
ስትሄድ አንድም በውበቷ፣ አንድም ለእናት ሀገሯ ነበር። “ሲኬድ ራስን ወክሎ አይደለም። ብዙ ሰው ባይገነዘበውም የምትወከለውና እኔም ወክዬ የምሄደው ሀገሬን ነው” ስትል ከመሄዷ በፊት ተናገራ ነበር። የሚያውቋት ግን ጥቂቶች ነበሩ፤ ስትመለስም ማን እንደሆነች ብዙዎች አወቋት።
‹ጀግና› ብለው የክብር አቀባበል አደረጉላት። ‹ውብ- የዓለም› ብለው ቁንጅናዋን አረጋገጡላት። ኢትዮጵያዊቷ የዓለም ቆንጂት፣ ሞዴል ሐሴት ደረጀ በሕንድ ሀገር በነበራት የአንድ ወር ቆይታ ሁሉንም ታሪኮች ካለመኖር ወደ መኖር ለውጣቸዋለች። የቆነጃጅት አደባባይ የሆነችው ኢትዮጵያ ስሟ ለመነሳት ከብዶት በኖረበት የዓለም የቁንጅና መድረክ ላይ በሐሴት ተወክላ ሐሴት ከፍ አድርጋ አነሳችው።
ለራሷም ለሀገራችንም የመጀመሪያ የሆነውን አዲስ ታሪክ አጻፈች። ሕንድ ላይ በተካሄደው በ72ኛው የዓለም የቁንጅና ውድድር ላይ ከዓለም 2ኛ፣ ከአፍሪካ 1ኛ በመሆን የ2025 ‹የሚስ ወርልድ› ማዕረግ ተቀዳጅታለች።
ጉዳዩ ቆንጆ ስለመሆን ወይንም ውብ-የዓለም ልጅ ስላለችን በቁንጅና የመመጻደቅ አይደለም። ጉዳዩ የሀገር ክብር፣ የኢትዮጵያ ከፍታ ነው። ከሀገሬው ቆነጃጅት መካከል ኩልል ካለው የምንጭ ውሀ ፈልቃ የውበትን ደምግባት የተሞላችው ሐሴት ደረጀ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ዓርማዋን ይዛ በቆመችበት ታላቅ መድረክ ላይ የገለጠችው የራሷን ውበት ሳይሆን በርሷ ውስጥ የነበረችውን ውብ እመቤቷን ኢትዮጵያን ነው። ኢትዮጵያ ተወዳደረች፣ ኢትዮጵያ አሸነፈች። “ኢትዮጵያ ተብዬ እየተጠራሁ ኢትዮጵያውያን ካላገዙኝማ…” በእርግጥም ይህ ደግ አይደለም። ‹የእኛ ልጅ በርቺ በርቺ፣ እንዳትረቺ!› ያልናትንም ሆነ ያላልናትን ዓለም ሲያጨበጭብላት፣ ከኢትዮጵያ ውስጥ ለእኛም አስጨብጭባልናለች።
ሚያዚያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ነበር ሐሴት የሀገሯን ሰንደቅ በአደራ ተረክባ፣ ቦሌ አየር ማረፊያ በተደረገላት ሽኝት፣ ዓርማዋን ከውስጧ ወኔውን ታጥቃ ወደ ሕንድ በረረች። በ72ኛው የዓለም የቁንጅና ውድድር ኢትዮጵያን ይዛ የድሉን መንገድ ቀጠለች። 24 ከባድ የውድድር ቀናት፣ 108 የዓለም ሀገራት ቆነጃጅት ስለ ሀገራቸው ክብር ተፋጠጡበት። ሐሴት የመጨረሻው የድል ብሥራት ደወል እስኪያቃጭል ድረስ ፈታኝ ጊዜያትን እንዳሳለፈች አልሸሸገችውም። ሃያ አራቱ የውድድር ቀናት ከሌላው ተወዳዳሪ በተለየ ያስጨነቋት ብዙ ነገሮች ነበሩ።
በወቅቱ በርቀትም ቢሆን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ድጋፉን ሊያደርግላት እየጣረ የነበረ ቢሆንም፤ እንደ መንግሥትም ይሁን እንደ ማኅበረሰባችን ወክሏት እንደሄደች ተወዳዳሪ ግን አልነበረችም። ቢውቱ ኪውንስ የተባለውና ለ13 ዓመታት በኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር ላይ ሲሠራ የነበረው ተቋም ከሐሴት ጋርም አብሮ ሲሠራ ነበር። ለዚህ እንድትበቃም ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል። “በጣም ብዙ ነገር ነበር የተቸገርኩት፣ ግን እግዚአብሔር ይመስገን ካሠኝ” ነበር ያለችው፤ ከድል በኋላ በደስታ ሲቃ ታጅባ። በዚህ አስቸጋሪ ቆይታዋ በአልባሳትና መሰል ነገሮች የተቻላቸውን ድጋፍ ያደረጉላት ግለሰቦች እንደነበሩ ገልጻ አመስግናለች።
ሐሴት እየገጠሟት ከነበሩት ብዙ ፈተናዎቿ አንጻር በውድድሩ አሸንፋለሁ የሚል ተስፋዋ መንምኖ እንደነበር አልደበቀችውም። ሆኖም ማንም ባልጠበቀበት ክስተት ሆና ታየች። ውበት ኩራቱ-ኩራት ደም ግባቱ ለሆነው ሓበሻ ድሉ በእርግጥም አኩሪ ነው። ሽንፈት ለሚያመው ኢትዮጵያዊ አሸናፊነቱ ጮቤ የሚያስረግጥ ነበር። ‹ኢትዮጵያ አሸነፈች› ሲባል ደስ የማይለው ማን አለ? በዚያች ቅጽበት ልዩነቶችን እረስተን ሁላችንም በአንድ ልብ በአንድ ስሜት ‹ኢትዮጵያ!› ብለናል።
ይህን ሁሉ ያገኘነው ታዲያ ትኩረት በነፈግነው የቁንጅና ዘርፍ ነው። ትኩረት ማጣቱ ቅር ያሰኛት ሐሴት ወደ ሕንድ ከማቅናቷ በፊት እንዲህ ብላ ነበር “እዚያ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ መባሉ በጣም ትልቅ ነገር ነው፤ አለመታጣችንም አንድ ነገር ነው፡፡” ምስጋናው ለርሷ ይሁንና ካለመታጣት በድል ወደ መጠራት ተሸጋግረናል። ከተሳታፊነት ወደ አሸናፊነት ስም ዝርዝር ገብተናል። ይህን ያገኘነው ግን ቆንጆ በመሆን ብቻ ሳይሆን፤ በብዙ ፈተናና ተጋድሎ ነው።
“ውድድሩ የቁንጅና ብቻ መስሎ የሚታያቸው አሉ፤ ነገር ግን ከቁንጅና በላይ የሆነ ነገር አለው” በማለት የዚህን መድረክ ትልቅነት ትገልጻለች። ትናንትም ሆነ ዛሬ ዓላማዋ ‹ቆንጆ› የመባል አይደለም። ከውስጧ የነበረው የአካላዊ ቁንጅና መንፈስና ስሜት አነበረም፤ የነበረው ልብ ላይ የሚያንጸባርቅ ኢትዮጵያዊነት ነበር። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለው ደግሞ አንድ ገጽ፣ አንድ መልክ አይደለም። “ኢትዮጵያ ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ባለባት ሀገር ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ሀበሻ ቀሚስ እያደረግን መቆም የማይሆን ነው” እንዳለችው ለዓለም ያሳየቻት ኢትዮጵያ ለብዙዎቻችን አዲስና ምንም የማናውቃት እስክትሆንብን ድረስ ነበር።
ቁንጅናው የመልክ ብቻ እንዳልሆነ ውድድሩም ቢሆን የሚናገረው ነው። እያንዳንዱ ተወዳዳሪ ስለ ሀገሩ የሚያደርገው ገለጻና ባህልና ወጉን የሚያስተዋውቅበት መንገድ፣ ከአቀራረቡ ጋር ለውድድሩ ነጥብ የሚያዝበት ብቻ ሳይሆን ትልቅ ዋጋ ያለው ነው። ራሱን የቻለ ቁንጅና ነው። ቁንጅና ማለትም “…የመልክ ብቻ አይደለም። አስተሳሰብ፣ አነጋገር፣ አኳኋን፣ ሰዎችን የምንቀበልበትና የምናስተናግድበት፣ እንዲሁም ማንነታችን የምንገልጽበት መንገድም ጭምር ነው። አንድ ሰው በመልኩ ቆንጆ ሆኖ እነኚህን መሰል ነገሮች ከሌሉት የዚያ ሰው ቁንጅና ዋጋ የለውም። ከውጫዊ ውበት በላይ የሚንፀባረቀው ውስጣዊ ውበት ነው ለኔ ቆንጆ ማለት።”
ከውበቷ ጋር በዓለም መድረክ ሐሴትን ያቆነጀው ይሄው ቁንጅናዋ ነበር። ሀገሯ በእርሷ አንደበት ስትገለጽ ልዩ ውበት ነበራት። ያሳለፈችበትን የውድድር መድረክ የተከታተልን በእርግጥም ይህን ውበት እንመለከተዋለን። “ስሜን እንኳን ሲጠሩ ኢትዮጵያ እያሉ ነው” ስትል በሀገረ ሕንድ በነበራት ቆይታ ሐሴት ማን ብለው ሲጠሯት እንደነበር ትገልጻለች። ታዲያ ካስጠሩ አይቀር እንዲህ ስሟን ተሸክሞ ነው እንጂ።
የሐሴት ውበት አሁን ዘነበ እንጂ ያካፋው ገና ድሮ ነበር። ቁንጅናዋ በድል ሲዘንብ የታየው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነበር። በጊዜው ስትማር በነበረችበት ካቴድራል ትምህርት ቤት ውስጥ ከተካሄደው የቁንጅና ውድድር የነገይቱ ወይዘሪት ኢትዮጵያ ብቅ አለች። ከውበቷ ውስጥ የሚፈልቅ እፁብ ኢትዮጵያዊነት ያኔም እንደነበራት ለመገንዘብ ይቻላል። ግራና ቀኝ፣ ከሕንጻው ላይና ታች እጅብ ብሎ ተማሪው ሁሉ የቆነጃጅቱን ሽር ብትን በተመስጦ ሲመለከት ነበር። በቀይ ደማቅ ቀሚስ፣ በቢጫው ተስፋ ሹራብ፣ ፀጉሯን ጉንጉን ጋሜ ለቃ፣ ከግንባሯ ወርቃማውን ዶቃ አስራ፣ ከጎኗ ያጀባትን የነጭ ፈረስ ልጓሙን በመጨበጥ፣ አረንጓዴውን የባንዲራ ክንፍ እንደ ንግሥት ካባ ከኋላዋ እየጎተተች፣ ሰከም! ሰከም! ስትል ከተማሪው መሐል ሰንጥቃ አለፈች። የዚያን ዕለት ሐሴት “ሚስ ካቴ ኢትዮጵያ” ሆና አሸነፈች።
ኢትዮጵያዊነት ውበት፣ ውበትም ኢትዮጵያዊነት የሆናት ሐሴት ደረጀ ከካቴድራሉ ድል በኋላ ጉዞዋን ይበልጥ አሳመረችው እንጂ አልገታችውም። የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን በድል አጠናቃ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስታቀና ቁንጅናውም መንገዱ ቀና ሆነላት። የ1ኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ልታጠናቅቅ አካባቢ ሐሴት ሁለተኛውን የውበት ፋኖስ የምታበራበትን ዕድል ተገናኘች። በክረምቱ የቁንጅና ዝናብ ‹በሚስ ኢንተርናሽናል› ውድድር ላይ ተሳትፋ 2ኛ በመውጣት ያኔም አሸነፈች። ሞዴሏ ሐሴት ደረጀ ሦስተኛዋን የቁንጅና ውድድር አድርጋ ድሏን ለመሠለስ ጉዞዋን ወደ ደቡብ አፍሪካ አደረገች። በደቡብ አፍሪካ በሚደረገው “ሚስ ቲ ዩኒቨርስ› የቁንጅና ውድድር ላይ አቀራረቧም ሆነ አካሄዷ ሀገሯን ወክላ ነበር። ይሁን እንጂ የሌሎች ሀገራት ተወዳዳሪዎች በአጃቢ ሚዜዎቻቸው ተከበው ሐሴት ግን ስትሄድ ብቻዋን ለብቻዋ እንደነበረች ትናገራለች። በሄዱበት ሁሉ ያገር ልጅ አይጥፋና ከዚያ የነበሩ ተቀብለው ጎኗ እንደቆሙም አልዘነጋችውም። ብርቱው የመንፈስ ጥንካሬዋም አልተገታም። ለ14 ቀናት ቆይታ በነበረው ውድድር ሐሴት ከምርጥ 20ዎቹ ለመግባትም ችላ ነበር። ከዚህ ውድድር አንድ ሳምንት ዘገየት ብሎ ደግሞ ‹የሚስ ወርልድ› ቆነጃጅት ምልመላ ተጀመረ። የተሳካው ምልመላ፣ ያሳካችውን ሐሴትን ለዚሁ ድልና ታሪክ አጫት።
ሐሴት ቆንጆ ናት። ሐሴት ተፈጥሮ የውበት ፀዳሏን ያደለቻት፣ ከውብ ሰማይ ስር የወጣች ደማቅ ጨረቃ ናት። የደስ ደስ የተሞላች ጠንበለል። ‹ችቦ አይሞላም ወገቧ› የሚባልላት፣ ሽንቅጥቅጥ ያለች ሎጋ። ውበትን ለመግለጽ የምንጠቀማቸው ቃላት ሁሉ ‹ይገባታል› ብንል የማይበዛባት ቆንጆ ናት። ለርሷ ግን ውበት ይህ አይደለም። ቁንጅናዋ የውስጧ ፀዓዳነት ነው። እዚያ መድረክ ላይ ቆማ ኢትዮጵያን ያስጠራችበት ውበት ግን ይሄ ብቻ አይደለም። እዚህ ውበት ላይ ፀዓዳው ውስጣዊ ውበት ሲጨመርበት ያኔ ነው ውበት ማለት። ያኔ ነው ሰማይ በሙሉ ጨረቃ በክዋክብት ታጅባ የምትወጣው። ስለ ሐሴት የሚናገሩ ሁሉ ከአካላዊ ቁመናና መልኳ ይልቅ ከአፋቸው የሚቀድመው ስለ ውስጧ መግነጢሳዊ እምቅ ውበት ነው። በውበት ላይ ውበትን ሲያድላት እንደገና ሌላ አንደበተ ርቱዕነትን ሠለሰላት። ከዚያ መድረክ ላይ ለውድድር ቆማ ስትናገር፣ ኢትዮጵያዊነትን ተላብሶ ከለመለመው ማንነቷ የውስጧን በአንደበቷ ስትገልጸው ሲሰማት የነበረውን የዓለምን አፍ ሁሉ ያስከፈተ እንደነበር እኛም ተመልክተን ይሆናል።
ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም ቦሌ አየር ማረፊያ፤ በሚያዚያ 29 የሸኘቻትን ሞዴል ሐሴት ደረጀን ለመቀበል ክንፎቿን ዘርግታ ስትጠባበቃት ነበር። ካሜራዎቻቸውን የደገኑ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካቶች የጀግና አቀባበል ለማድረግ በልዩ መስተንግዶ (VIP) ስፍራ ላይ አኮብኩበዋል። የኢትዮጵያ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ ሥነጥበብና ዕደ ጥበብ ዘርፍ ኃላፊዋ ክብርት ነፊሳ አልማህዲ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ ረ/ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዋ ዶክተር ሂሩት ካሣው በአየር ማረፊያው ከተገኙት መካከል ናቸው።
ልክ ቀትር 8 ሰዓት ሲሆን ጀግናዋን በውብ አበባ በባንዲራው እቅፍ፣ ባማረ የክብር አቀባበል ታጀበች። ሀገር…ክብር…ድል…ደስታ…ውስጧን ፈንቅለው በእንባ ሲቃ ደፈቋት። ተዘርግቶ ካቀፋት ባንዲራ ውስጥ ኢትዮጵያ በአካለ ሥጋ እየታየቻት ወደ ጆሮዋ ጠጋ ብላ ‹ኮራሁብሽ የኔ ጀግና ልጅ!› የሚል ድምፅ…እያቃጨለ፣ በደምስሯ እየተላወሰ ዓይነት ይሆን? ብዬ ባሰብኩት የሞኝ ጥያቄ ውስጥ፤ ሐሴትን ያስለቀሳት የደስታ እንባ፣ የተሰማት ስሜት ሁሉ ኢትዮጵያን ይሰማታል አልኩኝ። “ኢትዮጵያ ኮርታብሻለች” ያሉት ክብርት ነፊሳ አልማህዲ ግን “ከእንግዲህ የባህል አምባሳደራችን ነሽ” በማለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ላሰበላት የክብር ሹመት፣ የአምባሳደርነት ሰርተፍኬቱን እዚያው አበርክተውላታል።
ሐሴት በብዙ ውጣውረድ አቆራርጣ አልፋ አሁን ተስፋ ብቻ ሳትሆን ለሀገሯ አምባሳደር ሆናለች። ይህንን ሁሉ ስኬታማ ድል ስትቀዳጅ ገና ተማሪ ናት። በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሁለተኛ ዓመት የኬሚካል ኢንጅነሪንግ ተማሪ ናት። የእርሷን ስኬት፣ ዛሬ የደረሰችበትን ትልቅ ስፍራ ስናስብና ስናነሳ ወላጆቿን ብንረሳቸው ቅሬታዋ የዋዛ አይሆንም። ሀገሯን እንዳስጠራችው ሁሉ ቤተሰቦቿን ሳትጠራ እርሷም አታልፈውምና። “እናቴ ፖሊስ ናት፣ አባቴ ደግሞ ሹፌር ነው፤ እንዲህ ሆነው ነው ያሳደጉኝ። ሲያሳድጉኝ እኔ ላይ በጣም ብዙ ኢንቨስት አድርገው ነው፡፡” ልጃቸው ላይ ብዙ ኢንቨስት ያደረጉ ወላጆቿ በእርግጥም ብዙ እጥፍ አተረፉ እንጂ አልከሰሩም። የእነርሱን ቁንጥጫቸውን እንኳን እያሰበች ዛሬ እዚህ ለመድረሷ መድኃኒት እንደሆናት ታወራለች። ለቁንጅናዋ በመጀመሪያ ዓይኖቻቸው የተገለጠውና የተመለከቷት እናትና አክስቷ እንደነበሩም ሐሴት ታስታውሳለች። ያኔ “አንቺ እኮ…” ባይሏትና በልጅነት ልቧ ውስጥ ባይዘሩት ኖሮ ምናልባትም ፍላጎቱ ባልተወለደና ውበቷም የጋን መብራት በሆነ።
ከዚህም ከዚያም፣ ከወጀብ ከነፋሱም፣ ከውበት ከፀዳሉም፣ ከዕንባ ከፈገግታውም ጋር ሁሉ አልፋ አሁን ከማማው ላይ ቆማለች። ከሠገነቱ ላይ ተሰይማለች። ብዙ ዓይኖች ሊያይዋት በተስፋ ያንጋጥጣሉ። ብዙ ልቦች በሐሴት ሊቀበሏት ይጠባበቃሉ። ወይዘሪት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ወይዘሪት አፍሪካም ጭምር ናትና አፍሪካውያን ሁሉ ከእርሷ ጋር ስለመሥራት ያስባሉ። እርሷም አሕጉራዊ ግዴታዋ ነውና ለጥሪ ድምፃቸው ‹አቤት› ማለትን አትታክትም። ከምንም ከማንም ግን ሀገሯ ሁሌም የመጀመሪያዋ ናት። “እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማድረግ የምፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ” የምትለው ሐሴት ቀደም ሲል ከሁለት የርዳታ ድርጅቶች ጋር የነበራትን ሥራ በተሻለ ሁኔታ ማስቀጠል እንደምትፈልግም ገልጻለች። ‹ኢትዮጵያዊነት መልካምነት› የሚለውን በጎነቷን በተግባር እየኖረች ካለችባቸው መካከል አንደኛው “መስጠት” የተሰኘው ጎዳና ወድቀው ጧሪ ደጋፊ ያጡትን እናቶች የሚረዳ ሠናይ ድርጅት ነው። ሁለተኛው ደግሞ “ማያ ፋውንዴሽን” ነው። “ለወሬ ድምቀት ላደርጋቸው አይደለም የምፈልገው” ስትል የምትፈልገውና ለማድረግ የምታስባቸው ብዙ ነገሮ ች እንዳሉ ትናገራ ለች።
አሁንም ኢትዮጵያዊ ማንነቷን ከእንደራሴነቷ ጋር ደርባ ዓለምን የምትዞርባቸው በሮች ሁሉ ተከፍተው ይጠብቋታል። እናም “የኢትዮጵያን ገጽታ መቀየር እፈልጋለሁ” ትላለች። ብዙ ታሪክ ብዙ ጀብዱ እንዳለን ስናወራ፣ ስንፎክርና ስንሸልል “ያሉንን ታሪኮቻችንን ራሳችን ለራሳችን እንነግራለን እንጂ እነርሱ አያውቁም። ስነግራቸው በጣም ነበር የሚደነቁት” ብላ ሐሴት ስትነግረን ግን በራሳችን ከንቱ ዲስኩር እንሸማቀቅ ይሆናል። እዚያ ማዶውን ረስተን እዚሁ ለዚሁ ስናጉተመትም ስንት ያለን ታላቅነት ሊወይብባቸው አይገባም። ሐሴትም “ኢትዮጵያን እነርሱ ላይ መሳል እፈልጋለሁ” ትላለች።
ያወቁበት አሁን በፋሽንና የሞዴሊንግ ዘርፍ በቢሊዮን ዶላር የሚያፍሱበት ነው። እዚሁ አፍሪካና ጎረቤቶቻችን እንኳን ከእኛ በተሻለ እየተጠቀሙበት እንደሆን ሐሴት ትገልጻለች። ታዲያ የውበት መስፈሪያ ቁና አድርገን በምንጠራት ሀገራችን ውስጥ ካወራንም ማውራት ያለብን ዓለም እንዴት ወደዚህ ዥረት መጉረፍ እንዳለባቸው እንጂ ገና ትኩረት ስለመስጠት መሆን የለበትም። “በሚቀጥሉት ዓመታት ላይ ከመሳተፍ አልፈን ማዘጋጀት ላይ ብንደርስ፣ ወደ ሀገራችን የሚመጡት ከመቶ በላይ የሆኑ ሀገራት ናቸው” ታዲያ ምን እንጠብቃለን?
በሄደችባቸው ስፍራዎች ሁሉ ‹ሐሴት› በሚል ስም የሚያውቃት እንደሌለ የተናገረችው ሐሴትን ሲጠሯት ስሟ “ኢትዮጵያ” ነበር። ታዲያ ግን “…ኢትዮጵያ ተብዬ እየተጠራሁ ኢትዮጵያውያን ካላገዙኝ ትንሽ…” አዎን ትንሽ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ውስጣዊ ቅሬታን ይፈጥራል። ስማችንን በሀገራችን ላስጠራች ጀግና አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ ጎኗ መቆም ከመልካምነት የሚጠጥር የዜግነት ግዴታችንም ጭምር ነው። ታዲያ የእርሷ ንግግርም ሆነ የእኛ ኃላፊነት ስለ አንዲት ሐሴት ብቻ እንዳልሆነ ልብ ይሏል። አንዲት ሐሴት የሁላችንም ድል እንደሆነችው ሁሉ፣ በአንዲት ሐሴት ውስጥ ደግሞ እልፍ ቆነጃጂት ከእልፍ ድል ጋር ይከታተላሉና ለመንገዱ ጥርጊያ የቤት ሥራ አለብን። ተፈጥሮ እንደ ጥቅምት አበባ ካስጌጠው ውበቷ፣ ስለ ሀገሯ ለማውራት ቀናዒነት ከማያጎድለው አንደበቷ ጋር ገና የምንጠብቀው ብዙ ነው። እርሷም ገና መጀመሯ ነው።
ሙሉጌታ ብርሃኑ