የኢትዮጵያ ዘመናዊ የዲፕሎማሲ ታሪክ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ እንደሚጀምር ታሪክ ያወሳል፡፡ በዚህ ዘመንም ከነበሩ የአገሪቱ ነገስታት መካከል አፄ ቴዎድሮስ የውጭ ስልጣኔ ማርኳቸው ለአገራቸው ለማቋደስ በጓጉበት ወቅት ከምዕራብ አውሮፓ አገራት ጋር ጠንከር ያለ ግንኙነትን ሲመሰርቱ፤ በአፄ ምኒሊክ የንግስና ዘመን ደግሞ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተከናውነው ኢትዮጵያም አብዛኛዎቹን የአውሮፓ አገራት መድረስ የቻለችበት ወቅት ነበር፡፡
ይኸው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘመናዊነትን ተላብሶና ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሮ አገሪቱን በቋሚነት የሚወክሉ ዲፕሎማቶችን በመሰየም መልካም የሚባሉ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ዋናው ትኩረትም በአገር ውስጥ በሚሠራው ሥራ ላይ እንዲሆን፣ ኢኮኖሚውን ማዕከል እንዲያደርግ፣ በበቂ ጥናት ላይ ተመስርቶ ከውጭ የሚገኙ ጥቅሞችን አሟጦ መጠቀምና አደጋዎችን መቀነስ እንደሚገባ፣ ብቃት ያለው የመከላከያ ዓቅም እና ጠንካራ የማስፈፀም ብቃት መገንባት እንዳለብን በግልጽ በማስቀመጥ ከውስጥ ወደ ውጭ የሚመለከት ጤናማ የውጭ ግንኙነት ፖለሲ በማዘጋጀት ተፈፃሚነቱ ውጤት አስገኝቷል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማስፈንና አህጉራዊ ትስስርን ለመፍጠር በምታደርገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ትኩረትን አግኝታለች፡፡ ለዚህም ነው ታላላቅ የአገራት መሪዎች አዘውትረው በመጎብኘት መንግሥት የያዘውን ለውጥ በመደገፍና ከፍተኛ ዕርዳታ በማድረግ ላይ የሚገኙት፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ከፈረንሳይ ጋር ያለን ግንኙነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ዶክተር አብይ አህመድ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገሪቱ በለውጥ ጅማሮ ላይ በነበረችበት ወቅት በውጭ አገራት ካደረጉዋቸው ጉብኝቶች በፈረንሳይ ያካሄዱት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ጉብኝቱ የአገራቱን የግንኙነት ታሪካዊነትና ጥንካሬ መገለጫ ከመሆኑም በተጨማሪ ወደ ላቀ ደረጃም ያሸጋገረ ሆኗል።
ቀደም ሲል ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ አጋርነቷን ለማሳየት በቡድን ስምንትና በቡድን 20 ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች አፍሪካን የሚጠቅሙ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ ስትደግፍ መቆየቷ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ተግባሯም የአፍሪካ አምባሳደር በሚል ቅጽል ስም ትጠራለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2016 ለአፍሪካ አገራት የምታውለውን ዓመታዊ የልማት ትብብር ድጋፍ ከነበረበት 4 ቢሊዮን ዩሮ በ2021 ወደ 23 ቢሊዮን ዩሮ ለማሳደግ በ27ኛው የፈረንሳይ- አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ወቅት ይፋ ማድረጓም ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ ካላት ወገንተኝነት ነው፡፡
በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ቀደም ሲል በነበራት ታሪካዊና የጠበቀ ግንኙነት ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ከጅቡቲ የተነሳውና በፈረንሳዊው አውሮፕላን አብራሪ አዲስ አበባ ስጋ ሜዳ ያረፈው አውሮፕላን ፣ እ.ኤ.አ በ1947 ጀምሮ የሚገኘው ሊሴ ገብረማርያም ት/ ቤት እንዲሁም ሌላው የአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ የባህልና ቋንቋ ማዕከል፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ፈረንሳዊው ባለቅኔ አርተር ሬንቦ፣ ከ1928 ዓ.ምቱ የጣሊያን ወረራ በፊት ፈረንሳይኛ ቋንቋ ኢትዮጵያ ውስጥ ለትምህርት ቤቶችና ለዘመናዊ የአስተዳደር ሥራ እንዲያገለግል መወሰኑ፣ በ1893 ዓ.ም በሐረር የሥጋ ደዌ ሆስፒታል የሚሠሩ የፈረንሳይ ቄሶች እያሳተሙት እስከ አዲስ አበባ ድረስ የሚያሰራጩት ኩርየር የሚባል ጋዜጣ መጀመሩ፣ በእንስሳት ሕክምና የፓስተር ኢንስቲትዩት መመሥረቱ፤ በማዘጋጃ ቤት የሚተዳደር የምሕንድስና ትምህርት ቤት መክፈቱ፣ የብሔራዊ ባንክ ሕንፃን የሠራው አርክቴክትና ብሔራዊ ቴአትር አጠገብ የሚገኘውን የአንበሳ ሐውልት የቀረፁ ፈረንሳዊያን መሆናቸው የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ትስስር ፍሬዎች ሆነው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሁለቱ አገራት እ.ኤ.አ ከ1897 ጀምሮ ያላቸው ታሪካዊና ጠንካራ ግንኙነት እስከአሁን ቀጥሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአየር ንብረት ለውጥና በኢኮኖሚ የላቀውን ድርሻ የሚይዝ ነው፡፡ ፈረንሳይ የግብርና ውጤቶችና ጥሬ ዕቃዎችን ከኢትዮጵያ ትገዛለች፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የግብርና ግብአቶችና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከፈረንሳይ ታስመጣለች፡፡ በአሁኑ ወቅት 92 የፈረንሳይ ኩባንያዎች በአገራችን ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የታሪካዊውና ጤናማው ዲፕሎማሲ ፍሬዎች ናቸው፡፡
ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ ጉብኝት የጀመሩት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ታሪካዊ ቦታዎችን ጨምሮ ባካሄዱት ጉብኝት የአገሪቱን ታላቅነት ገልጸው፤ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ማደስ፣ የባለሙያ ድጋፍ ማድረግና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለማስከበርና ሽብርተኝነትን ለመከላከል ወሳኝ አጋር በመሆኗ የመከላከያ ሠራዊቱን ለማጠናከር በባሕር ሐይል ግንባታና አየር ሐይልን በማዘመን በኩል ከፍተኛ ድጋፍ ለማድረግ እንደወሰነች ነው ያስታወቁት፡፡ ይህ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ፍሬ ነው፡፡ አዎ ከራስ አገር አልፎ ለቀጣናው ሰላም አስተዋፅኦ ማበርከት ውጤቱ የላቀ ዕድገት ባስመዘገቡትና አስተዋይ በሆኑት አገራት መደገፍን ያስከትላልና መንግሥት በሃገር ውስጥ የሚሠራው ሥራና በዓለም አቀፍ መድረክ የተከናወነው ዲፕሎማሲ ፍሬ እያፈራ በመሆኑ ይኸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011