ልጆችን በፍቅርና በጥበብ ማሳደግ

ሁሉም ወላጆች ልጆቻቸው ጠንካራ፣ ብልህ እና ደግ ሆነው እንዲያድጉ ይፈልጋሉ። እናቶች እና አባቶች ለልጆቻቸው የተሻለውን ሕይወት የመስጠት ሕልም አላቸው። ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም የሰው ልጆች እውነታ ነው። ነገር ግን ወላጅነት ቀላል አይደለም። ልጆችን በጥሩ ሥነ ምግባር ማሳደግ ጊዜን፣ ትዕግስትን፣ ፍቅርን እና እውቀትን ይጠይቃል።

ልጆች እንዴት ማደግ እንዳለባቸው እና በምን መልኩ አዕምሯቸው መዳበር እንዳለበት መረዳት ሲቻል የተሻለ ወላጅ መሆን ይቻላል። ይህንን ጉዳይ በዚህ ምሳሌ ለመመልከት እንሞክር። ልጅን ማሳደግ ዛፍ እንደማሳደግ ነው። ችግኝ ስንተክል በየቀኑ ውሃ ማጠጣት ያስፈልገናል፤ ከመጥፎ የአየር ሁኔታ መጠበቅ ይኖርብናል። ለችግኙ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኝ ማድረግ የግድ ነው። ይህንን መስፈርት በትክክል ስንከተል አንድ ቀን ቆንጆ እና ጤናማ ዛፍ ሆኖ ያድጋል። በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ልጅ በየቀኑ ፍቅር፣ እንክብካቤ፣ ደህንነት እንዲሁም የተሻለ ትምህርት እና ድጋፍ ያስፈልገዋል። በዚህ መልኩ ልጆቻችንን ካሳደግን የምንፈልገውን ውጤት እናገኛለን።

ብዙ ወላጆች ጥሩ ‹‹አስተዳደግ ምንድን ነው›› ‹‹መጥፎ አስተዳደግ ማለትስ እንዴት ይገለፃል?›› ‹‹ልጆቻችንን ጠንካራ፣ አስተዋይ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?›› የሚሉ ጠንካራ ጥያቄዎችን ያነሳሉ። ይህ ጉዳይ ትኩረት ከሰጠነው ቀላል፣ ግልጽ መልሶች አሉት። በዛሬው መጋቢ አዕምሮ ዓምዳችን ለማተኮር የፈለግነውም በእነዚህ መፍትሄዎች ላይ ነው።

ጥሩ አስተዳደግ ማለት በልጆቻችሁ ሕይወት ውስጥ ሁሌም ንቁ ሆኖ መገኘት ማለት ነው። ለልጆች ፍቅር እና ትኩረት መስጠት ማለት ነው። ልጆች ሲናገሩ እነሱን ማዳመጥ እና ስለ ስሜታቸው መጨነቅ ማለት ነው። አንድ ልጅ ፍቅር እና ደህንነት ሲሰማው፤ በራስ መተማመን ያድጋል። የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማኅበር ጥናት እንደሚያሳየው በወላጆቻቸው ድጋፍ የሚሰማቸው ልጆች የተሻለ የአእምሮ ጤንነት ያላቸው እና በትምህርታቸው የተሻሉ ናቸው። በተጨማሪም ከሕይወታቸው ወንጀልን እና አደገኛ ልማዶችን ለማስወገድ የበለጠ እድል አላቸው።

ልጆችን በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ ማለት ሀብታም መሆን አይደለም፤ ለልጆች በቂ ጊዜ መስጠት ነው። በየቀኑ ከልጆች ጋር መነጋገርር እና ሀሳባቸውን እንዲገልፁ ማበረታታት ነው። ሲሳሳቱ በእርጋታ ማረም፤ ትክክል እና ስህተት የሆነው ሁሉ እንዲገነዘቡ መርዳት ያስፈልጋል። ልጆች ድጋፍ እንዳገኙና እንደተረዱት ሲሰማቸው የተሻለ ባህሪ ይኖራቸዋል፤ በፍጥነትም ይማራሉ።

