የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1945 ሥራ እንደጀመረ ይነገራል። አየር መንገዱ ስራውን የጀመረው በአሜሪካ ሠራሾቹ የአየር ኃይል አውሮፕላኖች ሲሆን፤ በጊዜው ተቋሙን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት አፄ ኃይለሥላሴ ከኩባንያው ጋር በፈፀሙት ስምምነት ነው። አየር መንገዱን ያቋቋመው ዛሬ ገበያ ላይ የሌለው የአሜሪካኑ ትራንስ ዎርልድ አቪዬሽን ነበር ሲል ያስታወሰን ቢቢሲ ነው። አየር መንገዱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በአፍሪካም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በአገልግሎት አሰጣጡ የጥራት ደረጃ አስተማማኝ ሆኖ ዘልቋል።
አየር መንገዱ ይህን ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ረገድ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሽልማት ሲያበረክቱለት ከታላቅ ምስጋና ጋር ነው። ምንም እንኳን አየር መንገዱ አኩሪና ስኬታማ አገልግሎት እየሰጠ ቢጓዝም በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የተለያዩ አደጋዎችን አስተናግዷል። እነዚህ አደጋዎች ግን ተቋሙን ከስኬታማነት አልገቱትም። በአፍሪካ ታላቅ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተበረከቱለት ሽልማቶች ውስጥ የባለ 4 ኮከብ የአየር መንገድ ደረጃን ከስካይትራክስ እና የበረራ የምግብ አገልግሎት የአፍሪካ ምርጥ በመሆን ፓክስ ከተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ያገኘው ሽልማት ተጠቃሽ ናቸው።
ሌላው በዓለም ቁጥር አንድ የአቪዬሽን ፋይናስ ተቋም በሆነው ኤየርላይንስ ኢኮኖሚስ የአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ የአመቱ ምርጥ አየር መንገድ ሽልማት አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል። ከእነዚህ በተጨማሪ የአህጉር አቀፍ እና አለም አቀፍ ሽልማቶች ባለቤት ነው። እነዚህ ተቋማት የአየር መንገዶችን ደረጃ እና ጥራት በዓለም አቀፍ መስፈርቶች በመመዘን እውቅና እና ሽልማት የሚሰጡ ዝነኛና ተአማኒ ናቸው። በዚህም ተቋማቱ ምዘናዎችን የሚያካሂዱት ግልጽ እና ሙያዊ በሆነ የኦዲት አሰራር እና የአገልግሎት ጥራት ደረጃዎች ትንታኔ ላይ በመመስረት በመሆኑ ሽልማቱ አኩሪም ጭምር ነው።
ደንበኛ ተኮሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም-አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቁ ምርቶችና በላቁ አገልግሎቶች የደንበኞችን ከፍተኛ እርካታ ለማረጋገጥ አዘውትሮ በሰራው ብርቱ ስራ ፍሬ እያፈራ በስኬታማነቱም እየተመሰከረለት ዛሬ ላይ ደርሷል። ችግሮች ቢገጥሙትም ዛሬም እንደ ትናንቱ ይህን አስጠብቆ ጉዞውን ይቀጥላል። ለዚህም ስኬት ከ12 ሺህ የሚልቁ ታታሪ ሰራተኞቹ ሊመሰገኑ ይገባል። አየር መንገዱ ምንም እንኳ ሰሞኑን በደረሰው የቦይንግ 737-8 ማክስ ET302 አደጋ ችግር ውስጥ ቢሆንም ዛሬም የአፍሪካው ምርጥ በመሆን የሚታወቅ ነው ። አየር መንገዱ አፍሪካ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ጥቂት አየር መንገዶች ትልቁና ታማኝ አገልግሎቱን እየሰጠ ነው። በመሆኑም ተቋሙ ለበርካታ ዓመታት በሚታወቅበት የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃው በስኬታማነት እንደሚቀጥል ትልቅ እምነት አለ።
አደጋው ከተከሰተ በኋላ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የቦይንግ 737 ማክስ 8አውሮፕላኖችን ለጥንቃቄ ከበረራ ውጪ አድርገዋል። አገራቱ ይህን የወሰኑበት ዋናው ምክንያት አውሮፕላኑን ያጋጠመው አደጋ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ሁለተኛው በመሆኑና የ157 ሰዎች ሕይወት በመጥፋቱ ነው። በመሆኑም አውሮፕላኑን ከበረራ በማገድ እንግሊዝ ማሌዥያን፣ ሲንጋፖርን፣ ቻይናንና አውስትራሊያን ተቀላቅላለች። የእንግሊዝ ሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤት ላልተወሰነ ጊዜ እገዳው እንደሚቀጥል ሲያሳውቅ የአየር ቀጣናዋን መጠቀም እንዳይችል በማገድ ጭምር ነው።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው እ.አ.አ. በ2017/2018 በጀት ዓመት አየር መንገዱ 245 ሚሊዮን ዶላር ሲያተርፍ ከአሥር ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን በማመላለስ ነው። ተቋሙ ከራሱ አልፎ የሌሎች አፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን በመርዳትም በስኬታማነቱ ይታወቃል። በዚህ እርምጃው በማላዊ አየር መንገድ 49 በመቶ ፣ በዛምቢያ 45 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያለው ሲሆን፤ በሞዛምቢክም በአዲስ መልክ አየር መንገድ ስራ የማስጀመር ፕላን እንዳለው ቀደም ብሎ አስታውቋል። በተመሳሳይ ትንንሽ አካባቢያዊ ጣቢያዎችን በጅቡቲ፣ ቻድ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ለመክፈት ንግግር ላይ ነው።
እንደ ማላዊና ቶጎ ባሉ አገራት አሁንም ማእከላት አሉት። በዚህ መልኩ ችግር ውስጥ የገቡ የአፍሪካ አየር መንገዶችን መታደግ ተቋሙን በኢንዱስትሪው ትልቅ አድርጎታል ይህንንም ስኬታማነቱን ይዞ ሊቀጥል ይገባል። በአጠቃላይ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት እያከናወነ ያለው ማስፋፊያ በአፍሪካ አቬዬሽን ወደ ሌላ ከፍታ ይወስደዋል ተብሎም ይታመናል። ተቋሙ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙትን ሰሞነኛ አደጋዎች ከታታሪ ሰራተኞቹ ጋር በፅናት በማለፍ በስኬታማነቱ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011