
አዳማ፡- በሁለተኛው ዙር የተቀናጀ ሀገር አቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በዘጠኝ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከ15 ሚሊዮን በላይ ህፃናት እንደሚከተቡ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ሁለተኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ መርሀግብር ትናንት በአዳማ የከተማ ተጀምሯል።
በክትባት ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ የዋይልድ ፖሊዮ በሽታን ከኢትዮጵያ ለመጥፋቱ ማረጋገጫ ከተሰጠበት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በክትባት እጥረት ምክንያት የሚከሰተው የፖሊዮ አይነት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመታየቱ ሰፊ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች እየተሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
አብዛኛዎቹ የፖሊዮ ታማሚዎች ሪፖርት የተደረጉት ከኦሮሚያ፣ አማራ፣ ጋምቤላና ሶማሌ ክልልሎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ በተያዘው ዓመት በጥቅምትና ታህሳስ ወራት በአራት ክልሎች ማለትም በአማራ፣ ጋምቤላ፣ በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ አስተዳደር እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ መካሄዱን ዋና ዳይሬክተሩ አውስተዋል፤ በዚህም በአጠቃላይ ከ 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከአምስት ዓመት በታች ህፃናትን ተጀራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በቀሩት ዘጠኝ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም ተካሂዶ ከ15 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ተደራሽ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
የዚሁ የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አካል የሆነውና በአዳማ ከተማ በይፋ የተጀመረው ሁለተኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በእነዚሁ ዘጠኝ የክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በድጋሚ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።
በሁለተኛው ዙር የክትባት ዘመቻ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑና ከዚህ በፊት ምንም ክትባት ያላገኙና ጀምረው ያልወሰዱ ከ15 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህፃናት ተደራሽ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
የወባ መከላከልና ቁጥጥር ሥራ እንዲሁም ሌሎች በኦሮሚያ ክልል የተከሰቱ የጤና ስጋቶችን በቅንጅት መቀልበስ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
ከሁለተኛ ዙር የፖሊዮ የክትባት ዘመቻ ጎን ለጎን ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ህፃናትን የመለየትና የመከተብ ሥራ እንዲሁም የኤም ፖክስ የተያዙ ሰዎችን የመለየትና የማከም ሥራ እንደሚከናወን ገልፀዋል።
በዚሁ መርሀ ግብር ላይ ንገግር ያደረጉት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ክበበው በበኩላቸው በክልሉ በመጀመሪያው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህፃናት መከተባቸውን አስታውሰዋል። በዚህ በሁለተኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ደግሞ 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ በክልሉ የሚገኙ ህፃናት እንደሚከተቡ ገልፀዋል።
የክትባት ዘመቻውን ለማካሄድም 20ሺህ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉና የክትባት ዘመቻውም ለክትባት ቅርበት ለሌላቸው ህፃናት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
በ አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም