተብለው ክስ ቀርቦባቸዋል። ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ እንዲሁም የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አትሌቶችን አስኮብልለው በወጣቶች ቻምፒዮና አወዳድረዋል የተባሉ ሦስት ክለቦች ክስ ቀርቦባቸዋል። ሁለቱ አትሌቶች የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሕጋዊ ሠልጣኞች ሲሆኑ ሦስቱ የተንታ ማሠልጠኛ ማዕከል አትሌቶች መሆናቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተቋሙ እውቅና ውጪ ለሌላ ክለብ ሲወዳደሩ ያገኛቸውን ሁለት አትሌቶች በተመለከተ ባቀረበው ክስ መሠረት የውድድሩ የክስ ሰሚ ኮሚቴ ዝርዝር ጉዳዮችን ተመልክቶ ውሳኔ አሳልፏል። ኦግሉ አጅሉ እና አፒዮ አጉድ የተባሉት ሁለት ወጣት አትሌቶች የቮሊ ቦል ሠልጣኝ ሆነው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን የተቀላቀሉት በዚህ ዓመት ነው። ይሁን እንጂ በወጣቶቹ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሁለቱ አትሌቶች ኢትዮ ኤሌክትሪክን ወክለው በዝላይ ውድድር ሲሳተፉ መገኘታቸው አስገራሚ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሁለቱን አትሌቶች በተመለከተ ባቀረበው የተገቢነት ክስ ከተቋሙ መልቀቂያ እንዳልወሰዱና አሁንም ድረስ የአራት ዓመት ውል ያሠሩ ሠልጣኞቹ እንደሆኑ አሳውቋል። ለዚህም ከአካዳሚው የመጋቢትና የሚያዝያ ወር የኪስ ገንዘብ የተቀበሉበትን ሰነድ አቅርቧል። የክስ ሰሚ ኮሚቴውም አትሌቶቹ ያስመዘገቡት ውጤት እንዲሰረዝ/እንዲሸጋሸግና የአትሌቶቹ ተገቢነትም የአካዳሚው እንዲሆን ወስኗል።
በተመሳሳይ አትሌት አየለ ሰውነት፣ አትሌት ታከለ በሪሁን፣ አትሌት ባንቻየሁ ቢክስ በተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ያላቸው ሕጋዊ ውል ሳይጠናቀቅ በቻምፒዮናው ለፀደይ ባንክና ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (ኢኮስኮ) ተሰልፈው ተወዳድረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። የክስ ሰሚ ኮሚቴው የቀረቡለትን ሰነዶች ከመረመረ በኋላ አትሌት ታከለ በሪሁን የተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ አትሌት ሆኖ መመዝገቡን የሚያሳይ ሕጋዊ ሰነድ ባለመቅረቡ ከቀረበበት ክስ ነፃ እንዲሆን ተወስኗል። አትሌት ባንቻየሁ ቢክስን በተመለከተ የተንታ ማሠልጠኛ ማዕከልም ኢኮስኮም አትሌቷ “የእኛ ነች” ብለው ያቀረቡት ሰነድ የሁለቱም ትክክለኛና አጠራጣሪ አለመሆኑን ተከትሎ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ተጨማሪ ማስረጃ አስፈልጓል። በዚህም መሠረት ተጨማሪ ማስረጃዎች ቀርበው እስኪጣራ ድረስ በአትሌቷ የተገኘ ውጤት ለጊዜው እንዲያዝና የሌሎች አትሌቶች ውጤት ባገኙት ደረጃ መሠረት እንዲፀድቅ ተውኗል። አትሌት አየለ ሰውነትን በተመለከተ ግን ቅሬታ ባቀረበው ክለብ ሕጋዊ ውሉ አለመጠናቀቁ በመረጋገጡ የአትሌቱ ተገቢነት ለተንታ ማሠልጠኛ ማዕከል መሆኑ ተወስኗል። በቻምፒዮናው አትሌቱ ያስመዘገበው ውጤት ካለም እንዲሰረዝ ውሳኔ ተላልፏል።
ጉዳዩን በማስመልከት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የአትሌቶች ትምህርት እና ሥልጠና መሪ ሥራ አስፈፃሚ አሠልጣኝ ፍቃዱ ከበደ፣ ሠልጣኞቹ በ2017 ዓ.ም ተመዝግበው በአካዳሚው በሥልጠና ላይ የሚገኙ አትሌቶች መሆናቸውን በመግለፅ፣ ነገር ግን ከአካዳሚው አውቅና ውጪ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ለሌላ ክለብ ተወዳድረው ውጤት ቢያስመዘግቡም ለፌዴሬሽኑ የአግባብነት ክስ አቅርበው ሠልጣኞቹ ከአካዳሚው ጋር የገቡትን ውል፣ በ2017 ዓ.ም የተመዘገበቡበትን ሰነድ እና የመጋቢትና የሚያዚያ ወር የኪስ ገንዘብ የተከፈላቸውን ፔሮል በማስረጃነት በማቅረብ የአካዳሚው ክስ ተቀባይነት በማግኘቱ የአትሌቶቹ ውጤት መሠረዙን ከአካዳሚው የፌስ ቡክ ገፅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አሠልጣኝ ፍቃዱ አያይዘው ባስተላለፉት መልዕክትም፣ “አካዳሚው የሚሠራው ለሀገር ነው፤ ብዙ ወጪ አውጥቶ ከመላው ሀገሪቱ በብዙ ጥረትና ድካም ያመጣቸውን አትሌቶች ክለቦች በሕጋዊ መንገድ ጊዜውን ጠብቀው መውሰድ እየቻሉ ባልተለመደ መልኩ ለጊዜያዊ ጥቅም ተብሎ ታዳጊዎችን ማታለል ተገቢ አለመሆኑ ታውቆ መሰል ሠልጣኞችና ክለባት ካልተገባ ተግባር እንዲቆጠቡ” በማለት አሳስበዋል።
የአንድ ክለብም ይሁን የስፖርት አካዳሚና የወጣቶች ማሠልጠኛ ተቋማት ዋነኛ ግብና ዓላማ ትንንሽ ውጤት ከመሰብሰብ ይልቅ ለሀገር ተተኪና ውጤታማ አትሌቶችን ማፍራት ነው። ይህ እንደመርህ የስፖርት ቤተሰቡ የሚስማማበት ጉዳይ ነው። አንዳንድ ክለቦች ግን ይህን ስተው መታየታቸው በወጣቶቹ ቻምፒዮና ከእድሜ ማጭበርበር ቀጥሎ የታየ ሌላ ድራማ ሆኗል።
የተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛም ይሁን የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በተሻለ መንገድ ወጣቶችን የሚያሰለጥኑት ለሀገር ጥቅም ነው። ክለቦች የየራሳቸውን ተተኪዎች ኮትኩተው በማሳደግ ለሀገሪቱ አትሌቲክስ የበኩላቸውን ከማበርከት ይልቅ ሌሎች የለፉበትን ያውም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ማስኮብለል “መንጠቅ” እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም። ይህ የሆነው በወጣቶች ቻምፒዮና ላይ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩ ለስፖርቱ ከልብ በሚቆረቆሩ ሰዎች ዘንድ ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።
በቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም