
በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ፤ በርካታ የተሀድሶ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ይገኛሉ። አዲስ አበባን ምርጥ ከተማ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከማስተዋወቅ ጀምሮ፤ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ከመንገድ ደህንነት ጋር በተገናኘ መፍትሄ ይሰጣል የተባለለት የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት አንዱ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በተሠሩ እና እየተሠሩ ባሉ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንጎችን በተመለከተ በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የፓርኪንግ እና የመንገድ ትራፊክ መሰረተ ልማት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ጌታቸው ከአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
አቶ ቢኒያም፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከ2010 ዓ.ም ወዲህ በርካታ ለውጦች ተስተውለዋል ሲሉ ገልፀዋል። በተለይ ከትራፊክ ደህንነት ጋር በተገናኘ የከተማ አስተዳደሩ ለከተማ ትራንስፖርት ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት እንደየተሽከርካሪ ማቆሚያ ያሉ ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል። የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ከሚባሉት ውስጥ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች፣ ተርሚናሎች እና ዲፖዎች ተጠቃሽ ናቸው። እነኚህ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ለትራንስፖርት ዘርፉ መዘመን ወሳኝ በመሆናቸው በከተማ አስተዳደሩ በኩል እየተሠራባቸው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራዎችን በተመለከተ ብዙ ማለት ይቻላል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት እንደዚሁም ከመጀመሪያው ቀደም ብሎ በነበረው ትግበራ በመንግሥት ብቻ መቶ አርባ ስምንት (148) የተሸከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። አዲስ አበባ ውስጥ ካለው የመሬት ውስንነት አንጻር መቶ አርባ ስምንት ቦታዎችን ለተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት መጠቀም ትልቅ ውሳኔ እንደሚጠይቅ በመጠቆም፤ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የተሽከርካሪ ማቆሚያዎቹ በአቀማመጣቸውም ሆነ በይዘታቸው የተለያዩ ሲሆኑ፤ እንደመስቀል አደባባይ፣ አንድነት ፓርክ፣ አድዋ ሙዚየም የመሳሰሉት ከመሬት በታች የተገነቡ የቤዝመንት ፓርኪንጎች ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ ከላይ የተሽከርካሪ ማቆሚያ (ሰርፌስ ፓርኪንግ) በሚል ስያሚ አገልግሎት እየሰጡ ያሉም እንዳሉ አንስተዋል።
ከተማ መሀል እና ወሳኝ ቦታ ላይ በመገንባታቸው በቀን በርካታ ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ የትራፊክ ደህንነትን ጨምሮ የመንገድ ላይ እንግልትን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ጥቅም እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ ሰፋፊ አስፓልቶች ላልተገባ የመኪና ማቆሚያነት ሲውሉ ነበር። ይህንን ተከትሎ ካለው ችግር በመነሳት እግረኛውም ተሸከርካሪውም በአንድ አቅጣጫ እየተጓዘ ችግሮች ሲፈጠሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ የኮሪደር ልማቱ አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ላይ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች በመሠራታቸው ችግር ከማቃለል አኳያ የማይተካ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።
የትራፊክ ፍሰት ተሻሻለ ለማለት የነበረውን ካለው ጋር ማስተያየት ተገቢ እንደሚሆን ገልፀው፤ ከዚህ በፊት የትራፊክ መጨናነቅ የሚታይባቸው የሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓቶች ላይ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ የመቀነስ ሁኔታን በማጤን የኮሪደር ልማቱ ለተሽከርካሪ ፍሰት የፈጠረውን እድል መመልከት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በፊት መኪናዎች አስፓልት ላይ ሲቆሙ፣ ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ሲገኙ እንደነበር አንስተው፤ በተለይ በበዓል ቀናት ቅዳሜና እሁድ በአምልኮ ሥፍራዎች አካባቢ ተሽከርካሪ ለማቆም ቦታ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰዋል። የተሽከርካሪ ማቆሚያዎቹ ለሁሉም ሰው ግልጽ በሆነ መልኩ ለሀገሪቱ የትራንስፖርት ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ በማብራራት፤ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎቹ በጥራት እና በብዛት መሠራታቸው በከተማዋ እየተስተዋለ ላለው የትራፊክ መጨናነቅ መፍትሄ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ፓርኮቹ እቅድ ተይዞላቸው በፕላን የተገነቡ በመሆኑ፤ አሁን ላይ እንደታሰበው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ለአብነት ከአንድ ሺህ በላይ ተሸከርካሪዎችን የሚይዘው የመስቀል አደባባይ ፓርኪንግ፤ በአካባቢው በዛ ላሉ የተሽከርካሪ ፍሰት መጨናነቅ መፍትሄ የሰጠ በመሆኑ ትልቅ ችግር ቀርፏል፡፡
ሾላ ፓርኪንግ ከሌሎቹ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች የሚለየው የሕንፃ ፓርኪንግ መሆኑን አንስተው፤ ሕንጻው ሲገነባ ለመኪና ማቆሚያ ዓላማ ታስቦ እንደተገነባ ጠቁመዋል። ሕንጻው ከመሬት በታች ሁለት፣ ከመሬት በላይ አምስት በአጠቃላይ ሰባት ወለሎች እንዳሉት ገልጸው፤ ተሽከርካሪዎቹ ከአንዱ ወለል ወደሌላኛው ወለል ለመሄድ ምንም አይነት መካኒካልም ሆነ ኤሌክትሪካል ሲስተም ሳይጠቀሙ በራሳቸው እያሽከረከሩ መሄዳቸው ለየት እንደሚያደርገው አብራርተዋል። ሾላ ፓርኪንግ በአንድ ጊዜ አንድ ሺህ ሀምሳ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሾላ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ ከመሠራቱ በፊትም ሆነ ከተሠራ በኋላ አሽከርካሪዎችን በማነጋገር አነስተኛ የዳሰሳ ጥናት ተሠርቶ ነበር ያሉት አቶ ቢኒያም፤ የብዙዎች ምላሽ አካባቢው የገበያ ሥፍራ በመሆኑ ለመሸመት የሚመጣ ሰው መኪና ማቆሚያ ያጣ እንደነበር ተናግረዋል። የተገኘው ቦታ ላይ አቁመው ሲሄዱ፤ መኪናቸው ተገጭቶ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፤ በተለይ መኪና መስረቅን በተመለከተ አስከፊ ችግር እንደነበር ጠቁመዋል። አሁን ግን በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ወጥቶባቸው የተገዙት ተሽከርካሪዎች ሁነኛ የደህንነት ቦታ በማግኘታቸው ስጋታቸው መቀረፉን ተናግረዋል ሲሉ አቶ ቢኒያም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ቢኒያም ገለጻ፤ በብዙ ቴክኖሎጂዎች የተደገፈው የሾላ ፓርኪንግ ከደህንነት አኳያ አስተማማኝ በሆነ መልኩ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት እየሠራ ነው። ፓርኪንጉ የብዙ አሽከርካሪዎችን ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ፤ እየተሠራ ላለው የምርጥ ከተማ (ስማርት ሲቲ) እንቅስቃሴ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው።
ከቴክኖሎጂ አኳያ ወለሉ ላይ በተገጠሙ ስክሪኖች ያልተያዙና የተያዙ ቦታዎችን መለየት ይቻላል። ተሽከርካሪዎች ፓርኪንግ ላይ ቆመው ብልሽት ቢገጥማቸው ተሽከርካሪዎቹን በካር ሊፍት ማውረድ የሚቻልበት ሁኔታ ተመቻችቷል። የእሳት አደጋ ከተነሳ በየወለሉ የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎች በመኖራቸው ወዲያውኑ ርምጃ ለመውሰድ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ተሽከርካሪዎች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የሚፈጠር የአየር ብክለትን ለመከላከል አየር ማስወጫ የተገጠመ ሲሆን፤ ፓርኪንጉ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ የተሠራ መሆኑም ለየት እንደሚያደርገው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በከተማዋ የተለያየ ይዘት ያላቸው መቶ አርባ ስምንት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ፓርኪንጎች እንዳሉ አንስተው፤ ከሰው ንክኪ በራቀ መልኩ በቴክኖሎጂ በታገዘ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት ላይ መደረሱን አመልክተዋል። እስከ አሁን ሀምሳ አንድ የሚደርሱ ማኅበራት በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ የፓርኪንግ አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
እንደ በፊቱ በትኬት ሳይሆን በሲስተም ቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ እንደሚሠራ በማስታወስ፤ ቴክኖሎጂው ተሽከርካሪ ምን ያህል ሰዓት እንደቆመ ይመዘግባል፤ የክፍያ መጠን ይገልጻል፤ ምቹ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጫ በመሆኑ ምንም አይነት ቅሬታ የማይስተናገድበት ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ ከተማ እንደስፋቷ፣ እንደምታስተናግደው የተሽከርካሪ መጠን አሁን ያሉት የፓርኪንግ ቦታዎች በቂ ናቸው? የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው በሰጡን ምላሽ የተሽከርካሪ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው። በዓመት አስራ ሁለት በመቶ ያህል አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገሪቱ ይገባሉ። ከዚህ አኳያ በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም ብለዋል። ይሁንና በአንድ ከተማ ላይ ብዙ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አይበረታታም፤ ሲበዛ ዜጎች የግል መኪናዎች ላይ አተኩረው የሕዝብን ተሽከርካሪ እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ ነው በሚል ይታሰባል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በሌሎች ሀገራት ላይ እንደሚታየው ይህን ያህል ተሽከርካሪ ስላለ ይህን ያህል ፓርኪንግ ይዘጋጅ የሚባል ነገር እንደሌለ አብራርተዋል።
ስለተሽከርካሪ ማቆሚያ የተነሳው መንግሥት እየሠራ ካለው በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ ሆቴል ሲገነባ፣ ሕንጻ ሲሠራ ለደንበኞቹ መኪና ማቆሚያ የሚሠራው የተከለለ ቦታ ሳይታሰብ ነው ብለዋል። የግሉ ዘርፍ ሲካተት፤ በመጠንም በአገልግሎትም የሰፋ የመኪና ማቆሚያ ቦታ የማግኘት አጋጣሚዎች መፈጠራቸው ሊታወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የኮሪደር ልማቱን መሰረት አድርገው የተሠሩ እና እየተሠሩ ያሉት እነዚህ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች ከዋናው አስፓልት ያራቁ በመሆናቸው ሚናቸው የጎላ ሆኖ ሊነሳ እንደሚችልም አመላክተዋል።
ከጥቅም አኳያ የተሽከርካሪ ፍሰትን ከማዘመን፣ የካርቦን ልህቀትን ከመቀነስ፣ አላስፈላጊ የነዳጅ ብክነትን ከመታደግ ብሎም የአሽከርካሪ እንግልትን ከመቀነስ አኳያ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች አይነተኛ ጥቅም እንዳላቸው አንስተዋል። አቶ ቢኒያም አያይዘውም፤ ለከተማ እድገት እና ለትራንስፖርት ልማት መሳካት የትራፊክ ፍሰት መሳለጥ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ሌሎች በግንባታ ላይ ያሉ መሰል የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች መኖራቸውን አንስተው፤ ለአብነት ቴዎድሮስ አደባባይ፣ ጥቁር አንበሳ፣ አፍሪካ ሕብረት፣ ቦሌ መስመር ቲኬ ሕንጻ አካባቢ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ቁጥራቸው ከሰባ እስከ ሰማኒያ የሚደርሱ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ከትራንስፖርት ልማት ጋር በተያያዘ እንደተቋም መታቀዱን በመጠቆም፤ የተሽከርካሪ ቁጥር ከመጨመሩ ጋር በተገናኘ እንዲሁም ያለውን አቅርቦት ለማሳደግ በቀጣይ የመሬት ላይ ፓርኪንጎች ብዙ ተሸከርካሪዎችን እንዲያስተናግዱ ወደ ሕንጻ ለማሳደግ ዲዛይን እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል። ከባለድርሻ አካላት ጋር በመዋሃድ የቡድን ሥራ እንደሚሠራ፣ የሕንጻ ባለቤቶችም በፍቃዳቸው መሰረት የፓርኪንግ ቦታዎችን ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ሰፊ ሥራ እንደሚሠሩ አመላክተዋል።
ሀገር በማሳደግ እንቅስቃሴ ውስጥ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ወሳኝ እና አስፈላጊ እንደሆነ ያነሱት አቶ ቢኒያም፤ የትራንስፖርት ዘርፉ በቅንጅት እና በትብብር የሚሠራ በመሆኑ የግል ዘርፉን ጨምሮ ሁሉም ወደ አንድ ሲስተም መጥቶ በጋራ የሚሠራበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል። በማከልም ዘመኑን በዋጀ ቴከኖሎጂ ነገን መቀበል አስፈላጊ በመሆኑ፤ ጊዜው ለሚፈቅደው የቴክኖሎጂ ሽግግር ራስን በማዘጋጀት ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኮሪደር ልማቱ ከተማን ከማዘመን እና መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን በወረቀት ይሰጡ የነበሩ ነባር አሰራሮችን የሚቀየሩበት፣ ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆኑ የቴክኖሎጂ ግብይቶች የሚፈፀሙበት በአጠቃላይ ምቹ እና አስተማማኝ አገልግሎቶች የሚተዋወቁበት ጭምር ነው፡፡
በከተማዋ ስምንት መቶ ሺህ አካባቢ መኪናዎች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ቢኒያም፤ በቀጣይ ይህ ቁጥር ስለሚጨምር ቴክኖሎጂ ተኮር የአገልግሎት መስጫ ፓርኪንጎች በብዛት እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል። በሂደቱም የተሳካ ውጤት እንደሚመጣ አመላክተዋል። ባማረ እና በሰፋ አስፓልት ላይ የትራፊክ ሕጉ የሚፈልገውን አይነት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ መኖሩ ከተማን ከማዘመን ባለፈ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ሚናው የላቀ ነው። ይሄን መሰሉ እውነታ ከትራንስፖርት ልማት እቅዶች መሀል አንዱ ሲሆን፤ እንደ ዓላማ ተይዞ እየተሠራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አቶ ቢኒያም የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ከከተማ አስተዳደሩ የተረከባቸውን እና ለአገልግሎት ክፍት ያደረጋቸው የአሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች ሰዎች ሲመጡ በሲስተም እንደሚገለገሉ፤ ደህንነቱ በተጠበቀ አስተማማኝ ቦታ መኪናቸው ጥበቃ እንደሚደረግለት አምነው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም