የበጀት ረቂቁ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳያ ነው !

 

ከሰሞኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ረቂቅ ላይ ተወያይቶ እና ግብዓት ጨምሮ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩ ይታወሳል:: የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከሰሞኑ ባካሄደው ስብሰባ ይሄንኑ ረቂቅ በጀት ተመልክቷል::

ረቂቅ በጀቱ በገንዘብ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ታግዞ ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን፤ ምክር ቤቱም በረቂቅ በጀቱ ላይ ጥያቄዎችን አንስቶ ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው አድርጓል:: ሰፊ ውይይት በማድረግም ግብዓትን ጨምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል::

በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ መመልከት እንደተቻለው ደግሞ፤ የ2018 የፌዴራል መንግሥቱ በጀት አንድ ነጥብ 93 ትሪሊዮን ሆኖ የቀረበ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም አንድ ነጥብ 183 ትሪሊዮኑ ለመደበኛ በጀት፤ 415 ነጥብ ሁለት ቢሊዮኑ ለካፒታል ወጪዎች፤ እንዲሁም 314 ነጥብ ስምንት ቢሊዮኑ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እና 14 ቢሊዮኑ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ይውላል::

በስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 35ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ እንዳመለከቱት፤ የበጀት ምንጩ አንድም፣ ከፌዴራል መንግሥት ከሀገር ውስጥ የገቢ፤ ሁለትም ከውጭ ርዳታ ሲሆን፤ በእነዚህ ሁለት ምንጮችም በድምሩ ከአንድ ነጥብ 510 ትሪሊዮን ብር በላይ እንደሚሰበሰብ ታሳቢ ተደርጓል::

እነዚህ የገቢ ግኝቶች ዝርዝር ሁኔታ ሲታይም፤ አንድ ነጥብ 228 ትሪሊዮን ወይም 81 ነጥብ ሦስት በመቶ ያህሉ ከሀገር ውስጥ ገቢ የሚገኝ ሲሆን፤ 235 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብሩ ወይም 15 ነጥብ ስድስት በመቶው ደግሞ ከቀጥታ የበጀት ድጋፍ ርዳታ፣ እንዲሁም 46 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብሩ ወይም ሦስት ነጥብ አንድ በመቶው ከፕሮጀክቶች ርዳታ እንደሚገኝ ይጠበቃል::

ይሄም ሆኖ ለበጀት ዓመቱ ከተያዘው የአንድ ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር በጀት የ416 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ያለ ሲሆን፤ የተጣራው የበጀት ጉድለትም ከጠቅላላው የሀገር ውስጥ ምርት (ጂ.ዲ.ፒ) አንጻር ሲታይ ድርሻው የአንድ በመቶ ነው:: ይሄን ጉድለት ከቀጥታ በጀት ድጋፍ፣ ከፕሮጀክቶች ብድር እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን ዕቅድ ተይዟል::

ለ2018 በጀት ዓመት የተያዘው የበጀት መጠን ለ2017 በጀት ዓመት ተይዞ ከነበረው የአንድ ነጥብ 43 ትሪሊዮን ብር አኳያ ሲታይ፤ እጅጉን ከፍ ያለ ዕድገት የታየበት ነው:: ይሄ ደግሞ እንደ ሀገር እያደገ የመጣውን የልማት ፍላጎት መመለስን ታላሚ ከማድረጉም በላይ፤ የተጀመረው ዘርፈ ብዙ የልማት ግስጋሴ ላይ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ይጠበቃል::

ከዝርዝር የበጀት ረቂቁ መረዳት እንደሚቻለው፤ በጀቱ በዋናነት በሀገር ውስጥ የገቢ አቅም የሚሸፈን ነው:: የሀገር ውስጥ ብድርም በእጅጉ የቀነሰ ነው:: የበጀት ጉድለቱም ቢሆን ከሀገራዊ ጥቅል ምርት አኳያ የአንድ በመቶ ድርሻ ብቻ ይዟል::

እነዚህ እና ሌሎች በረቂቅ በጀቱ የተመላከቱ እውነታዎች የሚያሳዩት፤ እንደ ሀገር እያደገ የመጣው የበጀት ፍላጎቱ ብቻ ሳይሆን፤ በጀት የመያዝ እና ያንን በጀት በአመዛኙ በራስ አቅም የመሸፈን ልምምድንም ነው:: ከዚህም በላይ እንደ ሀገር ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና አቅም ስለመፈጠሩም መልካም ማሳያ ነው::

ምክንያቱም፣ አንድ ሀገር ከፍ ያለ የበጀት ፍላጎት አለ ማለት እያደገ የመጣ ኢኮኖሚ ተፈጥሯል ማለት ነው:: አለፍ ሲልም፣ የበጀት ፍላጎትን የውጪ ጥገኝነትና የበጀት ጉድለት ሸክሙ አነስተኛ ሆኖ በራስ የውስጥ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ ለመሸፈን ቻለች ማለት፤ በጀት የሚፈልግ ብቻ ሳይሆን በጀቱን በራሱ የሚሞላ የኢኮኖሚ ዕድገት ባለቤት ሆናለች ማለት ነው:: ከዚህ አኳያ ሲታይ የበጀቱ ማደግ የሀገራዊ ዕድገቱ ጥሩ ምስክር ሆኖ ነው !

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You