በሌላ በኩል መጥፎ አስተዳደግ ልጅን በእጅጉ ሊጎዳ ይችላል። ወላጆች ብዙ ጊዜ ሲጮሁ፣ ልጆቻቸውን ሲደበድቡ ወይም ችላ ሲሏቸው ልጆች ይፈራሉ፣ ያዝናሉ ወይም ተናዳጅ ባህሪን ያዳብራሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው ናሽናል የአእምሮ ጤና ኢንስቲትዩት የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው በዓመፅና በጭንቀት በተሞላ ቤት ውስጥ የሚያድጉ ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ ለድብርት እና ለጭንቀት የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። እነዚህ ልጆች በትምህርት ቤት እና በሌሎች ግንኙነቶች ውስጥ ችግር ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ልጆቻችን እንዲጠነክሩ ከፈለግን በመጀመሪያ በፍቅር፣ አክብሮት እና በተረጋጋ ቃላት የተሞላ ቤት መፍጠር አለብን። አንድ ልጅ ስህተት ሲሠራ እንኳን ከመቅጣት ይልቅ ማብራራት ያስፈልጋል። መደብደብ ፍርሃትን እንጂ ማስተዋልን አያስተምርም። መጮህ ዝምታን እንጂ ለውጥ አያመጣም።

ልጆችን እንዴት ጠንካራ እናድርጋቸው

አሁን ልጆችን እንዴት ጠንካራ ማድረግ እንደሚቻል እንነጋገር። ጠንካራ ልጅ ማለት ተክለ ሰውነቱ ኃይል ያለው ብቻ አይደለም። ጠንካራ ልጅ ማለት ጠንካራ አእምሮ እና ልብ ያለውም ጭምር ነው። ይህንን መሰል ጥንካሬ ያላቸው ልጆች ችግሮችን መፍታት ይችላሉ። ለራሳቸው መቆም ይችላሉ። ለመጥፎ ጓደኞች ሲያጋጥማቸው በተፅእኖ አንድን ነገር ከማድረግ የሚቆጠቡ ‹‹አይሆንም፤ አልፈፅም›› ማለት ይችላሉ። ቁጣቸውን (በውስጣቸው የሚፈጠር ንዴት) መቆጣጠር ይችላሉ። እንደዚህ አይነት ጥንካሬን ለመገንባት ልጆቻችን በራሳቸው እንዲተማመኑ ማስተማር አለብን። ሁሌም አንደሚችሉ እና አቅም እንዳላቸው መንገር ይኖርብናል።

በቀላል ነገር ልናስተምራቸው እንችላለን። ለምሳሌ ክፍላቸው ማጽዳት ወይም በኩሽና ውስጥ መርዳትን የመሰሉ ትናንሽ ኃላፊነቶችን መስጠት ይገባናል። ሥራቸውን በስኬት ሲያጠናቅቁ ማወደስና ማመስገንም ያስፈልጋል። ይህ በልጆቻችን ላይ ድፍረትን ይገነባል። የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ በታዳጊነታቸው ጊዜ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የሚሠሩ ልጆች የበለጠ ኃላፊነት የሚሰማቸው አዋቂዎች እንደሚሆኑ አረጋግጧል። በተጨማሪም ልጆቻንን ጠንካራ እንዲሆኑ ስህተት ሲሠሩ ሳይሸማቀቁ ግን ስህተቱን እንዲረዱ ልንናደርግ ይገባል። ሁሉንም ነገር ኃላፊነት መውሰድ አይገባንም። ለምሳሌ ሲወድቁ በራሳቸው ጥረት እንዲቆሙ ልንረዳቸው ይገባል። ይህ ውሳኔያችን ልጆቻችን ሕይወትን በጥንካሬ እንዲጋፈጡ ያስተምራቸዋል።

በልጆች አስተዳደግ ውስጥ ጥንካሬ ብቻውን በቂ አይደለም። ልጆቻችንም ብልህ እንዲሆኑ ማድረግ አለብን። ብልህ ልጅ የዓለምን አሠራር ማሰብ፣ መማር እና መረዳት ይችላል። ልጅን ብልህ ለማድረግ ቀደም ብለን መሥራት አለብን። ከመናገራችን በፊትም ልጃችንን እናነጋግር። ዘፈኖችን፣ ታሪኮችን፣ የቀለሞችን እና የቅርጾችን ሁኔታ ማሳየት አለብን። በዚህ መልኩ ከቀረፅናቸው በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የልጆች አእምሮ በፍጥነት ያድጋል።

ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በአእምሮ እድገት ላይ ባደረገው ጥናት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የማሰብ ችሎታን ለመገንባት በጣም ጥሩው ጊዜ መሆናቸውን አስፍሯል። ይህንን ለማድረግ ሀብታም መሆን አያስፈልግም። በቤት ውስጥ ቀላል መሳሪያዎችን መጠቀም ይቻላል። ማንኪያዎችን፣ የእንስሳትን ስያሜ፣ የሀገር ውስጥ ታሪኮችን ማስተማር ይቻላል።

ልጆች ከጨዋታ ይማራሉ። ይሁን እንጂ የስልክ እና የቴሌቪዥን መመልከቻ ጊዜንና የሚከታተሉትን ፕሮግራም መገደብ ያስፈልጋል። በጣም ብዙ ጊዜ በኤሌክትሮኒክስ ዲቫይስ ላይ ሲያጠፉ ትኩረታቸውን ያዳክማል። በምትኩ ስዕል መሳልን፣ ማንበብን እና በዕለት ተዕለት ተግባራታቸው ላይ ልንረዳቸው እና ልናበረታታቸው ይገባል።

ሌላው የአዕምሮ እድገት አስፈላጊ አካል ምግብ ነው። የተራበ ልጅ በደንብ መማር አይችልም። የዓለም ጤና ድርጅት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጥሩ ምግብ የሚመገቡ ሕፃናት በትምህርት ቤት የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ። ስለዚህ ልጆቻችንን ጤናማ ምግብ መመገብ ይገባናል። በተጨማሪም ልጆች በቂ እንቅልፍ ያስፈልጋቸዋል። እንቅልፍ አንጎል እንዲያርፍ እና በበቂ ሁኔታ እንዲያድግ ይረዳል። በእንቅልፍ እጦት የደከሙ ልጆች ብዙውን ጊዜ ተናዳጅ ይሆናሉ ወይም ለነገሮች ትኩረት አይሰጡም።

መልካም ባኅሪን ለመገንባት

ልክ እንደ ብልሀትና ጥንካሬ ሁሉ ሌላኛው ለልጆች እድገት አስፈላጊ የሆነው ሥነ ምግባር ነው። ለልጆች ጥሩ ባኅሪም በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ልጅ ደግ፣ ታማኝ፣ ታጋሽ እና ሰው አክባሪ መሆን አስፈላጊ መሆኑን ማወቅ አለበት። እነዚህ ባሕርያት ልጆችን ጥሩ ሰው ያደርጋቸዋል። ለመሆኑ ጥሩ ባኅሪን እንዴት በልጆች ውስጥ እንቀርፃለን?

የመጀመሪያው ልጆች መልካም ባኅሪ እንዲኖራቸው የሚረዳው በምሳሌ ማሳየት ነው። ወላጆች ከሰዎች ጋር በደግነት እና በጥሩ ሥነ ምግባር የሚያሳልፉ ከሆነ ልጆችም ደግነትን ይማራሉ። ወላጆቻቸውን ወይም አሳዳጊያቸውን ይከተላሉ። መከባበርን ይማራሉ። ልጆች ዙሪያቸውን ይመለከታሉ፤ የተመለከቱትን ይደግማሉ፤ ከዋሸን ሊዋሹ ይችላሉ። ስለዚህ በእነሱ ውስጥ ማየት የምንፈልጋቸውን እሴቶች እኛ እራሳችን በምሳሌነት መኖር አለብን። ሁለተኛው ጉዳይ ትክክል እና ስህተት የሆነውን በንግግር ማስረዳት ነው። ሌላው ሶስተኛው ጉዳይ የልጆቻችንን ጥሩ ባኅሪ ማወደስ ነው። ልጆቻችን ለሌሎች ያላቸውን ሲያካፍሉ ወይም ለተቸገረ ሲረዱ ልናመሰግናቸውና ልናደንቃቸው ይገባል። ይህ ልጆች የበለጠ ጥሩ ባኅሪ እንዲላበሱ ያበረታታል። የዩኒሴፍ ጥናት እንደሚጠቁመው ልጆች ከከባድ ቅጣት ይልቅ በደግና በሩህሩህነት ለተሰጣቸው ተግሣጽ ቀና ምላሽ ይሰጣሉ። ይህ ከልጆቻችን ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ያበረታታል። መተማመን እና ፍቅርን ይገነባል።

በሌላ መልኩ ልጆቻችን ከሌሎች ጋር ከማወዳደር መቆጠብ አለብን። እያንዳንዱ ልጅ የተለየ ነው፤ በመሆኑም የራሳችንን ልጆች እንደ ባኅሪያቸው ማሳደግ እና ለጥሩ ተግባር ማብቃት ይገባናል። ልጆችን ማወዳደር በራስ የመተማመናቸውን እና ስሜታቸውን ሊጎዳ ሲከፋም ቅናት ሊያስከትል ይችላል።

ሌላው የልጆች አስተሳሰብ ግንባታ ነው። ጥሩ አስተሳሰብ ልጆቻችንን በሕይወት ውስጥ በተስፋ እና በራስ መተማመን እንዲኖሩ ይረዳቸዋል። ሁሌም ማንኛውንም ከባድ የሚመስል ነገር ማድረግ እንደሚችሉ፤ ምንም እንደማያቅታቸው በአስተሳሰባቸው ውስጥ ልንቀርፅ ይገባል። ሞክረው ባይሳካላቸው እና ውድቀት ቢያጋጥማቸው ደጋግመው እንዲሞክሩ ሊማሩ ይገባል። ለምሳሌ በሙያ ክህሎት እና ዝንባሌ ዶክተር፣ አስተማሪ ወይም ፓይለት መሆን ከፈለጉ ሕልማቸውን ከመኖር ምንም እንደማያግዳቸው ሊያውቁ ይገባል። ስህተቶችን ለተስፋ መቁረጥ ሳይሆን እንደ አንድ የትምህርት አጋጣሚ እንዲመለከቱ ማበረታታት አለብን። በሁኔታዎች ላይ ወቃሽና ቅሬታ አቅራቢ ብቻ ሳይሆኑ ችግር ፈቺና መፍትሄ አፍላቂ እንዲሆኑ አድርገን አስተሳሰባቸውን መገንባት አለብን።

የማኅበረሰቡ ድጋፍ

በልጆች አስተዳደግ ላይ ወላጆች ብቻቸውን ሁሉንም ነገር ማድረግ አይችሉም። ሕብረተሰቡ የራሱን ድርሻ በመወጣት መርዳት አለበት። መምህራን፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ ጎረቤቶች እና መገናኛ ብዙሃን የዚህ አካል ናቸው። ትምህርት ቤቶች ልጆችን ከቀለም ትምህርት በላይ ማስተማር አለባቸው። አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች ሰላም እና ፍቅርን ማስተማር አለባቸው። በማኅበረሰቡ ድጋፍ ለልጆች እድገት በሚመች መልኩ ጎዳናዎችን ንጹህ ማድረግ አለበት። የመጫወቻ ሜዳዎች ሊዘጋጁ ይገባል። ልጆች ለማደግ እና ለመጫወት ነጻ መሆን ይኖርባቸዋል። ለዚህ መገናኛ ብዙሀን ጥሩ ምሳሌዎችን ማቅረብና ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ፊልሞች፣ ሙዚቃዎች እና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ዓመፅንና ስግብግብነትን ብቻ ከማስተላለፍ መቆጠብ፤ በተቃራኒው ደግነት፣ ታማኝነት እና የሕብረት ሥራ ጠቀሜታን አጉልተው ለልጆች ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። መንግሥት ወላጆችን መደገፍ ፤ ጤና ጣቢያዎች መገንባት ፤ የልጆች ጥበቃ በሕግ እና በልዩ ልዩ መንገድ ጠንካራ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ድጋፍ ማግኘት አለባቸው። ምክንያቱም ገቢ ጥሩ የልጅ አስተዳደግ ላይ ማቆም መሆን የለበትም።

ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ እናቶች ብቻቸውን ልጆችን የማሳደግና ቤተሰብን የማስተዳደር ትልቅ ሸክም ይሸከማሉ። ይህ ሁኔታ ሊቆም እና አባቶች በእኩል መጠን ለልጆች አስተዳደግ ሚና ሊኖራቸው ይገባል። አንድ ልጅ በሚዛን እንዲያድግ ሁለቱም ወላጆች አስፈላጊ ናቸው።

ልጆች ዛሬ እንጂ ነገ ልጆች አይደሉም፤ የኢትዮጵያ የወደፊት ዶክተሮች፣ መምህራን፣ አርቲስቶች እና መሪዎች ናቸው። በደንብ ካሳደግናቸው የተሻለች ሀገር እንገነባለን። በልጆች አስተዳደግ ላይ ካልተሳካልን ግን ወላጅና አሳዳጊ ብቻ ሳንሆን ሀገሪቱም ትወድቃለች። ስለዚህ ልጆቻችንን በፍቅርና በጥበብ እናሳድግ። ሰላም!!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You