
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በመጪው ሰኔና ሐምሌ ሁለት ወራት ብቻ 74 ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንደሚካሄድ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ይግዛው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በኢትዮጵያ በመጪው ሰኔ እና ሀምሌ ወራት 74 ዓለም አቀፍ ጉባዔና ሁነቶች እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ዓለም አቀፍ ጉባዔና ሁነቶቹ የሚካሄዱት በሰኔ ወር 31 ሲሆን በሀምሌ ወር ደግሞ 43 መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም በአዲስ አበባ ፣ በድሬዳዋ ፣ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በአምቦ ፣ በደሴ እና በደብረታቦር መሆኑን ተናግረዋል።
ከዓለም አቀፍ ጉባዔዎችና ሁነቶቹ መካከልም ዘላቂ የውሃ አስተዳደር፣ ሥነምህዳር እርሻና ደን ፣ የዕጽዋት አፈርና የውሃ ሳይንስ፣ ሴል ኤንድ ቲሹ ፣ ናኖ ሳይንስ ኤንድ ናኖ ቴክኖሎጂ፣ ባዮቴክኖሎጂ፣ ባዮ ሜዲስን ኤንድ ጀኔቲክ ኢንጂነሪግ፣ ሊደር ሺፕ ፣ ኢንተርፕሪነርሽፕ ኤንድ ቢዝነስ ማኔጅመንት፣ ዋየርለስ ኔትወርክ ኤንድ ሞባይል ኮሙኒኬሽን ፤ ኢንቫይሮሜንት ኤንድ ላይፍ ሳይንስ ተጠቃሾች ናቸው።
በያዝነው 2017 ዓ.ም ባለፉት 9 ወራት ብቻ 84 ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችና ኹነቶች የተካሄዱ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህም 30 ሺህ 340 የውጭ ሀገርና 171 ሺህ 739 የሀገር ውስጥ ሰዎች ተሳትፈውበታል። በግንቦት ወር እስካሁን ድረስ ዘጠኝ ዓለምአቀፍ ኹነቶች መከናወናቸውን አቶ ጌትነት ጠቅሰዋል።
በ2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ 19 ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች የተካሄዱ መሆኑን አስታውሰው፤ በ2017 ዓ.ም የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔና ሁነቶች እያደገ እና ሀገሪቱ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ እየሆነች መምጣቷን ያመለክታል ነው ያሉት።
ቱሪዝም ላለፉት 55 ዓመታት አንድ ሚሊዮን ቱሪስቶች ለመሙላት ትኩረት አድርጎ ሲሠራ የነበረው የቅንጦት (ሌግዠሪ) ቱሪዝም ላይ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጌትነት፤ ነገር ግን እቅዱን ለማሳካት እንደ ሰማይ ርቆ እንደነበር ተናግረዋል።
አሁን ግን የዘርፉን አቅጣጫ ወደ ቢዝነስ ቱሪዝም በማሸጋገር በሀገሪቱ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ከአምስቱ የኢኮኖሚ ዘርፍ አንዱ ተደርጎ እየተሠራበት መሆኑን አብራርተዋል።
በቢዝነስ ቱሪዝም የሚመጡ ቱሪስቶች ማንኛውም የሚጠየቁትን ገንዘብ መክፈል የሚችል አቅም ያላቸው በመሆናቸው ይዘው የመጡትን ገንዘብ ተጠቅመውበት እንዲሄዱ የቆይታ ጊዜያቸውን አራዝመው የሚያሳልፉበት፣ በእግራቸው የሚጓዙበት፣ ስፖርት የሚሠሩበት፣ የሚዝናኑበት፣ መጽሀፍ የሚያነቡበት ሥፍራና አማራጭ መዝናኛዎች ያስፈልጋቸዋል። ይሄንን አሟልቶ መገኘት ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በነበረው የሌግዠሪ ቱሪዝም ትልቁ የሰው ቁጥር ከ23 እስከ 25 የሚደርስ ሲሆን በቢዝነስ ቱሪዝም ግን ከ200 ጀምሮ እስከ 25 ሺህ ጉባዔተኛ ሊመጣ ይችላል። በዚህም ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ ይገባል። ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ እድል ይኖራል፤ በማንኛውም አገልግሎት ላይ የተሠማራ የተማረም ሆነ ያልተማረው ተጠቃሚ ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ሁሉም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በትንሹ ከስድስት እስከ 33 የሚደርስ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችንና ሁነቶችን ወደ ሀገር ቤት በማምጣት በጋራ ኮንፈረንሶች እንዲካሄድ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራበት መሆኑን አቶ ጌትነት አብራርተው፤ ይሄም በአጭር ጊዜ ውጤት እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
እአአ ከ2024 እስከ 2027 በኢትዮጵያ ውስጥ ከ 300 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችና ኹነቶች ይካሄዳሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
በአልማዝ አያሌው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም