
አዲስ አበባ፡- ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺነታቸው በተረጋገጡ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ 23ኛው ዓለምአቀፍ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአፍሪካ ጉባዔ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሠሩ ጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀጣይነት ያለው ልማትን በማረጋገጥ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ፣ የሃይል አቅርቦት እጥረት እና ማህበራዊ ችግሮች የሰው ልጆችን እየገጠሙት ያሉት ፈተናዎች ናቸው ያሉት አቶ ኮራ፤ በእነዚህ ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናትና ምርምሮች አስፈላጊነታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የቅድስትማርያም ዩኒቨርሲቲ ይህንን ዓለምአቀፍ ጉባዔ በማዘጋጀት በትምህርት ዘርፍ እየፈጠረ ላለው እድል ሚኒስትር ዴኤታው አመስግነው፤ የዩኒቨርሲቲው እንቅስቃሴ ለሌሎች የግል የትምህርት ተቋማት መልካም ተሞክሮ መሆኑንም ተናግረዋል።
አቶ ኮራ የጉባዔው መዘጋጀት አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ተቋማት ጋር በጥምረት ፣ ለመሥራት ያላቸውን እድል የሚያሳድግ፣ እውቀት በማካፈል እና በዓለምአቀፍ ጥናትና ምርምሮች ላይ ያላቸውን ድርሻ ለማሳደግ የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሰል ጉባዔዎችን ይደግፋል ያሉት አቶ ኮራ፤ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ተደራሽነትን በማሳደግ፣ አካታችነት እና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያደርጉትን ጥረቶች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተወዳዳሪነት እንዲሠሩ የፖሊሲ ትግበራዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የቅድስትማርያም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ወንደሰን ታምራት (ፒ.ኤች.ዲ) በበኩላቸው ጉባዔው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቀጣዩን ማህበረሰብ በመቅረፅ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልጸው ፤ የጥናትና ምርምር አጀንዳ መሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ከማምጣት ጋር የተሳሰረ መሆን ይኖርበታል ሲሉ ገልፀዋል።
23ኛው ዓለምአቀፍ የግል ዩኒቨርሲቲዎች ጉባዔ “አካዳሚክ ፕሮፌሽን እና የጥናትና ምርምር ልህቀት በአፍሪካ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ሲሆን ፤ እውቀትን ለሌሎች በሚያስተላልፉ ባለሙያዎች እና እውቀት የሚተላለፍበት መንገድና ለማህበረሰባዊ እድገት ያለው ተፅዕኖ የሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገልፀዋል።
የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱ ፣ የሥርዓተ ትምህርት ዘርፎች እና አካዳሚክ እውቀቶች አሁን ባለንበት ዘመን በእጅጉ እየተለዋወጠ የመጣ መሆኑን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፤ ጠንካራ የትምህርት ሥርዓትን መገንባት እና በሀገር ውስጥ ያለውን አካሄድ ዓለም ከደረሰበት የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ጋር የተጣጣመ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በጉባዔው የተለያዩ ዓለምአቀፍ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች የሀገር ውስጥ የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ምሁራን የተገኙ ሲሆን የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለልማት ያላቸው ሚና ላይ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
በጉባዔው ከጋና ፣ ኬንያ ፣ ፈረንሳይ ፣ ስፔን፣ ካናዳ አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ ተመራማሪዎች ፣ ፖሊሲ አውጪዎች ፣ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ፣ ተማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ መድረክ መሆኑ ታውቋል።
በሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም